የሐዋርያት ሥራ 1:1-26

  • ለቴዎፍሎስ የተጻፈ (1-5)

  • “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” (6-8)

  • ኢየሱስ ወደ ሰማይ አረገ (9-11)

  • ደቀ መዛሙርቱ በአንድነት ተሰበሰቡ (12-14)

  • በይሁዳ ቦታ ማትያስ ተመረጠ (15-26)

1  ቴዎፍሎስ ሆይ፣ ኢየሱስ ስላደረገውና ስላስተማረው ነገር ሁሉ በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ጽፌልሃለሁ፤+  ታሪኩም አምላክ እስከወሰደው ቀን ድረስ ያለውን ያካትታል።+ ለመረጣቸው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያዎች ከሰጣቸው በኋላ አረገ።+  መከራ ከተቀበለ በኋላ ሕያው መሆኑን በብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች አሳያቸው።+ እነሱም ለ40 ቀናት ያዩት ሲሆን እሱም ስለ አምላክ መንግሥት ይነግራቸው ነበር።+  ከእነሱ ጋር ተሰብስቦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤+ ከዚህ ይልቅ አብ ቃል የገባውንና እኔም ስለዚሁ ጉዳይ ስናገር የሰማችሁትን ቃል ፍጻሜ ተጠባበቁ፤+  ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”+  እንደገና ተሰብስበው ሳሉ “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜያትንና ወቅቶችን የመወሰን ሥልጣን ያለው አብ ብቻ ስለሆነ* እናንተ ይህን ማወቅ አያስፈልጋችሁም።+  ሆኖም መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤+ በኢየሩሳሌም፣+ በመላው ይሁዳና በሰማርያ+ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ+ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”+  ይህን ከተናገረ በኋላም እያዩት ወደ ላይ ወጣ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረው።+ 10  እሱ ወደ ላይ እየወጣ ሳለ ትኩር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች+ ድንገት አጠገባቸው ቆሙ፤ 11  እንዲህም አሏቸው፦ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የተወሰደው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ ባያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመጣል።” 12  ከዚያም ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤+ ይህ ተራራ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን ርቀቱ የሰንበት መንገድ* ያህል ብቻ ነበር። 13  እዚያ በደረሱ ጊዜ ያርፉበት ወደነበረው ደርብ ወጡ። እነሱም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና እንድርያስ፣ ፊልጶስና ቶማስ፣ በርቶሎሜዎስና ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናተኛው ስምዖን እንዲሁም የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ነበሩ።+ 14  እነዚህ ሁሉ ከአንዳንድ ሴቶችና+ ከኢየሱስ እናት ከማርያም እንዲሁም ከወንድሞቹ+ ጋር በአንድ ልብ ተግተው ይጸልዩ ነበር። 15  በዚያው ሰሞን 120 የሚያህሉ ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ሳለ ጴጥሮስ በወንድሞች መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ 16  “ወንድሞች፣ ኢየሱስን የያዙትን ሰዎች እየመራ ስላመጣው ስለ ይሁዳ+ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት በኩል በትንቢት የተናገረው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል መፈጸሙ የግድ ነበር።+ 17  ምክንያቱም እሱ ከእኛ እንደ አንዱ ተቆጥሮ የነበረ+ ከመሆኑም በላይ በዚህ አገልግሎት የመካፈል አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። 18  (ይኸው ሰው ለዓመፅ ሥራው በተከፈለው ደሞዝ+ መሬት ገዛ፤ በአናቱም ወድቆ ሰውነቱ ፈነዳ፤* ሆድ ዕቃውም ተዘረገፈ።+ 19  ይህም በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ ታወቀ፤ በመሆኑም መሬቱ በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጉሙም “የደም መሬት” ማለት ነው።) 20  በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ‘መኖሪያው ወና ይሁን፤ በውስጡም ማንም ሰው አይኑርበት’+ እንዲሁም ‘የበላይ ተመልካችነት ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰደው’ ተብሎ ተጽፏልና።+ 21  ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል ሆኖ ሥራውን ያከናውን በነበረበት* ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር ከነበሩት ወንዶች መካከል በአንዱ እሱን መተካት ያስፈልጋል፤ 22  የሚተካው ሰው ኢየሱስ በዮሐንስ ከተጠመቀበት ጊዜ አንስቶ+ ከእኛ እስከተወሰደበት ጊዜ+ ድረስ አብሮን የነበረ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምሥክር መሆን ያስፈልገዋል።”+ 23  ስለዚህ ሁለት ሰዎችን ዕጩ አድርገው አቀረቡ፤ እነሱም በርስያን ተብሎ የሚጠራው ዮሴፍ (ኢዮስጦስ ተብሎም ይጠራል) እና ማትያስ ነበሩ። 24  ከዚያም እንዲህ ብለው ጸለዩ፦ “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቀው ይሖዋ* ሆይ፣+ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል የመረጥከውን አመልክተን፤ 25  ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ለመሄድ ሲል የተወውን ይህን የአገልግሎትና የሐዋርያነት ቦታ የሚወስደውን ሰው ግለጥልን።”+ 26  ከዚያም በሁለቱ ሰዎች ላይ ዕጣ ጣሉ፤+ ዕጣውም ለማትያስ ወጣና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ።*

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “(ጊዜያትንና ወቅቶችን) በራሱ ሥልጣን ሥር ስላደረገ።”
ይህ 890 ሜትር (2,000 ክንድ፤ 2,920 ጫማ) ገደማ ነው። ከኢያሱ 3:4 ጋር አመሣክር።
ወይም “ከመካከሉ ፈነዳ።”
ቃል በቃል “በገባበትና በወጣበት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ተደመረ።” እንደ ሌሎቹ 11 ሐዋርያት መሆኑን ያመለክታል።