ሕዝቅኤል 40:1-49
40 በግዞት በተወሰድን+ በ25ኛው ዓመት፣ በዓመቱ መጀመሪያ፣ በወሩ አሥረኛ ቀን፣ ከተማዋ በወደቀች+ በ14ኛው ዓመት፣ በዚያው ዕለት የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፤ እሱም ወደ ከተማዋ ወሰደኝ።+
2 አምላክ በገለጠልኝ ራእዮች አማካኝነት ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፤ በአንድ ትልቅ ተራራም+ ላይ አስቀመጠኝ፤ በዚያም በስተ ደቡብ በኩል ከተማ የሚመስል ሕንፃ ነበር።
3 ወደዚያ በወሰደኝ ጊዜ መዳብ የሚመስል መልክ ያለው አንድ ሰው አየሁ።+ በእጁም ከተልባ እግር የተሠራ ገመድና የመለኪያ ዘንግ* ይዞ+ መግቢያው ላይ ቆሞ ነበር።
4 ሰውየው እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ በደንብ ተመልከት፤ በጥሞና አዳምጥ፤ የማሳይህንም ሁሉ በትኩረት ተመልከት፤* እዚህ የመጣኸው ለዚህ ነውና። የምታየውን ነገር ሁሉ ለእስራኤል ቤት ሰዎች ተናገር።”+
5 ከቤተ መቅደሱ* ውጭ በዙሪያው ያለውን ቅጥር አየሁ። ሰውየው ስድስት ክንድ ርዝመት ያለው የመለኪያ ዘንግ ይዞ ነበር፤ እያንዳንዱ ክንድ አንድ ጋት ተጨምሮበት ነበር።* እሱም ቅጥሩን መለካት ጀመረ፤ የቅጥሩ ውፍረት አንድ ዘንግ፣ ቁመቱም አንድ ዘንግ ነበር።
6 ከዚያም በምሥራቅ ትይዩ ወዳለው በር+ መጣ፤ በደረጃዎቹም ወጣ። የበሩን ደፍ ሲለካ ወርዱ አንድ ዘንግ ነበር፤ የሌላኛውም ደፍ ወርድ አንድ ዘንግ ነበር።
7 እያንዳንዱ የዘብ ጠባቂ ክፍል ርዝመቱ አንድ ዘንግ፣ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበር፤ በዘብ ጠባቂ ክፍሎቹ+ መካከል ደግሞ አምስት ክንድ ስፋት ነበር። ከበሩ በረንዳ አጠገብ በውስጥ በኩል ያለው የበሩ ደፍ አንድ ዘንግ ነበር።
8 በውስጥ በኩል ያለውን የበሩን በረንዳ ለካ፤ አንድ ዘንግም ሆነ።
9 ከዚያም የበሩን በረንዳ ሲለካ ስምንት ክንድ ሆነ፤ በጎን በኩል ያሉትን ዓምዶችም ሲለካ ሁለት ክንድ ሆኑ፤ የበሩም በረንዳ በውስጥ በኩል ነበር።
10 በምሥራቁ በር ግራና ቀኝ ሦስት ሦስት የዘብ ጠባቂ ክፍሎች ነበሩ። ሦስቱም መጠናቸው እኩል ነበር፤ በሁለቱም በኩል ያሉት ዓምዶችም መጠናቸው እኩል ነበር።
11 ከዚያም የበሩን መግቢያ ወርድ ሲለካ 10 ክንድ ሆነ፤ የበሩ ስፋት ከውጭ በኩል 13 ክንድ ነበር።
12 ከዘብ ጠባቂ ክፍሎቹ ፊት ለፊት ያለው የተከለለ ቦታ በሁለቱም በኩል አንድ አንድ ክንድ ነበር። የዘብ ጠባቂ ክፍሎቹ በሁለቱም በኩል ስድስት ስድስት ክንድ ነበሩ።
13 ከዚያም በሩን ከአንዱ የዘብ ጠባቂ ክፍል ጣሪያ* እስከ ሌላኛው የዘብ ጠባቂ ክፍል ጣሪያ ድረስ ለካ፤ ወርዱም 25 ክንድ ነበር፤ አንደኛው መግቢያ ከሌላኛው መግቢያ ትይዩ ነበር።+
14 ከዚያም በጎንና በጎን በኩል ያሉትን ዓምዶች ቁመት ሲለካ 60 ክንድ ሆነ፤ በግቢው ዙሪያ በሚገኙት በሮች ላይ ያሉትንም ዓምዶች ለካ።
15 ከመግቢያው በር ፊት አንስቶ በበሩ ውስጠኛ ክፍል በኩል እስካለው በረንዳ ፊት ድረስ 50 ክንድ ነበር።
16 ከበሩ በውስጥ በኩል በግራና በቀኝ፣ የዘብ ጠባቂ ክፍሎቹና በጎን ያሉት ዓምዶቻቸው እየጠበቡ የሚሄዱ ክፈፎች ያሏቸው መስኮቶች* ነበሯቸው።+ በረንዳዎቹም በውስጥ በኩል፣ በግራም በቀኝም መስኮቶች ነበሯቸው፤ በጎን ያሉት ዓምዶች ደግሞ የዘንባባ ዛፍ ምስሎች ተቀርጸውባቸው ነበር።+
17 ከዚያም ወደ ውጨኛው ግቢ አመጣኝ፤ በግቢውም ዙሪያ የመመገቢያ ክፍሎችና*+ መመላለሻ መንገድ አየሁ። በመንገዱ ላይ 30 የመመገቢያ ክፍሎች ነበሩ።
18 በበሮቹ ጎን ያለው መመላለሻ መንገድ ከበሮቹ ርዝመት ጋር እኩል ነበር፤ ይህም የታችኛው መመላለሻ መንገድ ነበር።
19 ከዚያም ከታችኛው በር አንስቶ ወደ ውስጠኛው ግቢ እስከሚያስገባው በር ድረስ ያለውን ርቀት* ለካ። በምሥራቅም ሆነ በሰሜን በኩል ያለው ርቀት 100 ክንድ ነበር።
20 የውጨኛው ግቢ ከሰሜን ጋር ትይዩ የሆነ በር ነበረው፤ እሱም ርዝመቱንና ወርዱን ለካ።
21 በሁለቱም ጎን ሦስት ሦስት የዘብ ጠባቂ ክፍሎች ነበሩ። በጎን ያሉት ዓምዶቹና በረንዳው መጠናቸው ከመጀመሪያው በር ጋር እኩል ነበር። ርዝመቱ 50 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 25 ክንድ ነበር።
22 የመስኮቶቹ፣ የበረንዳውና የዘንባባ ዛፍ ምስሎቹ+ መጠን በምሥራቁ በር ካሉት ጋር እኩል ነበር። ሰዎች ሰባት ደረጃዎች ወጥተው ወደዚያ መግባት ይችላሉ፤ በረንዳውም ከፊት ለፊታቸው ነበር።
23 በውስጠኛው ግቢ፣ ከሰሜኑ በር ትይዩ አንድ በር፣ ከምሥራቁ በር ትይዩ ደግሞ ሌላ በር ነበር። እሱም ከአንደኛው በር እስከ ሌላኛው በር ሲለካ 100 ክንድ ሆነ።
24 ከዚያም ወደ ደቡብ አቅጣጫ አመጣኝ፤ በስተ ደቡብ በኩል አንድ በር አየሁ።+ እሱም በጎን ያሉትን ዓምዶቹንና በረንዳውን ለካ፤ መጠናቸውም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር።
25 በበሩና በበረንዳው ግራና ቀኝ እንደ ሌሎቹ ዓይነት መስኮቶች ነበሩ። ርዝመቱ 50 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 25 ክንድ ነበር።
26 ወደዚያ የሚወስዱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤+ በረንዳውም ከፊት ለፊታቸው ነበር። በግራና በቀኝ ባሉት ዓምዶች ላይ አንድ አንድ የዘንባባ ዛፍ ምስል ተቀርጾ ነበር።
27 የውስጠኛው ግቢ ከደቡብ ጋር ትይዩ የሆነ በር ነበረው፤ እሱም ወደ ደቡብ አቅጣጫ ከአንደኛው በር እስከ ሌላኛው በር ለካ፤ ርቀቱም 100 ክንድ ሆነ።
28 ከዚያም በደቡብ በር በኩል ወደ ውስጠኛው ግቢ ወሰደኝ፤ የደቡቡን በር ሲለካ መጠኑ ከሌሎቹ ጋር እኩል ሆነ።
29 የዘብ ጠባቂ ክፍሎቹ፣ በጎን ያሉት ዓምዶቹና በረንዳው መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር። በበሩና በበረንዳው ግራና ቀኝ መስኮቶች ነበሩ። ርዝመቱ 50 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 25 ክንድ ነበር።+
30 ዙሪያውን በረንዳዎች ነበሩ፤ ርዝመታቸው 25 ክንድ፣ ወርዳቸው ደግሞ 5 ክንድ ነበር።
31 በረንዳው ከውጨኛው ግቢ ጋር ትይዩ ነበር፤ በጎን ባሉት ዓምዶቹም ላይ የዘንባባ ዛፍ ምስሎች ነበሩ፤+ ወደዚያም የሚወስዱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ።+
32 በምሥራቅ በኩል ወደ ውስጠኛው ግቢ ሲወስደኝ በሩን ለካ፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር።
33 የዘብ ጠባቂ ክፍሎቹ፣ በጎን ያሉት ዓምዶቹና በረንዳው መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር፤ በበሩና በበረንዳው ግራና ቀኝ መስኮቶች ነበሩ። ርዝመቱ 50 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 25 ክንድ ነበር።
34 በረንዳው ከውጨኛው ግቢ ጋር ትይዩ ነበር፤ በግራና በቀኝ ባሉት ዓምዶች ላይ የዘንባባ ዛፍ ምስሎች ተቀርጸው ነበር፤ ወደዚያም የሚወስዱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ።
35 ከዚያም ወደ ሰሜን በር+ ወሰደኝና ለካው፤ መጠኑ ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር።
36 የዘብ ጠባቂ ክፍሎቹ፣ በጎን ያሉት ዓምዶቹና በረንዳው መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር። በግራና በቀኝ መስኮቶች ነበሩት። ርዝመቱ 50 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 25 ክንድ ነበር።
37 በጎን ያሉት ዓምዶቹ ከውጨኛው ግቢ ጋር ትይዩ ነበሩ፤ በግራና በቀኝ ባሉት ዓምዶቹ ላይ የዘንባባ ዛፍ ምስሎች ተቀርጸው ነበር፤ ወደዚያም የሚወስዱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ።
38 በበሮቹ ጎንና ጎን ባሉት ዓምዶች አጠገብ የመመገቢያ ክፍል ነበር፤ መግቢያም ነበረው፤ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠለውን መባ የሚያጥቡት በዚያ ነበር።+
39 በበሩም በረንዳ ላይ በግራና በቀኝ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ፣+ የኃጢአት መባና+ የበደል መባ+ የሚታረድባቸው ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች ነበሩ።
40 ወደ ሰሜን በር በሚወስደው መንገድ ላይ ከመግቢያው ውጭ ሁለት ጠረጴዛዎች ነበሩ። በተጨማሪም ከበሩ በረንዳ በሌላኛው በኩል ሁለት ጠረጴዛዎች ነበሩ።
41 በበሩ ግራና ቀኝ አራት አራት ጠረጴዛዎች፣ በድምሩ መሥዋዕት የታረደባቸው ስምንት ጠረጴዛዎች ነበሩ።
42 ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ ለማቅረብ የሚያገለግሉት አራቱ ጠረጴዛዎች ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ ነበሩ። ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል፣ ወርዳቸው አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመታቸው ደግሞ አንድ ክንድ ነበር። በእነሱም ላይ የሚቃጠለውን መባና መሥዋዕቱን ለማረድ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ተቀምጠው ነበር።
43 ከውስጠኛው ግንብ ጋር ተያይዘው ዙሪያውን የተሠሩ መደርደሪያዎች የነበሩ ሲሆን ወርዳቸው አንድ ጋት ነበር፤ በጠረጴዛዎቹም ላይ የስጦታ መባው ሥጋ ይቀመጥ ነበር።
44 ከውስጠኛው በር ውጭ የዘማሪዎቹ መመገቢያ ክፍሎች ነበሩ፤+ ክፍሎቹ ከደቡብ ትይዩ ባለው የሰሜን በር አጠገብ በሚገኘው በውስጠኛው ግቢ ውስጥ ነበሩ። ከሰሜን ትይዩ ባለው የምሥራቅ በር አጠገብ ሌላ የመመገቢያ ክፍል ነበር።
45 እሱም እንዲህ አለኝ፦ “በደቡብ ትይዩ ያለው ይህ የመመገቢያ ክፍል የቤተ መቅደሱን አገልግሎት እንዲያከናውኑ ኃላፊነት ለተጣለባቸው ካህናት የተመደበ ነው።+
46 በሰሜን ትይዩ ያለው የመመገቢያ ክፍል ከመሠዊያው ጋር የተያያዘ አገልግሎት እንዲያከናውኑ ኃላፊነት ለተጣለባቸው ካህናት የተመደበ ነው።+ እነዚህ የሳዶቅ+ ልጆች ሲሆኑ ከሌዋውያን መካከል ይሖዋን ለማገልገል ወደ እሱ እንዲቀርቡ የተመደቡ ናቸው።”+
47 ከዚያም የውስጠኛውን ግቢ ለካ። ርዝመቱ 100 ክንድ፣ ወርዱም 100 ክንድ የሆነ አራት ማዕዘን ነበር። መሠዊያው ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ነበር።
48 ከዚያም ወደ ቤተ መቅደሱ በረንዳ+ አመጣኝ፤ በጎን በኩል ያለውንም የበረንዳውን ዓምድ ለካ፤ ዓምዱም በአንደኛው ጎን አምስት ክንድ፣ በሌላኛውም ጎን አምስት ክንድ ነበር። የበሩ ወርድ በአንደኛው ጎን ሦስት ክንድ፣ በሌላኛውም ጎን ሦስት ክንድ ነበር።
49 የበረንዳው ርዝመት 20 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 11* ክንድ ነበር። ሰዎች ወደዚያ የሚወጡት በደረጃዎች ነበር። በጎንና በጎን ባሉት ምሰሶዎች አጠገብ በግራና በቀኝ አንድ አንድ ዓምድ ነበር።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “በማሳይህም ነገር ሁሉ ላይ ልብህን አድርግ።”
^ ቃል በቃል “ስድስት ክንድ የሆነ የመለኪያ ሸምበቆ፣ አንድ ክንድ ከጋት።” ይህ ረጅም ክንድ የሚባለውን መለኪያ ያመለክታል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “ከቤቱ።” ከሕዝቅኤል ምዕራፍ 40 እስከ 48 ድረስ “ቤት” የሚለው ቃል የቤተ መቅደሱን ሕንፃዎች በአጠቃላይ ወይም ራሱን ቤተ መቅደሱን ለማመልከት በተሠራባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ “ቤተ መቅደስ” ተብሎ ተተርጉሟል።
^ የዘብ ጠባቂውን ክፍል ግድግዳ አናት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
^ ወይም “በአንድ በኩል ጠባብ (በሌላ በኩል ደግሞ ሰፊ) ክፍተት ያላቸው መስኮቶች።”
^ ወይም “በግቢውም ዙሪያ ክፍሎችና።”
^ ቃል በቃል “ወርድ።”
^ “ወርዱ ደግሞ 12” ሊሆንም ይችላል።