ዘሌዋውያን 24:1-23

  • ለማደሪያው ድንኳን መብራቶች የሚሆን ዘይት (1-4)

  • ገጸ ኅብስት (5-9)

  • የአምላክን ስም የሰደበው በድንጋይ ተወገረ (10-23)

24  ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2  “መብራቱ ያለማቋረጥ እንዲበራ ለማድረግ ለመብራቱ የሚሆን ተጨቅጭቆ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው።+ 3  ከምሽት አንስቶ እስከ ጠዋት ድረስ መብራቱ በይሖዋ ፊት ያለማቋረጥ እንዲበራ አሮን በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ካለው ከምሥክሩ መጋረጃ ውጭ ያስቀምጠው። በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላለማዊ ደንብ ነው። 4  ዘወትር በይሖዋ ፊት እንዲሆኑ መብራቶቹን ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው መቅረዝ+ ላይ በቦታ በቦታቸው ያስቀምጣቸው። 5  “አንተም የላመ ዱቄት ወስደህ የቀለበት ቅርጽ ያላቸው 12 ዳቦዎችን ጋግር። እያንዳንዱ ዳቦ ከሁለት አሥረኛ ኢፍ* ዱቄት የተዘጋጀ መሆን ይኖርበታል። 6  እነዚህንም በይሖዋ ፊት ባለው ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው ጠረጴዛ+ ላይ ስድስት ስድስት አድርገህ በማነባበር በሁለት ረድፍ ታስቀምጣቸዋለህ።+ 7  ተነባብሮ በተቀመጠው በእያንዳንዱ ረድፍ ላይም ንጹሕ ነጭ ዕጣን አድርግ፤ ይህም ለምግቡ መታሰቢያ እንዲሆን+ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ይሆናል። 8  እሱም በየሰንበቱ ዘወትር በይሖዋ ፊት ይደርድረው።+ ይህ በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ያለ ዘላቂ ቃል ኪዳን ነው። 9  ይህም የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ይሆናል፤+ ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች መካከል ለእሱ እጅግ ቅዱስ ነገር ስለሆነ ቅዱስ በሆነ ቦታ ይበሉታል፤+ ይህ ዘላቂ ሥርዓት ነው።” 10  በእስራኤላውያን መካከል በእናቱ እስራኤላዊ በአባቱ ግን ግብፃዊ የሆነ አንድ ሰው ነበር፤+ በሰፈሩም ውስጥ በእሱና በአንድ እስራኤላዊ መካከል ጠብ ተነሳ። 11  የእስራኤላዊቷም ልጅ የአምላክን ስም* መሳደብና መራገም ጀመረ።+ በመሆኑም ወደ ሙሴ አመጡት።+ የእናትየውም ስም ሸሎሚት ነበር፤ እሷም ከዳን ነገድ የሆነው የዲብራይ ልጅ ነበረች። 12  እነሱም የይሖዋ ውሳኔ ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ አደረጉት።+ 13  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 14  “የተራገመውን ሰው ከሰፈሩ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሰዎች ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ መላው ጉባኤም በድንጋይ ይውገረው።+ 15  ለእስራኤላውያንም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ማንኛውም ሰው አምላኩን ቢራገም ለሠራው ኃጢአት ይጠየቅበታል። 16  ስለሆነም የይሖዋን ስም የተሳደበው ሰው ይገደል።+ መላው ጉባኤም በድንጋይ ይውገረው። የባዕድ አገሩም ሰው የአምላክን ስም ከተሳደበ ልክ እንደ አገሩ ተወላጅ ይገደል። 17  “‘አንድ ሰው የሰው ሕይወት ካጠፋ* ይገደል።+ 18  የቤት እንስሳን የገደለ* ሰው፣ ሕይወት ስለ ሕይወት* ካሳ አድርጎ መክፈል ይኖርበታል። 19  አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ ጉዳት ቢያደርስ ልክ እሱ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በራሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።+ 20  ስብራት ስለ ስብራት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ ይሁን፤ በሰውየው ላይ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በእሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።+ 21  እንስሳን መትቶ የገደለ ስለ እንስሳው ካሳ መክፈል ይኖርበታል፤+ ሰውን መትቶ የገደለ ግን መገደል አለበት።+ 22  “‘ለባዕድ አገሩም ሰው ሆነ ለአገሬው ተወላጅ፣ ለሁላችሁም የሚሠራው አንድ ዓይነት ድንጋጌ ነው፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’” 23  ከዚያም ሙሴ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ እነሱም የተራገመውን ሰው ከሰፈሩ ውጭ አውጥተው በድንጋይ ወገሩት።+ በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሁለት አሥረኛ ኢፍ 4.4 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ዘሌ 24:15 እና 16 እንደሚጠቁሙት ይሖዋ የሚለውን ስም ያመለክታል።
ወይም “የማንኛውንም ሰው ነፍስ መትቶ ከገደለ።”
ወይም “የቤት እንስሳን ነፍስ መትቶ የገደለ።”
ወይም “ነፍስ ስለ ነፍስ።”