የሐዋርያት ሥራ 20:1-38

  • ጳውሎስ በመቄዶንያና በግሪክ (1-6)

  • በጥሮአስ የነበረው አውጤኪስ ከሞት ተነሳ (7-12)

  • ከጥሮአስ ወደ ሚሊጢን ተጓዙ (13-16)

  • ጳውሎስ ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ጋር ተገናኘ (17-38)

    • ከቤት ወደ ቤት ማስተማር (20)

    • “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” (35)

20  ሁከቱ ሲበርድ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስጠራቸው፤ ካበረታታቸውና ከተሰናበታቸው በኋላ ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ።  በሚያልፍባቸው ስፍራዎች የሚያገኛቸውን ደቀ መዛሙርት በብዙ ቃል እያበረታታ ወደ ግሪክ መጣ።  በዚያ ሦስት ወር ቆየ፤ ይሁንና ወደ ሶርያ በመርከብ ለመሄድ ተነስቶ ሳለ አይሁዳውያን ሴራ ስለጠነሰሱበት+ ሐሳቡን ቀይሮ በመቄዶንያ አድርጎ ለመመለስ ወሰነ።  የጳይሮስ ልጅ የቤርያው ሶጳጥሮስ፣ የተሰሎንቄዎቹ አርስጥሮኮስና+ ሲኮንዱስ፣ የደርቤው ጋይዮስ፣ ጢሞቴዎስ+ እንዲሁም ከእስያ አውራጃ የመጡት ቲኪቆስና+ ጢሮፊሞስ+ አብረውት ነበሩ።  እነዚህም ወደ ጥሮአስ ቀድመውን በመሄድ እዚያ ጠበቁን፤  እኛ ግን የቂጣ በዓል+ ካለፈ በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሳን፤ በአምስት ቀን ጊዜ ውስጥም እነሱ ወዳሉበት ወደ ጥሮአስ ደረስን፤ በዚያም ሰባት ቀን ቆየን።  በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ምግብ ልንበላ አንድ ላይ ተሰብስበን ሳለን ጳውሎስ በማግስቱ ይሄድ ስለነበር ንግግር ይሰጣቸው ጀመር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አስረዘመ።  በመሆኑም ተሰብስበንበት በነበረው ፎቅ ላይ ባለው ክፍል ውስጥ ብዙ መብራት ነበር።  ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ መስኮት ላይ ተቀምጦ የነበረ አውጤኪስ የሚባል አንድ ወጣት ከባድ እንቅልፍ ያዘው፤ እንቅልፍ ስለጣለውም ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ወደቀ፤ ሲያነሱትም ሞቶ ነበር። 10  ጳውሎስም ከፎቅ ላይ ወርዶ በላዩ ላይ ተኝቶ አቀፈውና+ “በሕይወት ስላለ አትንጫጩ”* አላቸው።+ 11  ከዚያም ወደ ፎቅ ወጥቶ ማዕዱን ካስጀመረ* በኋላ በላ። እስከ ንጋትም ድረስ ሲነጋገር ቆየ፤ በኋላም ተነስቶ ሄደ። 12  ሰዎቹም ወጣቱን ወሰዱት፤ ሕያው በመሆኑም እጅግ ተጽናኑ። 13  እኛም ጳውሎስ በሰጠን መመሪያ መሠረት በመርከብ ተሳፍረን በቅድሚያ ወደ አሶስ ተጓዝን፤ ምክንያቱም ጳውሎስ በእግሩ ተጉዞ በዚያ ለመሳፈር አስቦ ነበር። 14  ስለዚህ አሶስ ላይ ከተገናኘን በኋላ አሳፍረነው ወደ ሚጢሊኒ ሄድን። 15  በነጋታውም ጉዟችንን በመቀጠል ከኪዮስ ትይዩ ወዳለው ስፍራ ደረስን፤ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ሳሞስ ላይ አጭር ቆይታ አደረግን፤ በማግስቱም ሚሊጢን ደረስን። 16  ጳውሎስ በእስያ አውራጃ ምንም መቆየት ስላልፈለገ ኤፌሶንን+ አልፎ ለመሄድ ወሰነ፤ ምክንያቱም ቢችል በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ኢየሩሳሌም ለመድረስ ቸኩሎ ነበር።+ 17  ይሁን እንጂ ከሚሊጢን ወደ ኤፌሶን መልእክት ልኮ የጉባኤውን ሽማግሌዎች አስጠራ። 18  ወደ እሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “በእስያ አውራጃ እግሬ ከረገጠበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በመካከላችሁ እንዴት እንደተመላለስኩ ታውቃላችሁ፤+ 19  በአይሁዳውያን ሴራ ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስብኝም እንኳ በታላቅ ትሕትናና+ በእንባ ጌታን አገለግል ነበር፤ 20  ደግሞም የሚጠቅማችሁን ማንኛውንም ነገር ከመንገርም ሆነ በአደባባይና+ ከቤት ወደ ቤት+ ከማስተማር ወደኋላ ብዬ አላውቅም። 21  ከዚህ ይልቅ አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ንስሐ እንዲገቡና+ ወደ አምላክ እንዲመለሱ እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ በተሟላ ሁኔታ* መሥክሬላቸዋለሁ።+ 22  አሁን ደግሞ እዚያ ምን እንደሚደርስብኝ ባላውቅም መንፈስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው፤ 23  እርግጥ ነው፣ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ በደረስኩበት ከተማ ሁሉ በተደጋጋሚ ያሳስበኛል።+ 24  ይሁንና ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ+ እንዲሁም ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ በመመሥከር* ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ሕይወቴ* ምንም አያሳሳኝም።* 25  “አሁንም እነሆ፣ የአምላክን መንግሥት የሰበክሁላችሁ እናንተ ሁላችሁ ዳግመኛ ፊቴን እንደማታዩ አውቃለሁ። 26  ስለዚህ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ መሆኔን ለማሳየት በዚህች ቀን እናንተን ምሥክር አድርጌ መጥራት እችላለሁ፤+ 27  ምክንያቱም የአምላክን ፈቃድ* ሁሉ ለእናንተ ከመንገር ወደኋላ አላልኩም።+ 28  ለራሳችሁም ሆነ አምላክ በገዛ ልጁ ደም+ የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ እንድትጠብቁ+ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች+ አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ትኩረት ስጡ።+ 29  እኔ ከሄድኩ በኋላ ጨካኝ* ተኩላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡና+ መንጋውን በርኅራኄ እንደማይዙ አውቃለሁ፤ 30  ከእናንተ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።+ 31  “ስለዚህ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ+ ሌሊትና ቀን እያንዳንዳችሁን በእንባ ከማሳሰብ ወደኋላ እንዳላልኩ አስታውሱ። 32  አሁንም ለአምላክ እንዲሁም ሊያንጻችሁና በቅዱሳኑ ሁሉ መካከል ርስት ሊያወርሳችሁ ለሚችለው፣ ስለ እሱ ጸጋ ለሚገልጸው ቃል አደራ እሰጣችኋለሁ።+ 33  የማንንም ብር፣ ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም።+ 34  እነዚህ እጆቼ ለእኔም ሆነ ከእኔ ጋር ለነበሩት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት እንዳገለገሉ+ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 35  እናንተም እንዲሁ እየሠራችሁ ደካማ የሆኑትን መርዳት እንዳለባችሁ በሁሉም ነገር አሳይቻችኋለሁ፤+ እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’+ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል።” 36  ይህን ተናግሮ ከጨረሰም በኋላ ከሁሉም ጋር ተንበርክኮ ጸለየ። 37  ከዚያም ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም እቅፍ አድርገው* ሳሙት፤ 38  ከሁሉ ይበልጥ ያሳዘናቸው ከዚህ በኋላ ፊቱን እንደማያዩ የተናገረው ቃል ነው።+ ከዚያም እስከ መርከቡ ድረስ ሸኙት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍሱ በውስጡ ስላለች አትንጫጩ።”
ቃል በቃል “ዳቦውን ከቆረሰ።”
ወይም “በሚገባ።”
ወይም “ለእኔ አንዳች ዋጋ የለውም።”
ወይም “በሚገባ በመመሥከር።”
ወይም “ነፍሴ።”
ወይም “ዓላማ።”
ወይም “ጨቋኝ።”
ቃል በቃል “ጳውሎስ አንገት ላይ ወድቀውም።”