መሳፍንት 13:1-25

  • አንድ መልአክ ማኑሄንና ሚስቱን አነጋገራቸው (1-23)

  • ሳምሶን ተወለደ (24, 25)

13  እስራኤላውያን እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ ይሖዋም ለ40 ዓመት በፍልስጤማውያን እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።+  በዚህ ጊዜ ከዳናውያን+ ቤተሰብ የሆነ ስሙ ማኑሄ+ የሚባል አንድ የጾራ+ ሰው ነበር። ሚስቱ መሃን ስለነበረች ልጅ አልነበራትም።+  ከጊዜ በኋላ የይሖዋ መልአክ ለሴቲቱ ተገለጠላትና እንዲህ አላት፦ “እነሆ አንቺ መሃን ነሽ፤ ልጅም የለሽም። ነገር ግን ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።+  እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤+ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብዪ።+  እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ይህ ልጅ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ* የአምላክ ናዝራዊ* ስለሚሆን ራሱን ምላጭ አይንካው፤+ እሱም እስራኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ በማዳን ረገድ ግንባር ቀደም ይሆናል።”+  ከዚያም ሴቲቱ ሄዳ ባሏን እንዲህ አለችው፦ “የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እኔ መጥቶ ነበር፤ መልኩም የእውነተኛውን አምላክ መልአክ ይመስላል፤ በጣም የሚያስፈራ ነበር። ከየት እንደመጣ አልጠየቅኩትም፤ እሱም ቢሆን ስሙን አልነገረኝም።+  ሆኖም እንዲህ አለኝ፦ ‘እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። እንግዲህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብዪ፤ ምክንያቱም ልጁ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ* እስከሚሞትበት ዕለት ድረስ የአምላክ ናዝራዊ ይሆናል።’”  ማኑሄም “ይቅርታ አድርግልኝ ይሖዋ። እባክህ ልከኸው የነበረው ያ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንደገና ወደ እኛ ይምጣና የሚወለደውን ልጅ በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይስጠን” በማለት ይሖዋን ተማጸነ።  በመሆኑም እውነተኛው አምላክ የማኑሄን ቃል ሰማ፤ የእውነተኛው አምላክ መልአክም ሴቲቱ ሜዳ ላይ ተቀምጣ ሳለ ዳግመኛ ወደ እሷ መጣ፤ ባሏ ማኑሄ ግን አብሯት አልነበረም። 10  ሴቲቱም በፍጥነት እየሮጠች ሄዳ ባሏን “ባለፈው ጊዜ ወደ እኔ መጥቶ የነበረው ሰው ተገለጠልኝ” አለችው።+ 11  ከዚያም ማኑሄ ተነስቶ ከሚስቱ ጋር ሄደ። ሰውየውንም ሲያገኘው “ሚስቴን ያነጋገርካት አንተ ነህ?” አለው፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አለ። 12  ማኑሄም “እንግዲህ እንደ ቃልህ ይሁንልን! ይሁንና ልጁን ማሳደግ የሚኖርብን እንዴት ነው? የእሱስ ሥራ ምን ይሆናል?” አለው።+ 13  የይሖዋም መልአክ ማኑሄን እንዲህ አለው፦ “ሚስትህ ከነገርኳት ነገር ሁሉ ራሷን ትጠብቅ።+ 14  ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤+ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብላ።+ ያዘዝኳትን ሁሉ ትጠብቅ።” 15  ማኑሄም የይሖዋን መልአክ “እባክህ አንድ የፍየል ጠቦት አዘጋጅተን እስክናቀርብልህ ድረስ ቆይ” አለው።+ 16  ሆኖም የይሖዋ መልአክ ማኑሄን “ብቆይም እንኳ የምታቀርበውን ምግብ አልበላም፤ ይሁንና ለይሖዋ የሚቃጠል መባ ማቅረብ የምትፈልግ ከሆነ እሱን አቅርበው” አለው። ማኑሄ ይህ ሰው የይሖዋ መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። 17  ከዚያም ማኑሄ የይሖዋን መልአክ “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?”+ በማለት ጠየቀው። 18  ሆኖም የይሖዋ መልአክ “ስሜ የሚያስደንቅ ሆኖ ሳለ ለምን ስሜን ትጠይቀኛለህ?” አለው። 19  ከዚያም ማኑሄ የፍየል ጠቦቱንና የእህል መባውን ወስዶ በዓለቱ ላይ ለይሖዋ አቀረበው። እሱም ማኑሄና ሚስቱ እየተመለከቱ አስደናቂ ነገር አደረገ። 20  የእሳቱ ነበልባል ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ የይሖዋ መልአክ ማኑሄና ሚስቱ እያዩት ከመሠዊያው በወጣው ነበልባል ውስጥ ሆኖ አረገ። እነሱም ወዲያውኑ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። 21  የይሖዋም መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ አልተገለጠላቸውም። ማኑሄ ሰውየው የይሖዋ መልአክ እንደነበር የተገነዘበው ያን ጊዜ ነበር።+ 22  ከዚያም ማኑሄ ሚስቱን “ያየነው አምላክን ስለሆነ መሞታችን አይቀርም” አላት።+ 23  ሚስቱ ግን “ይሖዋ ሊገድለን ቢፈልግማ ኖሮ የሚቃጠል መባና የእህል መባ ከእጃችን ባልተቀበለ ነበር፤+ ደግሞም ይህን ሁሉ ነገር ባላሳየንና እንዲህ ያለውንም ነገር ባልነገረን ነበር” አለችው። 24  በኋላም ሴቲቱ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳምሶን+ አለችው፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ባረከው። 25  ከጊዜ በኋላም በጾራ እና በኤሽታዖል+ መካከል በምትገኘው በማሃነህዳን+ ሳለ የይሖዋ መንፈስ ይገፋፋው ጀመር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ከማህፀን ጀምሮ።”
“የተወሰነ ወይም የተለየ” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ከማህፀን ጀምሮ።”