መሳፍንት 5:1-31

  • የዲቦራና የባርቅ የድል መዝሙር (1-31)

    • ከዋክብት ከሲሳራ ጋር ተዋጉ (20)

    • የቂሾን ወንዝ ጠራርጎ ወሰዳቸው (21)

    • ይሖዋን የሚወዱ እንደ ፀሐይ ይሁኑ (31)

5  በዚያን ቀን ዲቦራ+ ከአቢኖዓም ልጅ ከባርቅ+ ጋር ሆና ይህን መዝሙር ዘመረች፦+  2  “በእስራኤል ስላለው የተለቀቀ ፀጉር፣*ሕዝቡም ፈቃደኛ ስለሆነ፣+ይሖዋን አወድሱ!  3  እናንተ ነገሥታት ስሙ! እናንተ ገዢዎች ጆሯችሁን ስጡ! ለይሖዋ እዘምራለሁ። ለእስራኤል አምላክ+ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ።+  4  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ከሴይር+ በወጣህ ጊዜ፣ከኤዶም ክልል እየገሰገስክ በመጣህ ጊዜ፣ምድር ተናወጠች፤ ሰማያትም ውኃ አወረዱ፤ደመናትም ውኃ አንዠቀዠቁ።  5  ተራሮች በይሖዋ ፊት ቀለጡ፣*+ሲናም ሳይቀር በእስራኤል አምላክ+ በይሖዋ ፊት ቀለጠ።+  6  በአናት ልጅ በሻምጋር+ ዘመን፣በኢያዔል+ ዘመን ጎዳናዎቹ ጭር ያሉ ነበሩ፤ተጓዦችም በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ይሄዱ ነበር።  7  እኔ ዲቦራ+ እስክነሳ ድረስ፣እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳ ድረስ፣+የመንደር ነዋሪዎች ከእስራኤል ደብዛቸው ጠፋ።  8  እነሱ አዳዲስ አማልክትን መረጡ፤+በበሮቹም ላይ ጦርነት ነበር።+ በ40,000 የእስራኤል ወንዶች መካከል፣አንድ ጋሻ ወይም አንድ ጦር ሊታይ አልቻለም።  9  ልቤ ከእስራኤል አዛዦች፣+ከሕዝቡ ጋር በፈቃደኝነት ከወጡት ጋር ነው።+ ይሖዋን አወድሱ! 10  እናንተ፣ ነጣ ባሉ ቡናማ አህዮች የምትጋልቡ፣እናንተ፣ ባማሩ ምንጣፎች ላይ የምትቀመጡ፣እናንተ፣ በመንገድ ላይ የምትሄዱ፣ይህን ልብ በሉ! 11  የውኃ ቀጂዎች ድምፅ በውኃ መቅጃው ስፍራ ተሰማ፤እነሱም በዚያ የይሖዋን የጽድቅ ሥራዎች፣በእስራኤል መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦቹን የጽድቅ ሥራዎች መተረክ ጀመሩ። የይሖዋም ሕዝቦች ወደ በሮቹ ወረዱ። 12  ዲቦራ+ ሆይ፣ ንቂ፣ ንቂ! ንቂ፣ ንቂ፣ መዝሙርም ዘምሪ!+ የአቢኖዓም ልጅ ባርቅ+ ሆይ፣ ተነስ! ምርኮኞችህን እየመራህ ሂድ! 13  የተረፉትም ሰዎች ወደ መኳንንቱ ወረዱ፤የይሖዋ ሕዝቦች ኃያላኑን ለመውጋት ወደ እኔ ወረዱ። 14   በሸለቆው* የነበሩ ሰዎች ምንጫቸው ኤፍሬም ነበር፤ቢንያም ሆይ፣ እነሱ በሕዝቦችህ መካከል እየተከተሉህ ነው። ከማኪር+ አዛዦች፣ከዛብሎንም የመልማዮችን በትር የያዙ* ሰዎች ወረዱ። 15  የይሳኮር መኳንንት ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤እንደ ይሳኮር ሁሉ ባርቅም+ ከእሷ ጋር ነበር። እሱም በእግር ወደ ሸለቋማው ሜዳ* ተላከ።+ የሮቤል ቡድኖች ልባቸው በእጅጉ አመንትቶ ነበር። 16  አንተ በመንታ ጭነት መካከል የተቀመጥከው ለምንድን ነው?ለመንጎቹ ዋሽንታቸውን ሲነፉ ለማዳመጥ ነው?+ የሮቤል ቡድኖች እንደሆነ ልባቸው በእጅጉ አመንትቷል። 17  ጊልያድ ከዮርዳኖስ ማዶ አርፎ ተቀምጧል፤+ዳን ከመርከቦች ጋር የተቀመጠው ለምንድን ነው?+ አሴር በባሕር ዳርቻ ላይ ሥራ ፈቶ ተቀምጧል፤በወደቦቹም ላይ ይኖራል።+ 18  ዛብሎን እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ* ሕዝብ ነበር፤ንፍታሌምም ቢሆን+ በገላጣ ኮረብቶች ላይ ነው።+ 19  ነገሥታት መጡ፤ ተዋጉም፤በዚያን ጊዜ የከነአን ነገሥታት፣+በመጊዶ+ ውኃዎች አጠገብ በታአናክ ተዋጉ። ምንም ብር ማርከው አልወሰዱም።+ 20  ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤በምሕዋራቸው ላይ ሆነው ከሲሳራ ጋር ተዋጉ። 21  የቂሾን ወንዝ፣ጥንታዊው ወንዝ፣ የቂሾን ወንዝ ጠራርጎ ወሰዳቸው።+ ነፍሴ* ሆይ፣ ብርቱዎቹን ረገጥሽ። 22  የፈረሶች ኮቴ ሲረግጥ የተሰማው ያን ጊዜ ነበር፣ድንጉላ ፈረሶቹ በኃይል ይጋልቡ ነበር።+ 23  የይሖዋ መልአክ እንዲህ አለ፦ ‘መሮዝን እርገሙ፤ነዋሪዎቿንም እርገሙ፣ይሖዋን ለመርዳት አልመጡምና፣ይሖዋን ለመርዳት ከኃያላኑ ጋር አልመጡም።’ 24  የቄናዊው የሄቤር+ ሚስት ኢያዔል+ከሴቶች ሁሉ እጅግ የተባረከች ነች፤ በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ነች። 25  ውኃ ጠየቀ፣ ወተት ሰጠችው። ለመኳንንት በሚቀርብበት ጎድጓዳ ሳህን እርጎ ሰጠችው።+ 26  እጇን ዘርግታ የድንኳን ካስማ አነሳች፣በቀኝ እጇም የሠራተኛ መዶሻ ያዘች። ሲሳራንም ቸነከረችው፣ ጭንቅላቱንም ፈረከሰችው፣ሰሪሳራውንም ተረከከችው፤ በሳችው።+ 27  እሱም በእግሮቿ መካከል ተደፋ፤ በወደቀበት በዚያው ቀረ፤በእግሮቿ መካከል ተደፋ፣ ወደቀ፤እዚያው በተደፋበት ተሸንፎ ቀረ። 28  አንዲት ሴት በመስኮት ተመለከተች፣የሲሳራ እናት በፍርግርጉ አጮልቃ ወደ ውጭ ተመለከተች፣‘የጦር ሠረገሎቹ ሳይመጡ ለምን ዘገዩ? የሠረገሎቹ ኮቴ ድምፅስ ምነው ይህን ያህል ዘገየ?’+ 29  ጥበበኛ የሆኑት የተከበሩ ወይዛዝርቷ ይመልሱላታል፤አዎ፣ እሷም ለራሷ እንዲህ ትላለች፣ 30  ‘ያገኙትን ምርኮ እየተከፋፈሉ መሆን አለበት፣ለእያንዳንዱ ተዋጊ አንድ ልጃገረድ* እንዲያውም ሁለት ልጃገረዶች፣*ለሲሳራም ከምርኮው ላይ ቀለም የተነከሩ ልብሶች፣ አዎ ቀለም የተነከሩ ልብሶች፣ምርኮውን ለማረኩት ሰዎች አንገት፣ቀለም የተነከረ ባለ ጥልፍ ልብስ፣ እንዲያውም ሁለት ባለ ጥልፍ ልብስ እየተሰጠ ነው።’ 31  ይሖዋ ሆይ፣ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፣+አንተን የሚወዱ ግን ደምቃ እንደምትወጣ ፀሐይ ይሁኑ።” ከዚያ በኋላ ምድሪቱ ለ40 ዓመት አረፈች።* +

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ፀጉራቸውን ስለለቀቁት ተዋጊዎች።”
“ተናወጡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“የጸሐፊ መሣሪያ የሚይዙ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”
ወይም “ረባዳማው ሜዳ።”
ወይም “ነፍሱን የሚንቅ።”
ቃል በቃል “ማህፀን።”
ቃል በቃል “ማህፀኖች።”
ወይም “ሰላም አገኘች።”