መሳፍንት 4:1-24

  • ከነአናዊው ንጉሥ ያቢን እስራኤላውያንን ጨቆናቸው (1-3)

  • ነቢዪቱ ዲቦራና መስፍኑ ባርቅ (4-16)

  • ኢያዔል የሠራዊት አለቃ የሆነውን ሲሳራን ገደለችው (17-24)

4  ሆኖም ኤሁድ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ።+ 2  በመሆኑም ይሖዋ በሃጾር ሆኖ ይገዛ ለነበረው ለከነአን ንጉሥ ለያቢን አሳልፎ ሸጣቸው።+ የሠራዊቱም አለቃ በሃሮሼትጎይም+ የሚኖረው ሲሳራ ነበር። 3  ያቢን* የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው 900 የጦር ሠረገሎች* + ስለነበሩትና ለ20 ዓመት ክፉኛ ስለጨቆናቸው+ እስራኤላውያን ወደ ይሖዋ ጮኹ።+ 4  በዚያን ጊዜ የላጲዶት ሚስት ነቢዪቱ ዲቦራ+ በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆና ታገለግል ነበር። 5  እሷም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ፣ በራማና+ በቤቴል+ መካከል ባለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ሥር ትቀመጥ ነበር፤ እስራኤላውያንም ለፍርድ ወደ እሷ ይወጡ ነበር። 6  እሷም የአቢኖዓምን ልጅ ባርቅን+ ከቃዴሽንፍታሌም+ አስጠርታ እንዲህ አለችው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ የለም? ‘ሂድና ወደ ታቦር ተራራ ዝመት፤* ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን 10,000 ወንዶችን ውሰድ። 7  እኔም የያቢን ሠራዊት አለቃ የሆነውን ሲሳራን ከጦር ሠረገሎቹና ከሠራዊቱ ጋር ወደ ቂሾን ጅረት* + ወደ አንተ አመጣዋለሁ፤ እሱንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ።’”+ 8  በዚህ ጊዜ ባርቅ “አብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ እሄዳለሁ፤ አብረሽኝ የማትሄጂ ከሆነ ግን አልሄድም” አላት። 9  እሷም እንዲህ አለችው፦ “በእርግጥ አብሬህ እሄዳለሁ። ይሁንና ይሖዋ ሲሳራን በሴት እጅ አሳልፎ ስለሚሰጠው የምታካሂደው ዘመቻ ለአንተ ክብር አያስገኝልህም።”+ ከዚያም ዲቦራ ተነስታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴሽ+ ሄደች። 10  ባርቅም ዛብሎንንና ንፍታሌምን+ ወደ ቃዴሽ ጠራቸው፤ 10,000 ሰዎችም የእሱን ዱካ ተከተሉ። ዲቦራም አብራው ወጣች። 11  እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቄናዊው+ ሄቤር፣ የሙሴ አማት+ የሆባብ ዘሮች ከሆኑት ከቄናውያን ተለይቶ በቃዴሽ በሚገኘው በጻናኒም ትልቅ ዛፍ አጠገብ ድንኳኑን ተክሎ ነበር። 12  ከዚያም የአቢኖዓም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ+ እንደወጣ ለሲሳራ ነገሩት። 13  ሲሳራም ወደ ቂሾን ጅረት* + ለመሄድ ወዲያውኑ የጦር ሠረገሎቹን በሙሉ ይኸውም የብረት ማጭድ የተገጠመላቸውን 900 የጦር ሠረገሎች* እንዲሁም ከእሱ ጋር የነበረውን ሠራዊት ሁሉ ከሃሮሼትጎይም አሰባሰበ። 14  በዚህ ጊዜ ዲቦራ ባርቅን እንዲህ አለችው፦ “ይሖዋ ሲሳራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ይህ ስለሆነ ተነስ! ይሖዋ በፊትህ ቀድሞ ይወጣ የለም?” ባርቅም 10,000 ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ። 15  ይሖዋም ሲሳራንና የጦር ሠረገሎቹን በሙሉ እንዲሁም ሠራዊቱን ሁሉ ግራ እንዲጋቡ አደረጋቸው፤+ በባርቅም ሰይፍ አጠፋቸው። በመጨረሻም ሲሳራ ከሠረገላው ላይ ወርዶ በእግሩ መሸሽ ጀመረ። 16  ባርቅም የጦር ሠረገሎቹንና ሠራዊቱን እስከ ሃሮሼትጎይም ድረስ አሳደዳቸው። በመሆኑም የሲሳራ ሠራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ አንድም የተረፈ ሰው አልነበረም።+ 17  ሆኖም ሲሳራ የቄናዊው የሄቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል+ ድንኳን በእግሩ ሸሸ፤ ምክንያቱም በሃጾር ንጉሥ በያቢንና+ በቄናዊው በሄቤር+ ቤት መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ነበር። 18  ኢያዔልም ሲሳራን ልትቀበለው ወጣች፤ ከዚያም “ጌታዬ ና፤ ወደዚህ ግባ። አትፍራ” አለችው። በመሆኑም ወደ እሷ ድንኳን ገባ። እሷም ብርድ ልብስ አለበሰችው። 19  ከዚያም “እባክሽ ስለጠማኝ የምጠጣው ትንሽ ውኃ ስጪኝ” አላት። እሷም የወተት አቁማዳውን ፈትታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤+ ከዚያም በድጋሚ ሸፈነችው። 20  እሱም “ድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ ‘እዚህ ሰው አለ?’ ብሎ ቢጠይቅሽ ‘የለም!’ በይ” አላት። 21  የሄቤር ሚስት ኢያዔል ግን የድንኳን ካስማና መዶሻ ወሰደች። ከዚያም ሲሳራ ደክሞት ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ በቀስታ ወደ እሱ ሄዳ ካስማውን ሰሪሳራዎቹ* ላይ በመቸንከር ከመሬት ጋር አጣበቀችው። እሱም ሞተ።+ 22  ባርቅ ሲሳራን እያሳደደ ወደዚያ አካባቢ ሄደ፤ ኢያዔልም እሱን ለማግኘት ወጣች፤ ከዚያም “ና፣ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው። እሱም ከእሷ ጋር ወደ ውስጥ ገባ፤ ሲሳራንም ካስማው ሰሪሳራዎቹ ላይ እንደተቸነከረ ሞቶ አገኘው። 23  በመሆኑም አምላክ በዚያን ዕለት የከነአን ንጉሥ ያቢን ለእስራኤላውያን እንዲንበረከክ አደረገ።+ 24  እስራኤላውያን የከነአንን+ ንጉሥ ያቢንን እስኪያጠፉት ድረስ እጃቸው በከነአን ንጉሥ በያቢን ላይ ይበልጥ እየበረታ ሄደ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “እሱም።”
ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”
ወይም “ሰዎችህን በታቦር ተራራ አሰማራ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”
በዓይንና በጆሮ መካከል ያለውን የአካል ክፍል ያመለክታል።