መሳፍንት 16:1-31

  • ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄደ (1-3)

  • ሳምሶንና ደሊላ (4-22)

  • የሳምሶን የበቀል እርምጃና ሞት (23-31)

16  አንድ ቀን ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄደ፤ በዚያም አንዲት ዝሙት አዳሪ አይቶ ወደ እሷ ገባ።  ከዚያም ጋዛውያን “ሳምሶን እዚህ መጥቷል” የሚል ወሬ ደረሳቸው። እነሱም ከበውት በከተማዋ በር ላይ ሌሊቱን ሙሉ አድፍጠው ሲጠባበቁ አደሩ። ለራሳቸውም “ጎህ ሲቀድ እንገድለዋለን” በማለት ሌሊቱን ሙሉ ድምፃቸውን አጥፍተው አደሩ።  ይሁንና ሳምሶን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ተኛ። ከዚያም እኩለ ሌሊት ላይ ተነስቶ የከተማዋን በሮች ያዘ፤ በሮቹን ከነመቃኖቹና ከነመቀርቀሪያዎቹ ነቀለ። በትከሻው ከተሸከማቸውም በኋላ በኬብሮን ትይዩ እስከሚገኘው ተራራ አናት ድረስ ይዟቸው ወጣ።  ከዚህ በኋላ ሳምሶን በሶረቅ ሸለቆ* የምትገኝ ደሊላ+ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ።  የፍልስጤም ገዢዎችም ወደ እሷ ቀርበው እንዲህ አሏት፦ “እስቲ አታለሽ* + እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥንካሬ የሰጠው ምን እንደሆነ እንዲሁም እንዴት ልናሸንፈው፣ ልናስረውና በቁጥጥር ሥር ልናውለው እንደምንችል ለማወቅ ሞክሪ። ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን 1,100 የብር ሰቅል እንሰጥሻለን።”  ከጊዜ በኋላም ደሊላ ሳምሶንን “የታላቅ ኃይልህ ሚስጥር ምን እንደሆነ እንዲሁም አንተን በምን ማሰርና በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደሚቻል እስቲ ንገረኝ” አለችው።  ሳምሶንም “ገና እርጥብ በሆኑ ባልደረቁ ሰባት ጅማቶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።  በመሆኑም የፍልስጤም ገዢዎች ገና እርጥብ የሆኑ ያልደረቁ ሰባት ጅማቶች አመጡላት፤ እሷም በጅማቶቹ አሰረችው።  እነሱም በውስጠኛው ክፍል ውስጥ አድፍጠው ይጠባበቁ ነበር፤ እሷም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች። በዚህ ጊዜ ሳምሶን የተፈተለ የበፍታ ክር* እሳት ሲነካው በቀላሉ እንደሚበጣጠስ ጅማቶቹን በጣጠሳቸው።+ የኃይሉም ሚስጥር ሊታወቅ አልቻለም። 10  ደሊላም ሳምሶንን “አሞኝተኸኛል፣ ደግሞም ዋሽተኸኛል።* እሺ አሁን በምን ልትታሰር እንደምትችል እባክህ ንገረኝ” አለችው። 11  እሱም “ሥራ ላይ ባልዋሉ አዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት። 12  ደሊላም አዲስ ገመዶች ወስዳ አሰረችው፤ ከዚያም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች። (በዚህ ጊዜ ሁሉ በውስጠኛው ክፍል ውስጥ አድፍጠው የሚጠባበቁ ሰዎች ነበሩ።) ሳምሶንም ገመዶቹን ልክ እንደ ክር ከእጆቹ ላይ በጣጠሳቸው።+ 13  ከዚህ በኋላ ደሊላ ሳምሶንን “አሁንም አሞኘኸኝ፤ ዋሸኸኝ።+ በምን ልትታሰር እንደምትችል ንገረኝ” አለችው። እሱም “የራስ ፀጉሬን ሰባት ጉንጉኖች በመሸመኛ ላይ ከድር ጋር አብረሽ ሸምኛቸው” አላት። 14  በመሆኑም ደሊላ ጉንጉኖቹን በሸማኔ ዘንግ አጠበቀቻቸው፤ ከዚያም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች። እሱም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ዘንጉንና ድሩንም መዞ አወጣው። 15  እሷም “ልብህ ከእኔ ጋር ሳይሆን እንዴት ‘እወድሻለሁ’+ ትለኛለህ? ይኸው ሦስት ጊዜ አሞኘኸኝ፤ የታላቁ ኃይልህን ሚስጥር አልነገርከኝም”+ አለችው። 16  ዕለት ዕለት ስለነዘነዘችውና ለጭንቀት ስለዳረገችው ሞቱን እስኪመኝ ድረስ ተመረረ።* + 17  በመጨረሻም የልቡን ሁሉ አውጥቶ እንዲህ ሲል ነገራት፦ “ከተወለድኩበት ጊዜ አንስቶ* ለአምላክ ናዝራዊ ስለሆንኩ ራሴን ምላጭ ነክቶት አያውቅም።+ ፀጉሬን ከተላጨሁ ኃይሌን አጣለሁ፤ አቅምም አይኖረኝም፤ እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እሆናለሁ።” 18  ደሊላም ሳምሶን የልቡን ሁሉ አውጥቶ እንደነገራት ስታውቅ “የልቡን ሁሉ አውጥቶ ስለነገረኝ በቃ አሁን መምጣት ትችላላችሁ” በማለት የፍልስጤም ገዢዎችን+ ወዲያውኑ አስጠራቻቸው። የፍልስጤም ገዢዎችም ገንዘቡን ይዘው ወደ እሷ መጡ። 19  እሷም ሳምሶንን ጭኗ ላይ አስተኛችው፤ ሰውየውንም ጠርታ የራስ ፀጉሩን ሰባት ጉንጉኖች እንዲላጫቸው አደረገች። ከዚያ በኋላ ኃይሉ ከእሱ ስለተለየ በቁጥጥሯ ሥር አዋለችው። 20  እሷም “ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!” አለችው። በዚህ ጊዜ ከእንቅልፉ ነቅቶ “እንደ ሌላው ጊዜ እወጣለሁ፤+ ራሴንም ነፃ አደርጋለሁ” አለ። ሆኖም ይሖዋ እንደተወው አላወቀም ነበር። 21  በመሆኑም ፍልስጤማውያን ይዘው ዓይኖቹን አወጡ። ከዚያም ወደ ጋዛ ይዘውት በመውረድ ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አሰሩት፤ እሱም እስር ቤት ውስጥ እህል ፈጪ ሆነ። 22  ሆኖም ተላጭቶ የነበረው የሳምሶን ፀጉር እንደገና ማደግ ጀመረ።+ 23  የፍልስጤም ገዢዎች “አምላካችን ጠላታችንን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን!” በማለት ለአምላካቸው ለዳጎን+ ታላቅ መሥዋዕት ለመሠዋትና ለመደሰት አንድ ላይ ተሰብስበው ነበር። 24  ሕዝቡም ሳምሶንን ባዩት ጊዜ “አምላካችን ምድራችንን ያጠፋውንና+ ብዙ ወገኖቻችንን የገደለብንን+ ጠላታችንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” በማለት አምላካቸውን አወደሱ። 25  እነሱም ልባቸው ሐሴት በማድረጉ “እስቲ ሳምሶንን ጥሩትና ትንሽ ያዝናናን” አሉ። በመሆኑም እንዲያዝናናቸው ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠሩት፤ በዓምዶቹም መካከል አቆሙት። 26  ከዚያም ሳምሶን እጁን ይዞት የነበረውን ልጅ “ቤቱ የቆመባቸውን ዓምዶች አስይዘኝና ልደገፍባቸው” አለው። 27  (እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቤቱ በወንዶችና በሴቶች ተሞልቶ ነበር። የፍልስጤም ገዢዎችም በሙሉ እዚያ ነበሩ፤ በተጨማሪም ሳምሶን ሕዝቡን ሲያዝናና ይመለከቱ የነበሩ 3,000 ወንዶችና ሴቶች ጣሪያው ላይ ነበሩ።) 28  ሳምሶንም+ እንዲህ በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፣ እባክህ ለአሁን ብቻ አንድ ጊዜ ብርታት ስጠኝና+ ከሁለቱ ዓይኖቼ+ ስለ አንዱ ፍልስጤማውያንን ልበቀላቸው።” 29  ከዚያም ሳምሶን ቤቱን ደግፈው ያቆሙትን መሃል ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ዓምዶች፣ አንዱን በቀኝ እጁ ሌላውን ደግሞ በግራ እጁ አቅፎ ተደገፈባቸው። 30  እሱም “ከፍልስጤማውያን ጋር ልሙት!”* ብሎ ጮኸ። ከዚያም ዓምዶቹን ባለ በሌለ ኃይሉ ገፋቸው፤ ቤቱም በገዢዎቹና በውስጡ በነበሩት ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀ።+ በመሆኑም ሳምሶን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው ሰዎች ይልቅ በሞተበት ጊዜ የገደላቸው ሰዎች በለጡ።+ 31  በኋላም ወንድሞቹና የአባቱ ቤተሰቦች በሙሉ ሊወስዱት ወደዚያ ወረዱ። እነሱም ወስደው በጾራ+ እና በኤሽታዖል መካከል በሚገኘው በአባቱ በማኑሄ+ የመቃብር ስፍራ ቀበሩት። እሱም በእስራኤል ውስጥ ለ20 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “አግባቢው።”
ወይም “ገመድ።”
ወይም “ተጫውተህብኛል።”
ወይም “ነፍሱ ተመረረች።”
ቃል በቃል “ከእናቴ ማህፀን ጀምሮ።”
ወይም “ነፍሴ ከፍልስጤማውያን ጋር ትሙት።”