የሉቃስ ወንጌል 12:1-59

  • ‘የፈሪሳውያን እርሾ’ (1-3)

  • ሰውን ሳይሆን አምላክን ፍሩ (4-7)

  • ስለ ክርስቶስ መመሥከር (8-12)

  • ስለ ሞኙ ሀብታም ሰው የሚገልጽ ምሳሌ (13-21)

  • አትጨነቁ (22-34)

    • “ትንሽ መንጋ” (32)

  • ነቅቶ መጠበቅ (35-40)

  • ታማኝ መጋቢና ታማኝ ያልሆነ መጋቢ (41-48)

  • “የመጣሁት ሰላም ለማስፈን ሳይሆን ለመከፋፈል ነው” (49-53)

  • ዘመኑን መርምሮ መረዳት አስፈላጊ ነው (54-56)

  • ቅራኔን መፍታት (57-59)

12  በዚያን ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ እርስ በርስ እየተጋፋ እስኪረጋገጥ ድረስ ተሰብስቦ ሳለ ኢየሱስ በቅድሚያ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ከፈሪሳውያን እርሾ ይኸውም ከግብዝነት ተጠንቀቁ።+  ይሁንና የተሰወረ መገለጡ፣ ሚስጥር የሆነም መታወቁ አይቀርም።+  ስለዚህ በጨለማ የምትናገሩት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በጓዳ የምታንሾካሹኩት በሰገነት ላይ ይሰበካል።  በተጨማሪም ወዳጆቼ+ ሆይ፣ እላችኋለሁ፣ ሥጋን የሚገድሉትን ከዚያ በላይ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ።+  ይልቁንስ ማንን መፍራት እንደሚገባችሁ አሳያችኋለሁ፦ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም* የመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ።+ አዎ፣ እላችኋለሁ እሱን ፍሩ።+  አምስት ድንቢጦች አነስተኛ ዋጋ ባላቸው ሁለት ሳንቲሞች* ይሸጡ የለም? ሆኖም አንዷም እንኳ በአምላክ ዘንድ አትረሳም።*+  የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል።+ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።+  “እላችኋለሁ፣ በሰዎች ፊት የሚመሠክርልኝን+ ሁሉ የሰው ልጅም በአምላክ መላእክት ፊት ይመሠክርለታል።+  በሰዎች ፊት የሚክደኝ ሁሉ ግን በአምላክ መላእክት ፊት ይካዳል።+ 10  በሰው ልጅ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ሁሉ ይቅር ይባልለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ሁሉ ግን ይቅር አይባልም።+ 11  በሕዝባዊ ሸንጎዎች* እንዲሁም በመንግሥት ሹማምንትና ባለሥልጣናት ፊት ሲያቀርቧችሁ እንዴት ብለን ወይም ምን ብለን የመከላከያ መልስ እንሰጣለን ወይም ደግሞ ምን እንላለን ብላችሁ አትጨነቁ፤+ 12  ምን መናገር እንዳለባችሁ መንፈስ ቅዱስ በዚያኑ ሰዓት ያስተምራችኋልና።”+ 13  ከዚያም ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው “መምህር፣ ወንድሜ ውርሳችንን እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው። 14  ኢየሱስም “አንተ ሰው፣ በእናንተ መካከል ፈራጅና ዳኛ እንድሆን ማን ሾመኝ?” አለው። 15  ከዚያም “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም፤+ ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም* ሁሉ ተጠበቁ”+ አላቸው። 16  ይህን ካለ በኋላ እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሀብታም ሰው መሬቱ ብዙ ምርት አስገኘለት። 17  በመሆኑም ‘ምርቴን የማከማችበት ቦታ ስለሌለኝ ምን ባደርግ ይሻላል?’ ብሎ በልቡ ማሰብ ጀመረ። 18  ከዚያም እንዲህ አለ፦ ‘እንዲህ አደርጋለሁ፦+ ያሉኝን ጎተራዎች አፈርስና ትላልቅ ጎተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም እህሌንና ንብረቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ 19  ነፍሴንም* “ነፍሴ* ሆይ፣ ለብዙ ዘመን የሚበቃ የተከማቸ ሀብት አለሽ፤ እንግዲህ ዘና በይ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’ 20  አምላክ ግን ‘አንተ ማስተዋል የጎደለህ፣ በዚህች ሌሊት ሕይወትህን* ይፈልጓታል። ታዲያ ያከማቸኸው ነገር ለማን ይሆናል?’ አለው።+ 21  ለራሱ ሀብት የሚያከማች በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”+ 22  ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ* ምን እንበላለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ።*+ 23  ሕይወት* ከምግብ ሰውነትም ከልብስ የላቀ ዋጋ አለውና። 24  ቁራዎችን ተመልከቱ፦ አይዘሩም፣ አያጭዱም እንዲሁም የእህል ማከማቻ ወይም ጎተራ የላቸውም፤ ሆኖም አምላክ ይመግባቸዋል።+ ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ የላቀ ዋጋ የላችሁም?+ 25  ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ* መጨመር የሚችል ይኖራል? 26  ታዲያ እንዲህ ያለውን ትንሽ ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ ስለ ሌሎች ነገሮች ለምን ትጨነቃላችሁ?+ 27  እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፦ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም።+ 28  አምላክ ዛሬ ያለውንና ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን በሜዳ ያለ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ! 29  ስለዚህ ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ነገር ከልክ በላይ አታስቡ፤ እንዲሁም አትጨነቁ፤*+ 30  እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዓለም ያሉ ሰዎች አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው፤ ይሁንና አባታችሁ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።+ 31  ይልቁንስ ዘወትር መንግሥቱን ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ይሰጧችኋል።+ 32  “አንተ ትንሽ መንጋ+ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥት ሊሰጣችሁ ወስኗልና።+ 33  ያላችሁን ንብረት ሸጣችሁ ምጽዋት* ስጡ።+ የማያረጁ የገንዘብ ኮሮጆዎች አዘጋጁ፤ አዎ፣ ሌባ በማይደርስበት፣ ብልም ሊበላው በማይችልበት በሰማያት ለራሳችሁ የማያልቅ ውድ ሀብት አከማቹ።+ 34  ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናልና። 35  “ወገባችሁን ታጠቁ፤*+ መብራታችሁንም አብሩ፤+ 36  ጌታቸው ከሠርግ+ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁና+ መጥቶ በሩን ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት እንደተዘጋጁ ዓይነት ሰዎች ሁኑ። 37  ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው ሲጠባበቁ የሚያገኛቸው ባሪያዎች ደስተኞች ናቸው! እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታቸው ለሥራ ካሸረጠና* በማዕድ እንዲቀመጡ ካደረገ በኋላ ቆሞ ያስተናግዳቸዋል። 38  በሁለተኛው ክፍለ ሌሊትም* ይምጣ በሦስተኛው፣* ዝግጁ ሆነው ሲጠብቁ ካገኛቸው ደስተኞች ናቸው! 39  ነገር ግን ይህን እወቁ፤ አንድ ሰው ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር።+ 40  እናንተም የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ።”+ 41  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ይህን ምሳሌ እየተናገርክ ያለኸው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም?” አለው። 42  ጌታም እንዲህ አለ፦ “ጌታው ምንጊዜም የሚያስፈልጋቸውን ምግብ በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው በአገልጋዮቹ* ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም* መጋቢ* በእርግጥ ማን ነው?+ 43  ጌታው ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው! 44  እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 45  ነገር ግን ያ ባሪያ በልቡ ‘ጌታዬ የሚመጣው ዘግይቶ ነው’ ብሎ ቢያስብና ወንድና ሴት አገልጋዮችን መደብደብ እንዲሁም መብላት፣ መጠጣትና መስከር ቢጀምር+ 46  የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ይመጣል፤ ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል፤* ዕጣውንም ታማኝ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ያደርገዋል። 47  ደግሞም የጌታውን ፈቃድ እያወቀ ተዘጋጅቶ ያልጠበቀው ወይም ጌታው የጠየቀውን ነገር ያላደረገው * ያ ባሪያ ብዙ ግርፋት ይገረፋል።+ 48  ነገር ግን ሳያውቅ፣ ግርፋት የሚገባው ድርጊት የፈጸመ ጥቂት ይገረፋል። በእርግጥም ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይጠበቅበታል፤ ብዙ ኃላፊነት የተሰጠውም ብዙ ይጠበቅበታል።+ 49  “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኮስ ነው፤ ታዲያ እሳቱ ከተቀጣጠለ ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ? 50  እርግጥ እኔ የምጠመቀው አንድ ጥምቀት አለኝ፤ ይህ እስኪጠናቀቅ ድረስ በጣም ተጨንቄአለሁ!+ 51  የመጣሁት በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን ይመስላችኋል? በፍጹም አይደለም፤ እላችኋለሁ፣ የመጣሁት ሰላም ለማስፈን ሳይሆን ለመከፋፈል ነው።+ 52  ከአሁን ጀምሮ በአንድ ቤት ውስጥ እርስ በርስ የተከፋፈሉ አምስት ሰዎች ይኖራሉ፤ ሦስቱ በሁለቱ ላይ ሁለቱ ደግሞ በሦስቱ ላይ ይነሳሉ። 53   አባት በልጁ፣ ልጅ በአባቱ፣ እናት በልጇ፣ ልጅ በእናቷ፣ አማት በምራቷ፣ ምራት በአማቷ ላይ በመነሳት እርስ በርስ ይከፋፈላሉ።”+ 54  ከዚያም ለሕዝቡ ደግሞ እንዲህ አለ፦ “ከምዕራብ በኩል ደመና ሲመጣ ስታዩ ወዲያውኑ ‘ዶፍ ዝናብ ሊጥል ነው’ ትላላችሁ፤ እንዳላችሁትም ይሆናል። 55  የደቡብ ነፋስ ሲነፍስ ስታዩ ደግሞ ‘ኃይለኛ ሙቀት ይሆናል’ ትላላችሁ፤ በእርግጥም ይሆናል። 56  እናንተ ግብዞች፣ የምድሩንና የሰማዩን መልክ አይታችሁ መረዳት ትችላላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መርምራችሁ መረዳት እንዴት ተሳናችሁ?+ 57   ደግሞስ ጽድቅ የሆነውን ነገር ለራሳችሁ ለምን አትፈርዱም? 58  ለምሳሌ ከከሳሽህ ጋር ወደ አንድ ባለሥልጣን እየሄድክ ሳለ፣ ከእሱ ጋር ያለህን ቅራኔ እዚያው በመንገድ ላይ ለመፍታት ጥረት አድርግ፤ አለዚያ ዳኛ ፊት ያቀርብሃል፤ ዳኛውም ለፍርድ ቤቱ መኮንን አሳልፎ ይሰጥሃል፤ መኮንኑ ደግሞ እስር ቤት ያስገባሃል።+ 59  እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ትንሽ ሳንቲም* ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከዚያ ፈጽሞ አትወጣም።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በሁለት አሳሪዮን።” ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ችላ አትባልም።”
“በምኩራቦች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከመጎምጀትም።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ነፍሳችሁ።”
ወይም “መጨነቃችሁን ተዉ።”
ወይም “ነፍስ።”
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ከልክ በላይ ማሰብ አቁሙ፤ መጨነቃችሁንም ተዉ።”
ቃል በቃል “የምሕረት ስጦታ።” ወይም “ለድሆች ስጦታ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ይህ አባባል ለሥራ መዘጋጀትን ያመለክታል።
ወይም “ከታጠቀና።”
ሦስተኛው ክፍለ ሌሊት፣ ከእኩለ ሌሊት እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ ድረስ ነው።
ሁለተኛው ክፍለ ሌሊት፣ ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ነው።
ወይም “በቤቱ ሠራተኞች።”
ወይም “ጥበበኛ።”
ወይም “የቤት አስተዳዳሪ።”
ወይም “ለሁለት ይቆርጠዋል።”
ወይም “ከጌታው ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነገር ያላደረገው።”
ቃል በቃል “የመጨረሻዋን ሌፕተን።” ለ14ን ተመልከት።