የማቴዎስ ወንጌል 17:1-27

  • ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ተለወጠ (1-13)

  • “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት” (14-21)

  • ኢየሱስ እንደሚሞት በድጋሚ ተናገረ (22, 23)

  • ከዓሣ አፍ በተገኘው ሳንቲም ግብር ተከፈለ (24-27)

17  ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ።+  በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።*+  ከዚያም ሙሴና ኤልያስ ከእሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ከፈለግክ በዚህ ስፍራ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እተክላለሁ” አለው።  ገና እየተናገረ ሳለም ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ ተሰማ።  ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በፍርሃት ተውጠው በግንባራቸው ተደፉ።  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ወደ እነሱ ቀርቦ ዳሰሳቸውና “ተነሱ። አትፍሩ” አላቸው።  ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ሌላ ማንንም አላዩም።  ከተራራው እየወረዱ ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ ራእዩን ለማንም እንዳትናገሩ” ሲል አዘዛቸው።+ 10  ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ “ታዲያ ጸሐፍት ኤልያስ በመጀመሪያ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 11  እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ኤልያስ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመልሳል።+ 12  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ኤልያስ መምጣቱን መጥቷል፤ እነሱ ግን የፈለጉትን ነገር አደረጉበት+ እንጂ አላወቁትም። የሰው ልጅም እንደዚሁ በእነሱ እጅ ይሠቃያል።”+ 13  በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሆነ ገባቸው። 14  ወደ ሕዝቡ በመጡ ጊዜ+ አንድ ሰው ወደ እሱ ቀረበና ተንበርክኮ እንዲህ አለው፦ 15  “ጌታ ሆይ፣ ለልጄ ምሕረት አድርግለት፤ የሚጥል በሽታ ስላለበት በጠና ታሟል። አንዴ እሳት ውስጥ አንዴ ደግሞ ውኃ ውስጥ ይወድቃል።+ 16  ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ እነሱ ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” 17  ኢየሱስም መልሶ “እምነት የለሽና ጠማማ ትውልድ ሆይ፣+ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አለ። 18  ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ።+ 19  ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ መጥተው “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” አሉት። 20  እሱም “እምነታችሁ ስላነሰ ነው። እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም”+ አላቸው። 21  *—— 22  በገሊላ ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤+ 23  እነሱም ይገድሉታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።”+ ደቀ መዛሙርቱም በጣም አዘኑ። 24  ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ የቤተ መቅደሱን ግብር* የሚሰበስቡት ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀርበው “መምህራችሁ የቤተ መቅደሱን ግብር አይከፍልም?”+ አሉት። 25  እሱም “ይከፍላል” አላቸው። ይሁን እንጂ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ኢየሱስ በቅድሚያ እንዲህ አለው፦ “ስምዖን ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥ ወይም ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ወይስ ከሌሎች?” 26  እሱም “ከሌሎች” ብሎ ሲመልስለት ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “እንግዲያው ልጆቹ ግብር ከመክፈል ነፃ ናቸው። 27  ሆኖም እንቅፋት እንዳንሆንባቸው+ ወደ ባሕሩ ሄደህ መንጠቆ ጣል፤ ከዚያም መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት አንድ የብር ሳንቲም * ታገኛለህ። ሳንቲሙን ወስደህ ለእኔና ለአንተ ክፈል።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነጭ ሆነ።”
ቃል በቃል “ሁለት ድራክማ።” ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ስታቴር ሳንቲም።” ቴትራድራክማ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። ለ14ን ተመልከት።