ዘዳግም 27:1-26
27 ከዚያም ሙሴ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “እኔ ዛሬ የምሰጣችሁን ትእዛዛት በሙሉ ጠብቁ።
2 አምላካችሁ ይሖዋ ወደሚሰጣችሁ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ቀን ትላልቅ ድንጋዮችን አቁማችሁ ለስኗቸው።*+
3 ከዚያም የአባቶችህ አምላክ ይሖዋ ቃል በገባልህ መሠረት አምላክህ ይሖዋ ወደሚሰጥህ ምድር ይኸውም ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ ለመግባት በምትሻገርበት ጊዜ የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ ጻፍባቸው።
4 ዮርዳኖስን ስትሻገሩ ዛሬ በሰጠኋችሁ ትእዛዝ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በኤባል ተራራ+ ላይ አቁሟቸው፤ ደግሞም ለስኗቸው።*
5 በዚያም ለአምላክህ ለይሖዋ መሠዊያ ይኸውም የድንጋይ መሠዊያ ሥራ። ድንጋዮቹንም የብረት መሣሪያ አታስነካቸው።+
6 የአምላክህን የይሖዋን መሠዊያ ካልተጠረበ ድንጋይ ሥራ፤ በላዩም ላይ ለአምላክህ ለይሖዋ የሚቃጠሉ መባዎችን አቅርብ።
7 የኅብረት መሥዋዕቶችንም አቅርብ፤+ መሥዋዕቶቹንም እዚያው ብላቸው፤+ አንተም በአምላክህ በይሖዋ ፊት ደስ ይልሃል።+
8 በድንጋዮቹም ላይ የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ በግልጽ ጻፍባቸው።”+
9 ከዚያም ሙሴና ሌዋውያኑ ካህናት እስራኤላውያንን በሙሉ እንዲህ አሏቸው፦ “እስራኤል ሆይ፣ ጸጥ ብለህ አዳምጥ። በዛሬው ቀን አንተ የአምላክህ የይሖዋ ሕዝብ ሆነሃል።+
10 የአምላክህን የይሖዋን ቃል ስማ፤ እኔ ዛሬ የማዝህን የእሱን ትእዛዛትና ሥርዓቶች ፈጽም።”+
11 ሙሴም በዚያ ቀን ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፦
12 “ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ጊዜ በገሪዛን ተራራ+ ላይ ቆመው ሕዝቡን የሚባርኩት ነገዶች ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍ እና ቢንያም ናቸው።
13 እርግማኑን ለማሰማት በኤባል ተራራ+ ላይ የሚቆሙት ደግሞ ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳን እና ንፍታሌም ናቸው።
14 ሌዋውያኑም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ለእያንዳንዱ እስራኤላዊ እንዲህ ብለው ይናገራሉ፦+
15 “‘ይሖዋ የሚጠላውን አስጸያፊ ነገር+ ይኸውም የአንድ የእጅ ጥበብ ባለሙያ* የእጅ ሥራ ውጤት የሆነውን የተቀረጸ ምስል+ ወይም ከብረት የተሠራ ሐውልት*+ የሚሠራና በስውር የሚያስቀምጥ ሰው የተረገመ ይሁን።’ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’* ብሎ ይመልሳል።)
16 “‘አባቱን ወይም እናቱን የሚንቅ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
17 “‘የጎረቤቱን የወሰን ምልክት የሚገፋ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
18 “‘ዓይነ ስውሩን መንገድ የሚያሳስት የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
19 “‘የባዕድ አገሩን ሰው፣ አባት የሌለውን* ልጅ ወይም የመበለቲቱን ፍርድ የሚያዛባ+ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
20 “‘ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ አባቱን ስላዋረደ* የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
21 “‘ከማንኛውም ዓይነት እንስሳ ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
22 “‘የአባቱ ልጅ ወይም የእናቱ ልጅ ከሆነችው ከእህቱ ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
23 “‘ከሚስቱ እናት ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
24 “‘ጎረቤቱን አድብቶ በመጠበቅ የሚገድል የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
25 “‘ንጹሑን ሰው* ለመግደል ሲል ጉቦ የሚቀበል የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
26 “‘የዚህን ሕግ ቃል ተግባራዊ በማድረግ የማይጠብቅ ሰው የተረገመ ይሁን።’+ (ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይላል።)
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ኖራ ቀቧቸው።”
^ ወይም “ኖራ ቀቧቸው።”
^ ወይም “ይሁን!”
^ ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”
^ ወይም “የእንጨትና የብረት ሠራተኛ።”
^ ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን።”
^ ቃል በቃል “የአባቱን ቀሚስ ስለገለጠ።”
^ ወይም “የንጹሑን ደም ነፍስ።”