የማርቆስ ወንጌል 9:1-50

  • ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ተለወጠ (1-13)

  • ጋኔን ያደረበት ልጅ ተፈወሰ (14-29)

    • “እምነት ላለው ሰው፣ ሁሉ ነገር ይቻላል” (23)

  • ኢየሱስ እንደሚሞት በድጋሚ ተናገረ (30-32)

  • ደቀ መዛሙርቱ ማን ታላቅ እንደሚሆን ተከራከሩ (33-37)

  • “እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነው” (38-41)

  • ማሰናከያ (42-48)

  • “በሕይወታችሁ ውስጥ ጨው ይኑራችሁ” (49, 50)

9  ቀጥሎም “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የአምላክ መንግሥት በታላቅ ኃይል መምጣቱን እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም” አላቸው።+  ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤+  ልብሱ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ልብስ አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው ከሚችለው በላይ እጅግ ነጭ ሆኖ ያንጸባርቅ ጀመር።  ደግሞም ኤልያስና ሙሴ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር እየተነጋገሩ ነበር።  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ረቢ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው።  እርግጥ፣ በጣም ስለፈሩ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀም ነበር።  ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ መጣ።+  ከዚያም ድንገት ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም።  ከተራራው እየወረዱ ሳሉ የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ+ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ በጥብቅ አዘዛቸው።+ 10  እነሱም ቃሉን በልባቸው አኖሩ፤* ነገር ግን ከሞት መነሳት ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። 11  ከዚያም “ጸሐፍት፣ ኤልያስ+ በመጀመሪያ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 12  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “በእርግጥ ኤልያስ መጀመሪያ መጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመልሳል፤+ ይሁንና የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና+ መናቅ+ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? 13  ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ኤልያስ+ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት በእርግጥ መጥቷል፤ እነሱም የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል።”+ 14  ወደቀሩት ደቀ መዛሙርት በመጡም ጊዜ ብዙ ሕዝብ ከቧቸው አዩ፤ ጸሐፍትም ከእነሱ ጋር እየተከራከሩ ነበር።+ 15  ሆኖም የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን እንዳዩት በጣም ተገረሙ፤ ከዚያም ሰላም ሊሉት ወደ እሱ ሮጡ። 16  እሱም “ከእነሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጉዳይ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። 17  ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “መምህር፣ ልጄ ዱዳ የሚያደርግ መንፈስ ስላደረበት ወደ አንተ አመጣሁት።+ 18  በያዘው ስፍራ ሁሉ መሬት ላይ ይጥለዋል፤ ከዚያም አፉ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱን ያፋጫል እንዲሁም ይዝለፈለፋል። ደቀ መዛሙርትህ እንዲያስወጡት ጠየቅኳቸው፤ እነሱ ግን ሊያስወጡት አልቻሉም።” 19  እሱም መልሶ “እምነት የለሽ ትውልድ ሆይ፣+ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።+ 20  ልጁንም ወደ እሱ አመጡት፤ ልጁን የያዘው መንፈስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ወዲያውኑ ልጁን አንዘፈዘፈው። ልጁም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ አፉ አረፋ እየደፈቀ ይንከባለል ጀመር። 21  ከዚያም ኢየሱስ አባትየውን “እንዲህ ማድረግ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ሆነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለው፦ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22  ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥና ውኃ ውስጥ ይጥለዋል። ማድረግ የምትችለው ነገር ካለ እዘንልንና እርዳን።” 23  ኢየሱስም “‘የምትችለው ነገር ካለ’ አልክ? እምነት ላለው ሰው፣ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለው።+ 24  ወዲያውም የልጁ አባት “እምነት አለኝ! እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!”+ በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ። 25  ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እነሱ ግር ብሎ እየሮጠ በመምጣት ላይ መሆኑን ሲያይ ርኩሱን መንፈስ “አንተ ዱዳና ደንቆሮ የምታደርግ መንፈስ ከእሱ ውጣ፤ ዳግመኛም ወደ እሱ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ሲል ገሠጸው።+ 26  ርኩሱ መንፈስ በኃይል ከጮኸና ብዙ ካንዘፈዘፈው በኋላ ወጣ፤ ልጁም የሞተ ያህል ሆነ፤ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “ሞቷል!” ይሉ ጀመር። 27  ይሁን እንጂ ኢየሱስ እጁን ይዞ አስነሳው፤ ልጁም ተነስቶ ቆመ። 28  ከዚያም ወደ ቤት ከገባ በኋላ ብቻውን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 29  እሱም “እንዲህ ዓይነቱ በጸሎት ካልሆነ በቀር ሊወጣ አይችልም” አላቸው። 30  ከዚያ ተነስተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ሆኖም ይህን ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም። 31  ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱን እያስተማራቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነሱም ይገድሉታል፤+ ይሁንና ቢገደልም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል”+ በማለት እየነገራቸው ነበር። 32  ይሁን እንጂ የተናገረው ነገር አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። 33  ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ወደ ቤት ከገባም በኋላ “በመንገድ ላይ ስትከራከሩ የነበረው ስለ ምን ጉዳይ ነው?”+ ሲል ጠየቃቸው። 34  በመንገድ ላይ እርስ በርስ የተከራከሩት “ከሁላችን የሚበልጠው ማን ነው?” በሚል ስለነበረ ዝም አሉ። 35  ስለዚህ ከተቀመጠ በኋላ አሥራ ሁለቱን ጠርቶ “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉም መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት” አላቸው።+ 36  ከዚያም አንድ ትንሽ ልጅ አምጥቶ በመካከላቸው አቆመ፤ አቅፎትም እንዲህ አላቸው፦ 37  “እንዲህ ካሉት ልጆች+ አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ እኔን ብቻ ሳይሆን የላከኝንም ይቀበላል።”+ 38  ዮሐንስ እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያስወጣ አየን፤ ሆኖም እኛን ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን።”+ 39  ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “በስሜ ተአምር ሠርቶ ወዲያውኑ ስለ እኔ ክፉ ነገር ሊናገር የሚችል ስለሌለ አትከልክሉት። 40  እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና።+ 41  ደግሞም የክርስቶስ በመሆናችሁ ምክንያት አንድ ጽዋ የሚጠጣ ውኃ የሚሰጣችሁ ሁሉ፣+ እውነት እላችኋለሁ፣ በምንም መንገድ ብድራቱን አያጣም።+ 42  ሆኖም ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ* በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።+ 43  “እጅህ ቢያሰናክልህ ቁረጠው። ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ሊጠፋ ወደማይችልበት ወደ ገሃነም* ከምትሄድ ጉንድሽ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።+ 44  *—— 45  እግርህም ቢያሰናክልህ ቁረጠው። ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም* ከምትጣል አንካሳ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።+ 46  *—— 47  ዓይንህም ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።+ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነም* ከምትጣል አንድ ዓይን ኖሮህ ወደ አምላክ መንግሥት ብትገባ ይሻልሃል፤+ 48  በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱም አይጠፋም።+ 49  “ሰው ጨው እንደሚነሰንስ ሁሉ እንዲህ ዓይነት ሰዎችም እሳት ሊወርድባቸው ይገባል።+ 50  ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን በምን መመለስ ትችላላችሁ?+ በሕይወታችሁ ውስጥ ጨው ይኑራችሁ፤+ እርስ በርሳችሁም ሰላም ይኑራችሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ጉዳዩን በውስጣቸው ያዙት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በአህያ የሚዞር የወፍጮ ድንጋይ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።