ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 17:1-18

  • ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ የተላለፈ ፍርድ” (1-18)

    • ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠችው ታላቂቱ አመንዝራ (1-3)

    • ‘አውሬው ከዚህ በፊት ነበር፤ አሁን ግን የለም፤ ከጥልቁም ይወጣል’ (8)

    • አሥሩ ቀንዶች ከበጉ ጋር ይዋጋሉ (12-14)

    • አሥሩ ቀንዶች አመንዝራዋን ይጠሏታል (16, 17)

17  ሰባቱን ሳህኖች ይዘው ከነበሩት ሰባት መላእክት+ አንዱ መጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “ና፣ በብዙ ውኃዎች ላይ በምትቀመጠው በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የተበየነውን ፍርድ አሳይሃለሁ፤+  የምድር ነገሥታት ከእሷ ጋር አመነዘሩ፤*+ የምድር ነዋሪዎች ደግሞ በዝሙቷ* ወይን ጠጅ ሰከሩ።”+  እሱም በመንፈስ ኃይል ወደ ምድረ በዳ ወሰደኝ። በዚያም አንዲት ሴት አምላክን የሚሰድቡ ስሞች በሞሉበት እንዲሁም ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ባሉት ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ አየሁ።  ሴቲቱ ሐምራዊና+ ደማቅ ቀይ ልብስ ለብሳ እንዲሁም በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች አጊጣ ነበር፤+ በእጇም አስጸያፊ ነገሮችና የዝሙቷ* ርኩሰት የሞላበት የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር።  በግንባሯ ላይ “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና+ የምድር አስጸያፊ ነገሮች እናት”+ የሚል ሚስጥራዊ ስም ተጽፎ ነበር።  እኔም ሴቲቱ በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምሥክሮች ደም ሰክራ አየኋት።+ ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅኩ።  መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “የተደነቅከው ለምንድን ነው? የሴቲቱን+ እንዲሁም እሷ የተቀመጠችበትን ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት አውሬ+ ሚስጥር እነግርሃለሁ፦  ያየኸው አውሬ ከዚህ በፊት ነበር፤ አሁን ግን የለም፤ ይሁንና በቅርቡ ከጥልቁ+ ይወጣል፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ አንስቶ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል+ ላይ ያልተጻፈው የምድር ነዋሪዎች አውሬው ከዚህ በፊት እንደነበረ፣ አሁን ግን እንደሌለና ወደፊት እንደሚኖር ሲያዩ በአድናቆት ይዋጣሉ።  “ይህ ነገር ጥበብ ያለው አእምሮ* ይጠይቃል፦ ሰባቱ ራሶች+ ሴቲቱ የተቀመጠችባቸውን ሰባት ተራሮች ያመለክታሉ። 10  ደግሞም ሰባት ነገሥታት ናቸው፦ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም፤ በሚመጣበት ጊዜ ግን ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። 11  ከዚህ በፊት የነበረው፣ አሁን ግን የሌለው አውሬም+ ስምንተኛ ንጉሥ ነው፤ የሚወጣው ግን ከሰባቱ ነው፤ እሱም ወደ ጥፋት ይሄዳል። 12  “ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አሥር ነገሥታትን ያመለክታሉ፤ ይሁንና ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ። 13  እነዚህ አንድ ዓይነት ሐሳብ አላቸው፤ በመሆኑም ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ይሰጣሉ። 14  እነዚህ ከበጉ+ ጋር ይዋጋሉ፤ ሆኖም በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ+ ስለሆነ ድል ይነሳቸዋል።+ ከእሱ ጋር ያሉት የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ድል ያደርጋሉ።”+ 15  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “አመንዝራዋ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውኃዎች ወገኖችን፣ ብዙ ሕዝብን፣ ብሔራትንና ቋንቋዎችን ያመለክታሉ።+ 16  ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶችና+ አውሬውም+ አመንዝራዋን+ ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።+ 17  አምላክ ቃሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ+ አዎ፣ መንግሥታቸውን ለአውሬው+ በመስጠት አንድ የሆነውን የራሳቸውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ ይህን በልባቸው አኑሯልና። 18  ያየሃትም ሴት+ በምድር ነገሥታት ላይ መንግሥት ያላትን ታላቂቱን ከተማ ታመለክታለች።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “የማሰብ ችሎታ።”