ዘኁልቁ 31:1-54

  • በምድያም ላይ የተወሰደ የበቀል እርምጃ (1-12)

    • በለዓም ተገደለ (8)

  • የጦር ምርኮን በተመለከተ የተሰጠ መመሪያ (13-54)

31  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “ለእስራኤላውያን ምድያማውያንን+ ተበቀልላቸው።+ ከዚያ በኋላ ወደ ወገኖችህ ትሰበሰባለህ።”*+  በመሆኑም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ በምድያም ላይ የሚወስደውን የበቀል እርምጃ ለማስፈጸም ከምድያም ጋር ለሚደረገው ጦርነት* ከመካከላችሁ ወንዶችን አስታጥቁ።  ከሁሉም የእስራኤል ነገድ ከእያንዳንዱ 1,000 ወንዶችን ወደ ጦርነቱ ላኩ።”  ስለዚህ በሺዎች ከሚቆጠሩት እስራኤላውያን+ መካከል ከአንድ ነገድ 1,000 ወንዶች ተመርጠው በአጠቃላይ 12,000 ወንዶች ለጦርነቱ* ታጠቁ።  ከዚያም ሙሴ ከየነገዱ የተውጣጡትን አንድ አንድ ሺህ ወንዶች ወደ ጦርነቱ ላካቸው፤ ከእነሱም ጋር የሠራዊቱ ካህን የሆነውን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሃስን+ ላከው፤ ቅዱስ የሆኑት ዕቃዎችና በጦርነት ጊዜ የሚነፉት መለከቶች+ በእሱ እጅ ነበሩ።  እነሱም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በምድያም ላይ ጦርነት ከፈቱ፤ ወንዶቹንም ሁሉ ገደሉ።  ከተገደሉትም መካከል ኤዊ፣ ራቄም፣ ጹር፣ ሁር እና ረባ የተባሉት አምስቱ የምድያም ነገሥታት ይገኙበታል። እንዲሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን+ በሰይፍ ገደሉ።  ሆኖም እስራኤላውያን የምድያምን ሴቶችና ትናንሽ ልጆች ማርከው ወሰዱ። በተጨማሪም የቤት እንስሶቻቸውን፣ ከብቶቻቸውን እንዲሁም ንብረታቸውን በሙሉ ዘረፉ። 10  ይኖሩባቸው የነበሩትን ከተሞችና ሰፈሮቻቸውን* ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። 11  ሰውም ሆነ እንስሳ የማረኩትንና የዘረፉትን በሙሉ ወሰዱ። 12  ከዚያም የማረኳቸውን ሰዎችና የዘረፉትን ንብረት በኢያሪኮ፣ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ+ ላይ ወደሚገኘው ሰፈር ወደ ሙሴ፣ ወደ ካህኑ አልዓዛርና ወደ እስራኤል ማኅበረሰብ አመጡ። 13  ከዚያም ሙሴ፣ ካህኑ አልዓዛርና የማኅበረሰቡ አለቆች በሙሉ ከእነሱ ጋር ለመገናኘት ከሰፈሩ ውጭ ወጡ። 14  ሆኖም ሙሴ ከጦርነቱ በተመለሱት የሠራዊቱ አዛዦች ይኸውም በሺህ አለቆቹና በመቶ አለቆቹ ላይ ተቆጣ። 15  እንዲህም አላቸው፦ “ሴቶቹን በሙሉ እንዴት ሳትገድሉ ተዋችኋቸው? 16  የበለዓምን ቃል ሰምተው እስራኤላውያን በፌጎር በተከሰተው ነገር+ የተነሳ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ያሳቷቸውና+ በዚህም ምክንያት በይሖዋ ማኅበረሰብ ላይ መቅሰፍት እንዲመጣ ያደረጉት እነሱ አይደሉም?+ 17  በሉ አሁን ከልጆች መካከል ወንዶቹን በሙሉ እንዲሁም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ ሴቶችን በሙሉ ግደሉ። 18  ሆኖም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁትን ወጣት ሴቶች ሁሉ+ በሕይወት እንዲተርፉ ልታደርጉ ትችላላችሁ። 19  እናንተም ለሰባት ቀን ከሰፈሩ ውጭ ቆዩ። ከመካከላችሁ ሰው* የገደለም ሆነ የሞተ ሰው የነካ+ ማንኛውም ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሱን ያንጻ፤+ እናንተም ሆናችሁ የማረካችኋቸው ሰዎች ራሳችሁን አንጹ። 20  ማንኛውንም ልብስ፣ ማንኛውንም ከቆዳ የተሠራ ነገር፣ ማንኛውንም ከፍየል ፀጉር የተሠራ ነገር እንዲሁም ማንኛውንም ከእንጨት የተሠራ ነገር ከኃጢአት አንጹ።” 21  ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ወደ ጦርነቱ ሄደው የነበሩትን ወንዶች እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ደንብ ይህ ነው፦ 22  ‘ወርቁን፣ ብሩን፣ መዳቡን፣ ብረቱን፣ ቆርቆሮውንና እርሳሱን ብቻ 23  ይኸውም እሳትን መቋቋም የሚችለውን ማንኛውንም ነገር በእሳት ውስጥ እንዲያልፍ አድርጉ፤ እሱም ንጹሕ ይሆናል። ያም ሆኖ ለማንጻት በሚያገለግለው ውኃ መንጻት አለበት።+ እሳትን መቋቋም የማይችሉ ነገሮችን በሙሉ በውኃ ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ አለባችሁ። 24  በሰባተኛውም ቀን ልብሶቻችሁን እጠቡ፤ ንጹሕም ሁኑ፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ መግባት ትችላላችሁ።’”+ 25  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 26  “የምርኮውን ብዛት ቁጠር፤ ሰዎችም ሆኑ እንስሳት የተማረኩትን ሁሉ ቁጠር፤ ይህንም ከካህኑ ከአልዓዛርና ከማኅበረሰቡ የአባቶች ቤት መሪዎች ጋር አድርግ። 27  ምርኮውንም በጦርነቱ ለተካፈሉት ተዋጊዎችና ለቀረው ማኅበረሰብ ሁሉ እንዲከፋፈል ለሁለት ክፈለው።+ 28  ለይሖዋም ግብር እንዲሆን በጦርነቱ ከተካፈሉት ተዋጊዎች ላይ ከሰውም ሆነ ከከብት፣ ከአህያም ሆነ ከመንጋ ከ500 አንድ ነፍስ* ውሰድ። 29  ለእነሱ ተከፍሎ ከተሰጣቸው ድርሻ ላይ ወስዳችሁ ለካህኑ ለአልዓዛር የይሖዋ መዋጮ አድርጋችሁ ስጡት።+ 30  ለእስራኤላውያን ተከፍሎ ከተሰጣቸው ድርሻ ላይ ደግሞ ከሰውም ሆነ ከከብት፣ ከአህያም ሆነ ከመንጋ እንዲሁም ከማንኛውም እንስሳ ከ50 አንድ ወስደህ ከይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ኃላፊነት+ ለሚወጡት ለሌዋውያኑ ስጥ።”+ 31  በመሆኑም ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 32  በውጊያው የተካፈሉት ሰዎች ማርከው ካመጡት ምርኮ ውስጥ የቀሩት 675,000 በጎች፣ 33  72,000 ከብቶች 34  እንዲሁም 61,000 አህዮች ነበሩ። 35  ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁት ሴቶች*+ በአጠቃላይ 32,000 ነበሩ። 36  በውጊያው ለተሳተፉት ተከፍሎ የተሰጣቸው ድርሻ በአጠቃላይ 337,500 በግ ነበር። 37  ከበጎቹ መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 675 ነበሩ። 38  ከብቶቹ ደግሞ 36,000 ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 72 ነበሩ። 39  አህዮቹ 30,500 ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 61 ነበሩ። 40  ሰዎቹ* ደግሞ 16,000 ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 32 ሰዎች* ነበሩ። 41  ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ግብሩን ለይሖዋ መዋጮ እንዲሆን ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው።+ 42  ሙሴም በጦርነቱ የተካፈሉት ሰዎች ካመጡት ላይ ከፍሎ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ድርሻ ይህ ነው፦ 43  ሙሴ ከፍሎ የሰጣቸው ድርሻ 337,500 በግ፣ 44  36,000 ከብት፣ 45  30,500 አህያ 46  እንዲሁም 16,000 ሰው* ነበር። 47  ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ለእስራኤላውያን ተከፍሎ ከተሰጣቸው ድርሻ ላይ ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ከ50 አንድ ወስዶ በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን የተጣለባቸውን ኃላፊነት+ ለሚወጡት ሌዋውያን ሰጠ።+ 48  ከዚያም በሠራዊቱ ክፍሎች ውስጥ የተሾሙት አዛዦች ይኸውም የሺህ አለቆቹና+ የመቶ አለቆቹ ወደ ሙሴ ቀርበው 49  እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ በሥራችን ያሉትን ተዋጊዎች ቆጥረናል፤ ከመካከላችን አንድም የጎደለ የለም።+ 50  ስለዚህ እያንዳንዳችን በይሖዋ ፊት ለራሳችን* ማስተሰረያ እንዲሆኑልን፣ ያገኘናቸውን ነገሮች ይኸውም የወርቅ ጌጣጌጦችን፣ የእግር አልቦዎችን፣ የእጅ አምባሮችን፣ የማኅተም ቀለበቶችን፣ የጆሮ ጉትቻዎችንና ሌሎች ጌጣጌጦችን ለይሖዋ መባ አድርገን ማቅረብ እንፈልጋለን።” 51  በመሆኑም ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ይኸውም ጌጣጌጡን ሁሉ ተቀበሏቸው። 52  ከሺህ አለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው ለይሖዋ መዋጮ እንዲሆን የሰጡት ወርቅ በጠቅላላ 16,750 ሰቅል* ሆነ። 53   በሠራዊቱ ውስጥ ያሉት ወንዶች እያንዳንዳቸው ከምርኮው ላይ ድርሻቸውን ወስደው ነበር። 54  ስለዚህ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሺህ አለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው በይሖዋ ፊት ለእስራኤል ሕዝብ ማስታወሻ* እንዲሆን ወደ መገናኛ ድንኳኑ አስገቡት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
ወይም “ለሚገጥመው ሠራዊት።”
ወይም “ለሠራዊቱ።”
ወይም “በግንብ የታጠሩ ሰፈሮቻቸውን።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍሳት።”
ወይም “ነፍሳት።”
ወይም “ነፍሳቱ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ለነፍሳችን።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “መታሰቢያ።”