ምሳሌ 9:1-18

  • እውነተኛ ጥበብ ትጣራለች (1-12)

    • “በእኔ ምክንያት ዘመንህ ይረዝማል” (11)

  • ማስተዋል የጎደላት ሴት ትጣራለች (13-18)

    • “የተሰረቀ ውኃ ይጣፍጣል” (17)

9  እውነተኛ ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ሰባቱን ምሰሶዎቿንም ጠርባ አዘጋጀች።   ሥጋዋን በሚገባ አዘጋጀች፤*የወይን ጠጇንም ደባለቀች፤ደግሞም ገበታዋን አሰናዳች።   ከከተማዋ በላይ ባሉ ከፍታ ቦታዎች ላይ ሆነውእንዲህ ብለው እንዲጣሩ ሴት አገልጋዮቿን ላከች፦+   “ተሞክሮ የሌለው ሁሉ ወደዚህ ይምጣ።” ማስተዋል* ለጎደለው እንዲህ ትላለች፦   “ኑ፣ ያዘጋጀሁትን ምግብ ብሉ፤የደባለቅኩትንም የወይን ጠጅ ጠጡ።   አላዋቂነታችሁን ተዉ፤* በሕይወትም ኑሩ፤+በማስተዋል መንገድ ወደ ፊት ሂዱ።”+   ፌዘኛን የሚያርም በራሱ ላይ ውርደት ያመጣል፤+ክፉን ሰው የሚወቅስም ሁሉ ጉዳት ይደርስበታል።   ፌዘኛን አትውቀስ፤ አለዚያ ይጠላሃል።+ ጥበበኛን ሰው ውቀሰው፤ እሱም ይወድሃል።+   ጥበበኛን ሰው አስተምረው፤ ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል።+ ጻድቅን ሰው አስተምረው፤ ተጨማሪ እውቀት ያገኛል። 10  የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው፤+እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ማወቅም+ ማስተዋል ነው። 11  በእኔ ምክንያት ዘመንህ ይረዝማል፤+በሕይወትህም ላይ ዕድሜ ይጨመርልሃል። 12  ጥበበኛ ብትሆን፣ ጥበበኛነትህ የሚጠቅመው ራስህን ነው፤ፌዘኛ ብትሆን ግን መዘዙን የምትቀበለው አንተው ነህ። 13  ማስተዋል የጎደላት ሴት ጯኺ ናት።+ እሷ ጨርሶ ማመዛዘን አትችልም፤ ደግሞም አንዳች ነገር አታውቅም። 14  በከተማዋ ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ፣በቤቷ ደጃፍ ወንበር ላይ ትቀመጣለች፤+ 15  በጎዳናው የሚያልፉትን፣ቀጥ ብለው በመንገዳቸው የሚሄዱትን ትጣራለች፦ 16  “ተሞክሮ የሌለው ሁሉ ወደዚህ ይምጣ።” ማስተዋል* ለጎደላቸው ሁሉ እንዲህ ትላለች፦+ 17  “የተሰረቀ ውኃ ይጣፍጣል፤ተደብቀው የበሉት ምግብም ይጥማል።”+ 18  እሱ ግን በሞት የተረቱት በዚያ እንዳሉ፣እንግዶቿም በመቃብር* ጥልቅ ውስጥ እንደሚገኙ አያውቅም።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “እርዷን አረደች።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “ተሞክሮ ከሌላቸው ሰዎች ራቁ።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።