ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 9:1-21

  • አምስተኛው መለከት (1-11)

  • አንደኛው ወዮታ አልፏል፤ ሁለት ወዮታዎች ይመጣሉ (12)

  • ስድስተኛው መለከት (13-21)

9  አምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ።+ እኔም ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀ አንድ ኮከብ አየሁ፤ ለእሱም የጥልቁ መግቢያ ቁልፍ+ ተሰጠው።  የጥልቁንም መግቢያ ከፈተው፤ በመግቢያውም በኩል ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጭስ ያለ ጭስ ወጣ፤ ከዚያ በወጣው ጭስም ፀሐይ ጨለመች፤+ አየሩም ጠቆረ።  ከጭሱም አንበጦች ወጥተው ወደ ምድር ወረዱ፤+ እነሱም በምድር ላይ ያሉ ጊንጦች ያላቸው ዓይነት ሥልጣን ተሰጣቸው።  የአምላክ ማኅተም በግንባራቸው ላይ የሌላቸውን ሰዎች ብቻ እንጂ ማንኛውንም የምድር ተክል ወይም ማንኛውንም ዕፀዋት ወይም ማንኛውንም ዛፍ እንዳይጎዱ ተነገራቸው።+  አንበጦቹም ሰዎቹን እንዲገድሏቸው ሳይሆን ለአምስት ወር እንዲያሠቃዩአቸው ተፈቀደላቸው፤ በእነሱም ላይ የሚደርሰው ሥቃይ ጊንጥ+ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዓይነት ሥቃይ ነው።  በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይሻሉ፤ ሆኖም ፈጽሞ አያገኙትም፤ ለመሞት ይመኛሉ፤ ሞት ግን ከእነሱ ይሸሻል።  የአንበጦቹም ገጽታ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶች ይመስል ነበር፤+ በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊሎች የሚመስሉ ነገሮች ነበሩ፤ ፊታቸው ደግሞ የሰው ፊት ይመስል ነበር፤  ፀጉራቸው የሴት ፀጉር ይመስል ነበር። ጥርሳቸው ግን የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር፤+  የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩርም ነበራቸው። የክንፎቻቸው ድምፅም ወደ ጦርነት የሚገሰግሱ በፈረስ የሚጎተቱ ሠረገላዎች ድምፅ ይመስል ነበር።+ 10  በተጨማሪም የጊንጥ ዓይነት ተናዳፊ ጅራት አላቸው፤ ደግሞም ሰዎቹን ለአምስት ወር የሚጎዱበት ሥልጣን በጅራታቸው ላይ ነበር።+ 11  በእነሱ ላይ የተሾመ ንጉሥ አላቸው፤ እሱም የጥልቁ መልአክ ነው።+ በዕብራይስጥ ስሙ አባዶን* ሲሆን በግሪክኛ ደግሞ ስሙ አጶልዮን* ነው። 12  አንዱ ወዮታ አልፏል። እነሆ፣ ከዚህ በኋላ ሌሎች ሁለት ወዮታዎች+ ይመጣሉ። 13  ስድስተኛው መልአክ+ መለከቱን ነፋ።+ ደግሞም በአምላክ ፊት ካለው የወርቅ መሠዊያ+ ቀንዶች የወጣ አንድ ድምፅ ሰማሁ፤ 14  ድምፁም መለከት የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ “በታላቁ ወንዝ፣ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው” አለው።+ 15  ለዚህ ሰዓት፣ ቀን፣ ወርና ዓመት ተዘጋጅተው የነበሩት አራቱ መላእክትም ከሰዎቹ አንድ ሦስተኛውን እንዲገድሉ ተፈቱ። 16  የፈረሰኞቹ ሠራዊት ብዛት ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ* ነበር፤ ቁጥራቸውንም ሰማሁ። 17  በራእዩ ላይ ያየኋቸው ፈረሶችና በላያቸው የተቀመጡት ይህን ይመስሉ ነበር፦ እንደ እሳት ቀይ፣ እንደ ያክንት ሰማያዊና እንደ ድኝ ቢጫ የሆነ ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበር፤+ ከአፋቸውም እሳት፣ ጭስና ድኝ ወጣ። 18  ከአፋቸው በወጡት በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች ይኸውም በእሳቱ፣ በጭሱና በድኙ ከሰዎቹ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ተገደሉ። 19  የፈረሶቹ ሥልጣን ያለው በአፋቸውና በጅራታቸው ላይ ነውና፤ ጅራታቸው እባብ የሚመስል ሲሆን ራስም አለው፤ ጉዳት የሚያደርሱትም በዚህ ነው። 20  ሆኖም በእነዚህ መቅሰፍቶች ያልተገደሉት የቀሩት ሰዎች ከእጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤ ደግሞም አጋንንትን እንዲሁም ማየት፣ መስማትም ሆነ መሄድ የማይችሉትን ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ፣ ከድንጋይና ከእንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለካቸውን አልተዉም።+ 21  እንዲሁም ከፈጸሙት የነፍስ ግድያ፣ ከመናፍስታዊ ድርጊቶቻቸው፣ ከፆታ ብልግናቸውም* ሆነ ከሌብነታቸው ንስሐ አልገቡም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ጥፋት” የሚል ትርጉም አለው።
“አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “20,000 ጊዜ 10,000” ማለትም 200,000,000።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።