ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 5:1-14

  • በሰባት ማኅተሞች የታሸገ ጥቅልል (1-5)

  • በጉ ጥቅልሉን ወሰደ (6-8)

  • በጉ ማኅተሙን ለመክፈት ብቁ ሆኖ ተገኘ (9-14)

5  እኔም በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው+ በሁለቱም በኩል* የተጻፈበትና በሰባት ማኅተሞች በደንብ የታሸገ ጥቅልል በቀኝ እጁ ይዞ ተመለከትኩ።  አንድ ብርቱ መልአክም በታላቅ ድምፅ “ማኅተሞቹን ሊያነሳና ጥቅልሉን ሊከፍት የሚገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ አየሁ።  ሆኖም በሰማይም ሆነ በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ጥቅልሉን ሊከፍትም ሆነ ውስጡን ሊመለከት የሚችል ማንም አልነበረም።  ጥቅልሉን ሊከፍትም ሆነ ውስጡን ሊመለከት የሚገባው ማንም ባለመገኘቱ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ።  ሆኖም ከሽማግሌዎቹ አንዱ “አታልቅስ። እነሆ፣ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣+ የዳዊት+ ሥር+ ድል ስላደረገ+ ሰባቱን ማኅተሞችና ጥቅልሉን ሊከፍት ይችላል” አለኝ።  በዙፋኑ መካከል፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከልና በሽማግሌዎቹ+ መካከል የታረደ+ የሚመስል በግ+ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች አሉት፤ ዓይኖቹም ወደ መላው ምድር የተላኩትን ሰባቱን የአምላክ መናፍስት+ ያመለክታሉ።  እሱም ወዲያውኑ ወደ ፊት ቀርቦ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ቀኝ እጅ ጥቅልሉን ወሰደ።  ጥቅልሉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና 24ቱ ሽማግሌዎች+ በበጉ ፊት ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም በገናና ዕጣን የተሞሉ የወርቅ ሳህኖች ነበሯቸው። (ዕጣኑ የቅዱሳኑን ጸሎት ያመለክታል።)+  እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፦+ “ጥቅልሉን ልትወስድና ማኅተሞቹን ልትከፍት ይገባሃል፤ ታርደሃልና፤ በደምህም ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ+ ሰዎችን ለአምላክ ዋጅተሃል፤+ 10  እንዲሁም ለአምላካችን መንግሥትና+ ካህናት እንዲሆኑ አድርገሃቸዋል፤+ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።”+ 11  እኔም አየሁ፤ ደግሞም በዙፋኑ፣ በሕያዋን ፍጥረታቱና በሽማግሌዎቹ ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና* ሺዎች ጊዜ ሺዎች ነበር፤+ 12  እነሱም በታላቅ ድምፅ “ታርዶ የነበረው በግ+ ኃይል፣ ብልጽግና፣ ጥበብ፣ ብርታት፣ ክብር፣ ግርማና በረከት ሊቀበል ይገባዋል” አሉ።+ 13  እንዲሁም በሰማይ፣ በምድር፣ ከምድር በታችና+ በባሕር ያለ ፍጡር ሁሉ፣ አዎ በውስጣቸው ያሉ ነገሮች ሁሉ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና+ ለበጉ+ በረከት፣ ክብር፣+ ግርማና ኃይል ለዘላለም ይሁን” ብለው ሲናገሩ ሰማሁ።+ 14  አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት “አሜን!” ይሉ ነበር፤ ሽማግሌዎቹም ተደፍተው ሰገዱ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በውስጥም በውጭም በኩል።”
ወይም “አሥር ሺዎች ጊዜ አሥር ሺዎችና።”