ዘሌዋውያን 19:1-37
19 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
2 “ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።+
3 “‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤*+ ሰንበቶቼንም ይጠብቅ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
4 ከንቱ ወደሆኑ አማልክት ዞር አትበሉ፤+ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክትን አትሥሩ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
5 “‘ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕት የምታቀርቡ+ ከሆነ ተቀባይነት በሚያስገኝላችሁ መንገድ አቅርቡት።+
6 መሥዋዕቱም በዚያው ባቀረባችሁበት ዕለትና በቀጣዩ ቀን መበላት ይኖርበታል፤ ተርፎ እስከ ሦስተኛው ቀን የቆየ ካለ ግን በእሳት መቃጠል አለበት።+
7 ይሁንና ከተረፈው ላይ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የሌለው አስጸያፊ ነገር ይሆናል።
8 የበላውም ሰው የይሖዋን ቅዱስ ነገር ስላረከሰ በጥፋቱ ይጠየቃል፤ ያም ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።
9 “‘የምድራችሁን አዝመራ በምትሰበስቡበት ጊዜ በእርሻችሁ ዳር ዳር ያለውን ሙልጭ አድርጋችሁ አትጨዱት፤ የእርሻችሁን ቃርሚያም አትልቀሙ።+
10 በተጨማሪም በወይን እርሻህ ላይ የተረፈውን አትሰብስብ፤ በወይን እርሻህ ላይ የወዳደቀውን የወይን ፍሬ አትልቀም። እነዚህን ለድሃውና* ለባዕድ አገሩ ሰው ተውለት።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
11 “‘አትስረቁ፤+ አታታሉ፤+ አንዳችሁ በሌላው ላይ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት አትፈጽሙ።
12 በስሜ በሐሰት አትማሉ፤+ በዚህም የአምላካችሁን ስም አታርክሱ። እኔ ይሖዋ ነኝ።
13 ባልንጀራህን አታጭበርብር፤+ አትዝረፈውም።+ የቅጥር ሠራተኛውን ደሞዝ ሳትከፍል አታሳድር።+
14 “‘መስማት የተሳነውን አትርገም ወይም በዓይነ ስውሩ ፊት እንቅፋት አታስቀምጥ፤+ አምላክህን ፍራ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።
15 “‘ፍርድ አታዛቡ። ለድሃው አታዳላ ወይም ባለጸጋውን ከሌሎች አስበልጠህ አትመልከት።+ ለባልንጀራህ ፍትሐዊ ፍርድ ፍረድ።
16 “‘በሕዝብህ መካከል እየዞርክ ስም አታጥፋ።+ በባልንጀራህ ሕይወት* ላይ አትነሳ።*+ እኔ ይሖዋ ነኝ።
17 “‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው።+ የባልንጀራህ ኃጢአት ተባባሪ እንዳትሆን ተግሣጽ በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ ገሥጸው።+
18 “‘የሕዝብህን ልጆች አትበቀል፤+ በእነሱም ላይ ቂም አትያዝ፤ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።
19 “‘የሚከተሉትን ደንቦቼን ጠብቁ፦ ሁለት ዓይነት እንስሳትን አታዳቅል። በእርሻህ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤+ ከሁለት የተለያዩ የክር ዓይነቶች የተሠራ ልብስ አትልበስ።+
20 “‘አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ቢተኛና ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም፣ ሴቲቱ ደግሞ ለሌላ ወንድ የታጨች ሆኖም ገና ያልተዋጀች ወይም ነፃ ያልወጣች ባሪያ ብትሆን የቅጣት እርምጃ መወሰድ አለበት። ይሁንና ይህች ሴት ገና ነፃ ስላልወጣች መገደል የለባቸውም።
21 ሰውየው የበደል መባውን ይኸውም ለበደል መባ የሚሆነውን አውራ በግ ወደ ይሖዋ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ያምጣ።+
22 ካህኑም ሰውየው ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ እንዲሆን በቀረበው አውራ በግ በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል፤ የሠራውም ኃጢአት ይቅር ይባልለታል።
23 “‘እናንተም ወደ ምድሪቱ ብትገቡና ለምግብ የሚሆን ዛፍ ብትተክሉ ፍሬውን ርኩስና የተከለከለ* አድርጋችሁ ቁጠሩት። ለሦስት ዓመት ከእሱ መብላት የለባችሁም።* ፍሬው መበላት የለበትም።
24 በአራተኛው ዓመት ግን ፍሬው በሙሉ በይሖዋ ፊት የምትደሰቱበት ቅዱስ ነገር ይሆናል።+
25 ከዚያም በአምስተኛው ዓመት ፍሬውን መብላት ትችላላችሁ፤ ይህን ካደረጋችሁ ምርታችሁ ይበዛላችኋል። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
26 “‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ።+
“‘አታስጠንቁሉ ወይም አስማት አትሥሩ።+
27 “‘ጆሮ ግንዳችሁ አካባቢ ያለውን ፀጉር አትላጩ* ወይም የጢማችሁን ዳር ዳር አትላጩ።+
28 “‘ለሞተ ሰው* ብላችሁ አካላችሁን አትተልትሉ+ ወይም ሰውነታችሁን አትነቀሱ። እኔ ይሖዋ ነኝ።
29 “‘ምድሪቱ ዝሙት እንዳትፈጽምና ልቅ በሆነ ምግባር እንዳትሞላ+ ሴት ልጅህን ዝሙት አዳሪ በማድረግ አታዋርዳት።+
30 “‘ሰንበቶቼን ጠብቁ፤+ ለመቅደሴ አክብሮት* ይኑራችሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ።
31 “‘ወደ መናፍስት ጠሪዎች አትሂዱ፤+ ጠንቋዮችንም አትጠይቁ፤+ እንዲህ ካደረጋችሁ በእነሱ ትረክሳላችሁ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
32 “‘በሸበተው ሰው ፊት ተነስ፤+ አረጋዊውንም አክብር፤+ አምላክህን ፍራ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።
33 “‘በምድራችሁ አብሯችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ካለ አትበድሉት።+
34 አብሯችሁ የሚኖረውን የባዕድ አገር ሰው እንደ አገራችሁ ተወላጅ አድርጋችሁ ተመልከቱት፤+ እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁም ውደዱት፤ ምክንያቱም እናንተም በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
35 “‘ርዝመትን፣ ክብደትን ወይም መጠንን ስትለኩ በተጭበረበረ መለኪያ አትጠቀሙ።+
36 ትክክለኛ ሚዛን፣ ትክክለኛ የሚዛን ድንጋዮች፣ ትክክለኛ የደረቅ ነገር መስፈሪያና* ትክክለኛ የፈሳሽ ነገር መለኪያ* ሊኖራችሁ ይገባል።+ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
37 ስለሆነም ደንቦቼን ሁሉና ድንጋጌዎቼን በሙሉ ጠብቁ፤ እንዲሁም ፈጽሟቸው።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።’”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “ይፍራ።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “ለጎስቋላውና።”
^ ቃል በቃል “ደም።”
^ “የባልንጀራህ ሕይወት ለአደጋ ሲጋለጥ ዝም ብለህ አትመልከት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “እንደ ፍሬው ሸለፈት።”
^ ቃል በቃል “ለእናንተ እንዳልተገረዘ ይሆናል።”
^ ወይም “አትከርክሙ፤ አትቁረጡ።”
^ ወይም “ነፍስ።” እዚህ ቦታ ላይ የገባው ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል የሞተን ሰው የሚያመለክት ነው።
^ ወይም “አድናቆት።” ቃል በቃል “ፍርሃት።”