ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 20:1-15
20 እኔም የጥልቁን ቁልፍና+ ታላቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ አንድ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ።
2 እሱም ዘንዶውን+ ያዘውና ለ1,000 ዓመት አሰረው፤ ይህም ዘንዶ ዲያብሎስና+ ሰይጣን+ የሆነው የጥንቱ እባብ+ ነው።
3 ደግሞም ይህ 1,000 ዓመት እስኪያበቃ ድረስ ከእንግዲህ ሕዝቦችን እንዳያሳስት ወደ ጥልቁ+ ወረወረውና ዘጋበት፤ በማኅተምም አሸገው። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል።+
4 ዙፋኖችንም አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለተቀመጡት የመፍረድ ሥልጣን ተሰጣቸው። ስለ ኢየሱስ በመመሥከራቸውና ስለ አምላክ በመናገራቸው የተነሳ የተገደሉትን* ሰዎች ነፍሳት* እንዲሁም አውሬውን ወይም ምስሉን ያላመለኩትንና ምልክቱን በግንባራቸውም ሆነ በእጃቸው ላይ ያልተቀበሉትን ሰዎች አየሁ።+ እነሱም ሕያው ሆነው ከክርስቶስ ጋር ለ1,000 ዓመት ነገሡ።+
5 (የቀሩት ሙታን+ ይህ 1,000 ዓመት እስኪያበቃ ድረስ ሕያው አልሆኑም።) ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው።+
6 በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆኑ ሁሉ ደስተኞችና ቅዱሳን ናቸው፤+ ሁለተኛው ሞት+ በእነዚህ ላይ ሥልጣን የለውም፤+ ከዚህ ይልቅ የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤+ ከእሱም ጋር ለ1,000 ዓመት ይነግሣሉ።+
7 ይህ 1,000 ዓመት እንዳበቃም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤
8 እሱም በአራቱም የምድር ማዕዘናት ያሉትን ብሔራት፣ ጎግንና ማጎግን ለማሳሳትና ለጦርነቱ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ይወጣል። የእነዚህም ቁጥር በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነው።
9 እነሱም በምድር ሁሉ ተሰራጩ፤ እንዲሁም የቅዱሳኑን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ። ሆኖም እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው።+
10 ሲያሳስታቸው የነበረው ዲያብሎስም፣ አውሬውና+ ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ ተወረወረ፤+ እነሱም ለዘላለም ቀንና ሌሊት ይሠቃያሉ።*
11 እኔም አንድ ትልቅ ነጭ ዙፋንና በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን አየሁ።+ ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤+ ስፍራም አልተገኘላቸውም።
12 ከዚያም ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ የመጽሐፍ ጥቅልሎችም ተከፈቱ። ሌላም ጥቅልል ተከፈተ፤ ይህም የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ነው።+ ሙታን በጥቅልሎቹ ውስጥ በተጻፉት ነገሮች መሠረት እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።+
13 ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና መቃብርም* በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ፤ እነሱም እያንዳንዳቸው እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።+
14 ሞትና መቃብርም* ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወሩ።+ ይህም የእሳት ሐይቅ+ ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል።+
15 በተጨማሪም በሕይወት መጽሐፍ+ ላይ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወረ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “በመጥረቢያ የተቀሉትን።”
^ የቃላት መፍቻውንና ራእይ 6:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
^ ወይም “ቀንና ሌሊት ይታገታሉ፤ ቀንና ሌሊት ይታሰራሉ።”
^ ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።