የሐዋርያት ሥራ 13:1-52

  • በርናባስና ሳኦል ሚስዮናውያን ሆነው ተላኩ (1-3)

  • በቆጵሮስ የተከናወነ አገልግሎት (4-12)

  • ጳውሎስ በጵስድያ አንጾኪያ የሰጠው ንግግር (13-41)

  • ለብሔራት እንዲሰብኩ በትንቢት የተነገረ ትእዛዝ (42-52)

13  በአንጾኪያ ባለው ጉባኤ ውስጥ ነቢያትና አስተማሪዎች ነበሩ፤+ እነሱም፦ በርናባስ፣ ኒጌር ማለትም ጥቁር ተብሎ የሚጠራው ሲምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ የአውራጃ ገዢ ከሆነው ከሄሮድስ ጋር የተማረው ምናሔና ሳኦል ናቸው።  እነዚህ ይሖዋን* እያገለገሉና* እየጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳኦልን አንድ ሥራ እንዲሠሩ ስለመረጥኳቸው ለዩልኝ”+ አለ።  እነሱም ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ ከዚያም አሰናበቷቸው።  ሰዎቹም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ተጓዙ።  ስልማና በደረሱ ጊዜም የአምላክን ቃል በአይሁዳውያን ምኩራቦች ማወጅ ጀመሩ። ዮሐንስም እንደ አገልጋይ ሆኖ ይረዳቸው ነበር።+  ደሴቲቱን ከዳር እስከ ዳር አዳርሰው እስከ ጳፎስ ተጓዙ፤ በዚህ ጊዜ በርያሱስ የተባለ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የነበረ አንድ አይሁዳዊ አገኙ።  እሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ የሮም አገረ ገዢ* ጋር ነበር። ይህ አገረ ገዢ የአምላክን ቃል ለመስማት ስለጓጓ በርናባስንና ሳኦልን ጠራቸው።  ይሁን እንጂ ጠንቋዩ ኤልማስ* አገረ ገዢው ይህን እምነት እንዳይቀበል ለማከላከል ፈልጎ ይቃወማቸው ጀመር። (ኤልማስ የተባለው ስም ትርጉም ጠንቋይ ማለት ነው።)  በዚህ ጊዜ፣ ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራው ሳኦል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ተመለከተው፤ 10  ከዚያም እንዲህ አለው፦ “አንተ ተንኮልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፣ የዲያብሎስ ልጅ፣+ የጽድቅም ሁሉ ጠላት! ቀና የሆነውን የይሖዋን* መንገድ ማጣመምህን አትተውም? 11  እነሆ፣ የይሖዋ* እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዓይነ ስውር ትሆናለህ፤ ለተወሰነ ጊዜም የፀሐይ ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑም ጭጋግና ጨለማ ዓይኑን ጋረደው፤ እጁን ይዞ የሚመራው ሰው ለማግኘትም ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። 12  አገረ ገዢውም ስለ ይሖዋ* በተማረው ነገር ተደንቆ ስለነበር ይህን ባየ ጊዜ አማኝ ሆነ። 13  ጳውሎስና ባልደረቦቹ ከጳፎስ ተነስተው በባሕር ላይ በመጓዝ ጵንፍልያ ውስጥ ወዳለችው ወደ ጴርጌ ሄዱ። ዮሐንስ+ ግን ከእነሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።+ 14  እነሱ ግን ጉዟቸውን በመቀጠል ከጴርጌ ተነስተው በጵስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ መጡ። በሰንበት ቀንም ወደ ምኩራብ ገብተው+ ተቀመጡ። 15  የሕጉና የነቢያት መጻሕፍት በሕዝቡ ፊት ከተነበበ+ በኋላ የምኩራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ” የሚል መልእክት ላኩባቸው። 16  ስለዚህ ጳውሎስ ተነስቶ በእጁ ምልክት በመስጠት እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል ሰዎችም ሆናችሁ አምላክን የምትፈሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፣ ስሙ። 17  የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብፅ ምድር ባዕዳን ሆነው ይኖሩ በነበረበት ጊዜም ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኃያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው።+ 18  ለ40 ዓመት ያህልም በምድረ በዳ ታገሣቸው።+ 19  በከነአን ምድር የነበሩትን ሰባት ብሔራት ካጠፋ በኋላ ምድራቸውን ርስት አድርጎ ሰጣቸው።+ 20  ይህ ሁሉ የሆነው በ450 ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነው። “ይህ ከሆነ በኋላ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው።+ 21  ከዚያ በኋላ ግን ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ጠየቁ፤+ አምላክም ከቢንያም ነገድ የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን+ ለ40 ዓመት አነገሠላቸው። 22  እሱን ከሻረው በኋላ ‘እንደ ልቤ የሆነውን+ የእሴይን+ ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤ እሱ የምፈልገውን ነገር ሁሉ ያደርጋል’ ሲል የመሠከረለትን ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ አስነሳላቸው።+ 23  አምላክ በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር ለእስራኤል አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን አመጣ።+ 24  ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት በይፋ ሰብኮ ነበር።+ 25  ይሁንና ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ ‘እኔ ማን እመስላችኋለሁ? እኔ እኮ እሱ አይደለሁም። ይሁን እንጂ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል፤ እኔ የእግሩን ጫማ ለመፍታት እንኳ አልበቃም’ ይል ነበር።+ 26  “ወንድሞች፣ እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ እንዲሁም በመካከላችሁ ያሉ አምላክን የሚፈሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፣ ይህ የመዳን ቃል ለእኛ ተልኳል።+ 27  የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና የሃይማኖት መሪዎቻቸው* የእሱን ማንነት አልተገነዘቡም፤ በእሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ግን በየሰንበቱ ከፍ ባለ ድምፅ የሚነበበውን ነቢያት የተናገሩትን ቃል ፈጸሙ።+ 28  ለሞት የሚያበቃ አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ+ ያስገድለው ዘንድ ጲላጦስን ወተወቱት።+ 29  ስለ እሱ የተጻፈውን ነገር ሁሉ ከፈጸሙ በኋላም ከእንጨት* ላይ አውርደው መቃብር ውስጥ አኖሩት።+ 30  ሆኖም አምላክ ከሞት አስነሳው፤+ 31  እሱም ከገሊላ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ አብረውት ለሄዱት ሰዎች ለብዙ ቀናት ታያቸው። እነሱም አሁን ስለ እሱ ለሕዝቡ እየመሠከሩ ነው።+ 32  “ስለሆነም እኛ ለአባቶቻችን ስለተገባው ቃል የሚገልጸውን ምሥራች እያወጅንላችሁ ነው። 33  አምላክ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት+ ለእነሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ሙሉ በሙሉ ፈጽሞታል፤ ይህም የሆነው በሁለተኛው መዝሙር ላይ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ’ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ነው።+ 34  አምላክ ኢየሱስን የማይበሰብስ አካል ሰጥቶ ከሞት አስነስቶታል፤ ይህን አስቀድሞ በትንቢት ሲናገር ‘ለዳዊት ቃል የተገባውን የማይከስም * ታማኝ ፍቅር አሳያችኋለሁ’ ብሏል።+ 35  ስለዚህ በሌላም መዝሙር ላይ ‘ታማኝ አገልጋይህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ ብሏል።+ 36  በአንድ በኩል፣ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ አምላክን ካገለገለ* በኋላ በሞት አንቀላፍቷል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮ መበስበስን አይቷል።+ 37  በሌላ በኩል ግን አምላክ ከሞት ያስነሳው ኢየሱስ መበስበስን አላየም።+ 38  “ስለዚህ ወንድሞች፣ በእሱ በኩል የሚገኘው የኃጢአት ይቅርታ አሁን እየታወጀላችሁ እንዳለ እወቁ፤+ 39  በኢየሱስ የሚያምን ማንኛውም ሰው፣ በእሱ አማካኝነት ‘ከበደል ነፃ ነህ’ ሊባል ይችላል፤+ የሙሴ ሕግ ግን እናንተን ከበደል ነፃ ሊያደርጋችሁ አልቻለም።+ 40  ስለዚህ በነቢያት መጻሕፍት እንዲህ ተብሎ የተነገረው ነገር በእናንተ ላይ እንዳይደርስ ተጠንቀቁ፦ 41  ‘እናንተ ፌዘኞች፣ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም በዝርዝር ቢነግራችሁ እንኳ ፈጽሞ የማታምኑትን ሥራ በእናንተ ዘመን እያከናወንኩ ነውና።’”+ 42  እየወጡ ሳሉም ሰዎቹ ስለዚሁ ጉዳይ በሚቀጥለው ሰንበትም እንዲነግሯቸው ለመኗቸው። 43  በምኩራቡ የተደረገው ስብሰባ ከተበተነ በኋላ ከአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ተለውጠው አምላክን ከሚያመልኩት መካከል ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው፤ እነሱም ሰዎቹን በማነጋገር የአምላክን ጸጋ አጥብቀው እንደያዙ እንዲቀጥሉ አሳሰቧቸው።+ 44  በቀጣዩ ሰንበት የከተማዋ ሕዝብ ሁሉ ማለት ይቻላል፣ የይሖዋን* ቃል ለመስማት አንድ ላይ ተሰበሰበ። 45  አይሁዳውያንም ሕዝቡን ባዩ ጊዜ በቅናት ተሞልተው ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በመቃወም ይሳደቡ ጀመር።+ 46  በዚህ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ በድፍረት እንዲህ አሏቸው፦ “የአምላክ ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገሩ አስፈላጊ ነበር።+ እናንተ ግን ወደ ጎን ገሸሽ እያደረጋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ እየፈረዳችሁ ስለሆነ እኛም ለአሕዛብ እንሰብካለን።+ 47  ይሖዋ* ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ መዳንን እንድታመጣ ለብሔራት ብርሃን አድርጌ ሾሜሃለሁ’ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶናልና።”+ 48  ከአሕዛብ ወገን የሆኑት ይህን ሲሰሙ እጅግ በመደሰት የይሖዋን* ቃል አከበሩ፤ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ። 49  ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ* ቃል በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ እየተስፋፋ ሄደ። 50  ይሁንና አይሁዳውያን ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን የተከበሩ ሴቶችና በከተማዋ የሚኖሩትን ታላላቅ ወንዶች በመቀስቀስ በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት አስነሱ፤+ ከክልላቸውም አስወጧቸው። 51  እነሱም የእግራቸውን አቧራ አራግፈው* ወደ ኢቆንዮን ሄዱ።+ 52  ደቀ መዛሙርቱም በደስታና+ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ለይሖዋ ሕዝባዊ አገልግሎት እያቀረቡና።”
የሮም የአንድ አውራጃ ገዢ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ይህ ሰው ሥራ 13:6 ላይ በርያሱስ ተብሎም ተጠርቷል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ገዢዎቻቸው።”
ወይም “ከዛፍ።”
ወይም “እምነት የሚጣልበት፤ አስተማማኝ የሆነ።”
ወይም “የአምላክን ፈቃድ ካገለገለ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የእግርን አቧራ ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።