ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 11:1-19

 • ሁለቱ ምሥክሮች (1-13)

  • ማቅ ለብሰው ለ1,260 ቀናት ትንቢት ተናገሩ (3)

  • ተገድለው ሳይቀበሩ ቀሩ (7-10)

  • ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ሕያው ሆኑ (11, 12)

 • ሁለተኛው ወዮታ አልፏል፤ ሦስተኛው እየመጣ ነው (14)

 • ሰባተኛው መለከት (15-19)

  • “የጌታችንና የእሱ መሲሕ መንግሥት” (15)

  • ምድርን እያጠፉ ያሉት ይጠፋሉ (18)

11  እኔም ዘንግ* የሚመስል ሸምበቆ+ ተሰጠኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ “ተነስና የአምላክን ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ፣* መሠዊያውንና በዚያ የሚያመልኩትን ለካ።  ሆኖም ከቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ውጭ ያለውን ግቢ ሙሉ በሙሉ ተወው፤ አትለካው፤ ምክንያቱም ለአሕዛብ ተሰጥቷል፤ እነሱም የተቀደሰችውን ከተማ+ ለ42 ወራት ይረግጧታል።+  እኔም ሁለቱ ምሥክሮቼ ማቅ ለብሰው ለ1,260 ቀናት ትንቢት እንዲናገሩ አደርጋለሁ።”  እነዚህ በሁለቱ የወይራ ዛፎችና+ በሁለቱ መቅረዞች ተመስለዋል፤+ እነሱም በምድር ጌታ ፊት ቆመዋል።+  ማንም እነሱን ሊጎዳ ቢፈልግ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ይበላል። ማንም ሊጎዳቸው ቢፈልግ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መገደል አለበት።  እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ቀናት ምንም ዝናብ እንዳይዘንብ+ ሰማይን የመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤+ እንዲሁም ውኃዎችን ወደ ደም የመለወጥና+ የፈለጉትን ጊዜ ያህል፣ በማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት ምድርን የመምታት ሥልጣን አላቸው።  የምሥክርነት ሥራቸውን ባጠናቀቁ ጊዜ፣ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ውጊያ ይከፍትባቸዋል፤ ድል ይነሳቸዋል፤ እንዲሁም ይገድላቸዋል።+  አስከሬናቸውም በመንፈሳዊ ሁኔታ ሰዶምና ግብፅ ተብላ በምትጠራውና የእነሱም ጌታ በእንጨት ላይ በተሰቀለባት በታላቂቱ ከተማ አውራ ጎዳና ላይ ይጋደማል።  ከተለያዩ ሕዝቦች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችም ለሦስት ቀን ተኩል አስከሬናቸውን ያያሉ፤+ አስከሬናቸውም እንዲቀበር አይፈቅዱም። 10  እነዚህ ሁለት ነቢያት በምድር ላይ የሚኖሩትን አሠቃይተው ስለነበር በምድር ላይ የሚኖሩት በእነሱ ሞት ይደሰታሉ፤ ሐሴትም ያደርጋሉ እንዲሁም እርስ በርሳቸው ስጦታ ይሰጣጣሉ። 11  ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ከአምላክ የመጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤+ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ያዩአቸውም ሰዎች በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ። 12  ከሰማይም አንድ ታላቅ ድምፅ “ወደዚህ ውጡ” ሲላቸው ሰሙ። እነሱም በደመና ውስጥ ሆነው ወደ ሰማይ ወጡ፤ ጠላቶቻቸውም አዩአቸው።* 13  በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር ነውጥ ተከሰተ፤ የከተማዋ አንድ አሥረኛም ወደቀ፤ በምድር ነውጡም 7,000 ሰዎች ሞቱ፤ የቀሩትም ፍርሃት አደረባቸው፤ ለሰማይ አምላክም ክብር ሰጡ። 14  ሁለተኛው ወዮታ+ አልፏል። እነሆ፣ ሦስተኛው ወዮታ በፍጥነት ይመጣል። 15  ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ።+ በሰማይም ታላላቅ ድምፆች እንዲህ ሲሉ ተሰሙ፦ “የዓለም መንግሥት የጌታችንና+ የእሱ መሲሕ+ መንግሥት ሆነ፤ እሱም ለዘላለም ይነግሣል።”+ 16  በአምላክ ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው የነበሩት 24ቱ ሽማግሌዎችም+ በግንባራቸው ተደፍተው ለአምላክ ሰገዱ፤ 17  እንዲህም አሉ፦ “ያለህና+ የነበርክ፣ ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ* አምላክ ሆይ፣ ታላቅ ኃይልህን ስለያዝክና ንጉሥ ሆነህ መግዛት ስለጀመርክ+ እናመሰግንሃለን። 18  ሆኖም ብሔራት ተቆጡ፤ የአንተም ቁጣ መጣ፤ በሙታን ላይ የምትፈርድበት፣ ለባሪያዎችህ ለነቢያት፣+ ለቅዱሳንና ስምህን ለሚፈሩ ለታናናሾችና ለታላላቆች ወሮታ የምትከፍልበት+ እንዲሁም ምድርን እያጠፉ ያሉትን+ የምታጠፋበት* የተወሰነው ጊዜ መጣ።” 19  በሰማይ ያለው የአምላክ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ* ተከፍቶ ነበር፤ የቃል ኪዳኑ ታቦትም በቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ታየ።+ እንዲሁም የመብረቅ ብልጭታ፣ ድምፅ፣ ነጎድጓድ፣ የምድር ነውጥና ታላቅ በረዶ ተከሰተ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መለኪያ ዘንግ።”
ቅድስቱንና ቅድስተ ቅዱሳኑን የያዘውን የቤተ መቅደሱን ማዕከላዊ ክፍል ያመለክታል።
ወይም “ይመለከቷቸው ነበር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ምድርን እያበላሹ ባሉት ላይ እርምጃ የምትወስድበት።”
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።