ሕዝቅኤል 8:1-18

  • ሕዝቅኤል በራእይ ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰደ (1-4)

  • በቤተ መቅደሱ ውስጥ አስጸያፊ ነገሮች ታዩ (5-18)

    • ሴቶች ለታሙዝ አለቀሱ (14)

    • ወንዶች ፀሐይን አመለኩ (16)

8  በስድስተኛውም ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ ከወሩም በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ፣ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ በዚያ የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ እጅ ያዘኝ።  እነሆም እሳት የሚመስል ነገር ተመለከትኩ፤ ወገቡ ከሚመስለው ነገር በታች እሳት ነበር፤+ ደግሞም ከወገቡ በላይ መልኩ እንደሚያብረቀርቅ ብረት* ደማቅ ነበር።+  ከዚያም እጅ የሚመስል ነገር ዘርግቶ የራስ ፀጉሬን ያዘ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል ይዞ ወሰደኝ፤ አምላክ በገለጠልኝ ራእዮች አማካኝነት ወደ ኢየሩሳሌም ይኸውም ቅናት የሚቀሰቅሰው የቅናት ጣዖት ምልክት* ወደቆመበት+ በሰሜን ትይዩ ወደሚገኘው ወደ ውስጠኛው ግቢ በር+ አመጣኝ።  እነሆም፣ በሸለቋማው ሜዳ አይቼው የነበረውን የሚመስል የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበር።+  ከዚያም “የሰው ልጅ ሆይ፣ እባክህ ዓይንህን አንስተህ ወደ ሰሜን ተመልከት” አለኝ። ስለዚህ ወደ ሰሜን ተመለከትኩ፤ በዚያም ከመሠዊያው በር በስተ ሰሜን በኩል መግቢያው ላይ ይህ የቅናት ምልክት* ነበር።  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ የእስራኤል ቤት ሰዎች በዚህ ቦታ የሚሠሯቸውን ከመቅደሴ እንድርቅ የሚያደርጉ ነገሮች+ ይኸውም የሚፈጽሟቸውን አስከፊና አስጸያፊ ነገሮች ትመለከታለህ?+ ይበልጥ አስከፊ የሆኑ አስጸያፊ ነገሮችን ገና ታያለህ።”  ከዚያም ወደ ቅጥር ግቢው መግቢያ አመጣኝ፤ እኔም ስመለከት በግድግዳው ላይ አንድ ቀዳዳ አየሁ።  እሱም “የሰው ልጅ ሆይ፣ እስቲ ግድግዳውን ንደለው” አለኝ። እኔም ግድግዳውን ነደልኩት፤ አንድ መግቢያም ተመለከትኩ።  እሱም “ወደ ውስጥ ግባና በዚህ ቦታ የሚሠሯቸውን ክፉና አስጸያፊ ነገሮች ተመልከት” አለኝ። 10  እኔም ገብቼ አየሁ፤ መሬት ለመሬት የሚሳቡ ፍጥረታትንና የሚያስጠሉ አራዊትን+ ሁሉ እንዲሁም አስጸያፊ የሆኑ የእስራኤል ቤት ጣዖቶችን* ሁሉ ምስል+ ተመለከትኩ፤ ምስላቸውም በግድግዳው ዙሪያ ተቀርጾ ነበር። 11  ደግሞም 70 የሚሆኑ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች በምስሎቹ ፊት ቆመው ነበር፤ የሳፋን+ ልጅ ያአዛንያህ በመካከላቸው ቆሞ ነበር። እያንዳንዳቸውም በእጃቸው ጥና የያዙ ሲሆን መልካም መዓዛ ያለው የዕጣን ጭስም እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር።+ 12  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዳቸው ጣዖቶቻቸው ባሉባቸው* እልፍኞች ውስጥ በጨለማ ምን እንደሚያደርጉ ታያለህ? እነሱ ‘ይሖዋ አያየንም። ይሖዋ ምድሪቱን ትቷታል’ ይላሉና።”+ 13  ደግሞም “እነሱ የሚሠሯቸውን ይበልጥ አስከፊ የሆኑ አስጸያፊ ነገሮች ታያለህ” አለኝ። 14  በመሆኑም በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ይሖዋ ቤት በር መግቢያ አመጣኝ፤ በዚያም ሴቶች ተቀምጠው ታሙዝ ለተባለው አምላክ ሲያለቅሱ አየሁ። 15  እሱም በመቀጠል “የሰው ልጅ ሆይ፣ ይህን ታያለህ? ከእነዚህ የባሰ አስከፊ የሆኑ አስጸያፊ ነገሮች ታያለህ” አለኝ።+ 16  በመሆኑም ወደ ይሖዋ ቤት ውስጠኛው ግቢ+ አመጣኝ። በዚያም በይሖዋ ቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ በበረንዳውና በመሠዊያው መካከል 25 ያህል ወንዶች ነበሩ፤ እነሱም ጀርባቸውን ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ሰጥተው ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው ነበር፤ ደግሞም በምሥራቅ አቅጣጫ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር።+ 17  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ ይህን ታያለህ? የይሁዳ ቤት እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች መፈጸማቸው፣ ምድሪቱን በዓመፅ መሙላታቸውና+ እኔን ማስቆጣታቸው ቀላል ነገር ነው? እነሆ፣ ቅርንጫፉን* ወደ አፍንጫዬ አቅርበዋል። 18  በመሆኑም በቁጣ እርምጃ እወስዳለሁ። ዓይኔ አያዝንም፤ ደግሞም አልራራም።+ በታላቅ ድምፅ ወደ ጆሮዬ ቢጮኹም አልሰማቸውም።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

የሚያብረቀርቅ የወርቅና የብር ቅይጥ።
ወይም “ምስል።”
ወይም “ምስል።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “የተቀረጹ ምስሎቻቸው በሚገኙባቸው።”
ለጣዖት አምልኮ ይጠቀሙበት የነበረ ቅርንጫፍ እንደሆነ ይታመናል።