የያዕቆብ ደብዳቤ 5:1-20

  • ለሀብታሞች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (1-6)

  • አምላክ በትዕግሥት የሚጸኑትን ይባርካል (7-11)

  • “‘አዎ’ ካላችሁ አዎ ይሁን” (12)

  • በእምነት የቀረበ ጸሎት ኃይል አለው (13-18)

  • ኃጢአተኛን ከስህተት ጎዳናው መመለስ (19, 20)

5  እናንተ ሀብታሞች እንግዲህ ስሙ፤ እየመጣባችሁ ባለው መከራ አልቅሱ እንዲሁም ዋይ ዋይ በሉ።+ 2  ሀብታችሁ በስብሷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል።+ 3  ወርቃችሁና ብራችሁ ሙሉ በሙሉ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሠክራል፤ ሥጋችሁንም ይበላል። ያከማቻችሁት ነገር በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደ እሳት ይሆናል።*+ 4  እነሆ፣ በእርሻችሁ ላይ ያለውን ሰብል ለሰበሰቡት ሠራተኞች ሳትከፍሏቸው የቀራችሁት ደሞዝ ይጮኻል፤ አጫጆቹም ለእርዳታ የሚያሰሙት ጥሪ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ ይሖዋ* ጆሮ ደርሷል።+ 5  በምድር ላይ በቅንጦት ኖራችኋል፤ የራሳችሁንም ፍላጎት ለማርካት ትጥሩ ነበር። በእርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል።+ 6  ጻድቁን ኮነናችሁት፤ ደግሞም ገደላችሁት። እሱ እየተቃወማችሁ አይደለም?* 7  እንግዲህ ወንድሞች፣ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ+ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ። እነሆ፣ ገበሬ የመጀመሪያውና የኋለኛው ዝናብ እስኪመጣ ድረስ በመታገሥ የምድርን መልካም ፍሬ ይጠባበቃል።+ 8  እናንተም በትዕግሥት ጠብቁ፤+ ጌታ የሚገኝበት ጊዜ ስለተቃረበ ልባችሁን አጽኑ።+ 9  ወንድሞች፣ እንዳይፈረድባችሁ አንዳችሁ በሌላው ላይ አታጉረምርሙ።*+ እነሆ፣ ፈራጁ ደጃፍ ላይ ቆሟል። 10  ወንድሞች፣ በይሖዋ* ስም የተናገሩትን ነቢያት+ መከራ በመቀበልና ትዕግሥት በማሳየት+ ረገድ አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው።+ 11  እነሆ፣ የጸኑትን ደስተኞች* እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን።+ ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤+ በውጤቱም ይሖዋ* ያደረገለትን አይታችኋል፤+ በዚህም ይሖዋ* እጅግ አፍቃሪና* መሐሪ እንደሆነ ተመልክታችኋል።+ 12  ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም በሌላ መሐላ መማላችሁን ተዉ። ከዚህ ይልቅ “አዎ” ካላችሁ አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ካላችሁ አይደለም ይሁን፤+ አለዚያ ለፍርድ ትዳረጋላችሁ። 13  ከእናንተ መካከል መከራ እየደረሰበት ያለ ሰው አለ? መጸለዩን ይቀጥል።+ ደስ የተሰኘ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር።+ 14  ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤+ እነሱም በይሖዋ* ስም ዘይት ቀብተው+ ይጸልዩለት። 15  በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን* ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም* ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባላል። 16  ስለዚህ ፈውስ ማግኘት እንድትችሉ አንዳችሁ ለሌላው ኃጢአታችሁን በግልጽ ተናዘዙ፤+ እንዲሁም አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ። ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።+ 17  ኤልያስ እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር፤ ያም ሆኖ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ በጸለየ ጊዜ በምድሩ ላይ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናብ አልዘነበም።+ 18  ከዚያም እንደገና ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብ ሰጠ፤ ምድሩም ፍሬ አፈራ።+ 19  ወንድሞቼ፣ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ከእውነት መንገድ ስቶ ቢወጣና ሌላ ሰው ቢመልሰው፣ 20  ኃጢአተኛን ከስህተት ጎዳናው የሚመልስ ማንኛውም ሰው+ ኃጢአተኛውን* ከሞት እንደሚያድንና ብዙ ኃጢአትን እንደሚሸፍን እወቁ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሥጋችሁን እንደ እሳት ይበላዋል። በመጨረሻዎቹ ቀናት ሀብት አከማችታችኋል።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እሱ እየተቃወማችሁ አይደለም።”
ወይም “አታማሩ።” ቃል በቃል “አታቃስቱ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ከአንጀት የሚራራና።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የተባረኩ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“የደከመውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የኃጢአተኛውን ነፍስ።”