የዮሐንስ ወንጌል 5:1-47
5 ከዚህ በኋላ የአይሁዳውያን በዓል+ ስለነበረ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
2 በኢየሩሳሌም በበጎች በር+ አጠገብ አምስት ባለ መጠለያ መተላለፊያዎች ያሉት በዕብራይስጥ ቤተዛታ ተብሎ የሚጠራ አንድ የውኃ ገንዳ ነበር።
3 በእነዚህ መተላለፊያዎች ውስጥ ብዙ ሕመምተኞች፣ ዓይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች* ይተኙ ነበር።
4 *——
5 በዚያም ለ38 ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር።
6 ኢየሱስ ይህን ሰው በዚያ ተኝቶ አየውና ለረጅም ጊዜ ሕመምተኛ ሆኖ እንደኖረ አውቆ “መዳን ትፈልጋለህ?”+ አለው።
7 ሕመምተኛውም “ጌታዬ፣ ውኃው በሚናወጥበት ጊዜ ገንዳው ውስጥ የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ ወደ ገንዳው ስሄድ ደግሞ ሌላው ቀድሞኝ ይገባል” ሲል መለሰለት።
8 ኢየሱስም “ተነስ! ምንጣፍህን* ተሸክመህ ሂድ” አለው።+
9 ሰውየውም ወዲያውኑ ተፈወሰ፤ ምንጣፉንም* አንስቶ መሄድ ጀመረ።
ቀኑም ሰንበት ነበር።
10 በመሆኑም አይሁዳውያን የተፈወሰውን ሰው “ሰንበት እኮ ነው፤ ምንጣፍህን* እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት።+
11 እሱ ግን “የፈወሰኝ ሰው ራሱ ‘ምንጣፍህን* ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው።
12 እነሱም “‘ምንጣፍህን* ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ ሰው ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
13 ሆኖም ኢየሱስ ከቦታው ዞር ብሎ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ስለነበር ሰውየው የፈወሰውን ሰው ማንነት ማወቅ አልቻለም።
14 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሰውየውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘውና “አሁን ደህና ሆነሃል። የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ኃጢአት አትሥራ” አለው።
15 ሰውየውም ሄዶ የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ለአይሁዳውያኑ ነገራቸው።
16 ከዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ በኢየሱስ ላይ ስደት ያደርሱበት ጀመር፤ ይህን ያደረጉት በሰንበት ቀን እነዚህን ነገሮች ይፈጽም ስለነበረ ነው።
17 እሱ ግን “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ”+ ሲል መለሰላቸው።
18 ከዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ ሰንበትን ስለጣሰ ብቻ ሳይሆን አምላክን የገዛ አባቱ እንደሆነ አድርጎ በመጥራት+ ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል ስላደረገ+ እሱን ለመግደል ይበልጥ ተነሳሱ።
19 ስለሆነም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ወልድ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ብቻ እንጂ በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ አይችልም።+ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድም በተመሳሳይ መንገድ ያንኑ ያደርጋል።
20 ምክንያቱም አብ ወልድን ይወደዋል፤+ እንዲሁም እሱ ራሱ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።+
21 አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸውና ሕያው እንደሚያደርጋቸው+ ሁሉ ወልድም እንዲሁ የፈለገውን ሰው ሕያው ያደርጋል።+
22 አብ በማንም ላይ አይፈርድምና፤ ከዚህ ይልቅ የመፍረዱን ሥልጣን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶታል፤+
23 ይህን ያደረገውም ሁሉም አብን እንደሚያከብሩ ሁሉ ወልድንም እንዲያከብሩ ነው። ወልድን የማያከብር ሁሉ እሱን የላከውን አብንም አያከብርም።+
24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሌን የሚሰማና የላከኝን የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤+ ወደ ፍርድም አይመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግሯል።+
25 “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሙታን የአምላክን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።
26 አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው* ሁሉ፣+ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።+
27 እሱ የሰው ልጅ+ ስለሆነ የመፍረድ ሥልጣን ሰጥቶታል።+
28 በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤+
29 መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ* ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።+
30 በራሴ ተነሳስቼ አንድም ነገር ማድረግ አልችልም። እንደሰማሁ እፈርዳለሁ፤ የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ+ መፈጸም ስለምፈልግ የምፈርደው የጽድቅ ፍርድ ነው።+
31 “እኔ ብቻ ስለ ራሴ ብመሠክር ምሥክርነቴ እውነት አይደለም።+
32 ስለ እኔ የሚመሠክር ሌላ አለ፤ ደግሞም እሱ ስለ እኔ የሚሰጠው ምሥክርነት እውነት እንደሆነ አውቃለሁ።+
33 ወደ ዮሐንስ ሰዎች ልካችሁ ነበር፤ እሱም ለእውነት መሥክሯል።+
34 ይሁን እንጂ እኔ የሰው ምሥክርነት አያስፈልገኝም፤ ይህን የምናገረው ግን እናንተ እንድትድኑ ነው።
35 ያ ሰው የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበር፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በእሱ ብርሃን እጅግ ለመደሰት ፈቃደኞች ነበራችሁ።+
36 እኔ ግን ከዮሐንስ የበለጠ ምሥክር አለኝ፤ ምክንያቱም አባቴ እንዳከናውነው የሰጠኝ ሥራ ማለትም እየሠራሁት ያለው ይህ ሥራ አብ እንደላከኝ ይመሠክራል።+
37 የላከኝ አብም ራሱ ስለ እኔ መሥክሯል።+ እናንተ መቼም ቢሆን ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤+
38 እሱ የላከውንም ስለማታምኑ ቃሉ በልባችሁ ውስጥ አይኖርም።
39 “እናንተ በቅዱሳን መጻሕፍት የዘላለም ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ እነሱን ትመረምራላችሁ፤+ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሠክሩ ናቸው።+
40 ሆኖም ሕይወት እንድታገኙ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም።+
41 እኔ ከሰው ክብር መቀበል አልፈልግም፤
42 ይሁንና እናንተ የአምላክ ፍቅር በውስጣችሁ እንደሌለ በሚገባ አውቃለሁ።
43 እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም። ሌላው ግን በራሱ ስም ቢመጣ ትቀበሉታላችሁ።
44 እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡና ከአንዱ አምላክ የሚገኘውን ክብር የማትፈልጉ ሆናችሁ ሳላችሁ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?+
45 እኔ በአብ ፊት የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ ሌላ አለ፤ እሱም ተስፋ የጣላችሁበት ሙሴ ነው።+
46 ደግሞም ሙሴን ብታምኑት ኖሮ እኔንም ታምኑኝ ነበር፤ እሱ ስለ እኔ ጽፏልና።+
47 ሆኖም እሱ የጻፈውን ካላመናችሁ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “እግራቸው ወይም እጃቸው የሰለለ።”
^ ወይም “መኝታህን።”
^ ወይም “መኝታውንም።”
^ ወይም “መኝታህን።”
^ ወይም “መኝታህን።”
^ ወይም “መኝታህን።”
^ ወይም “በራሱ የሕይወት ስጦታ እንዳለው።”
^ መጥፎ ነገር መሥራትን ልማድ ያደረጉ ሰዎችን ያመለክታል።