ዘፀአት 16:1-36

  • ሕዝቡ በምግብ የተነሳ አጉረመረመ (1-3)

  • ይሖዋ ማጉረምረማቸውን ሰማ (4-12)

  • ድርጭትና መና ተሰጣቸው (13-21)

  • በሰንበት ቀን መና አልነበረም (22-30)

  • መና ለመታሰቢያነት ተቀመጠ (31-36)

16  ከኤሊም ከተነሱ በኋላም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ከግብፅ ምድር በወጣ በሁለተኛው ወር በ15ኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወደሚገኘው ወደ ሲን ምድረ በዳ+ መጣ።  ከዚያም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ በምድረ በዳ ሳለ በሙሴና በአሮን ላይ ማጉረምረም ጀመረ።+  እስራኤላውያንም እንዲህ ይሏቸው ነበር፦ “በግብፅ ምድር በሥጋው ድስት አጠገብ ተቀምጠን ሳለንና እስክንጠግብ ድረስ ዳቦ ስንበላ በነበረበት ጊዜ ምነው በይሖዋ እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ።+ እናንተ ግን ይህን ጉባኤ በሙሉ በረሃብ ልትጨርሱት ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን።”+  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኔ ከሰማይ ምግብ አዘንብላችኋለሁ፤+ ሕዝቡም ይውጣ፤ እያንዳንዱም ሰው ወጥቶ የሚበቃውን ያህል በየዕለቱ ይሰብስብ፤+ በዚህም ሕጌን አክብረው ይመላለሱ እንደሆነና እንዳልሆነ እፈትናቸዋለሁ።+  በስድስተኛው ቀን+ የሰበሰቡትን በሚያዘጋጁበት ጊዜ ግን በሌሎቹ ቀናት ከሚሰበስቡት እጥፍ ይሁን።”+  በመሆኑም ሙሴና አሮን እስራኤላውያንን በሙሉ እንዲህ አሏቸው፦ “ከግብፅ ምድር ያወጣችሁ ይሖዋ መሆኑን በዚህ ምሽት በእርግጥ ታውቃላችሁ።+  ጠዋት ላይ የይሖዋን ክብር ታያላችሁ፤ ምክንያቱም ይሖዋ በእሱ ላይ ማጉረምረማችሁን ሰምቷል። በእኛ ላይ የምታጉረመርሙት ለመሆኑ እኛ ማን ነን?”  ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ምሽት ላይ፣ የምትበሉት ሥጋ ጠዋት ላይ ደግሞ የምትፈልጉትን ያህል ዳቦ ሲሰጣችሁ ይሖዋ በእሱ ላይ ያጉረመረማችሁትን ማጉረምረም እንደሰማ ታያላችሁ። ታዲያ እኛ ማን ነን? ያጉረመረማችሁት በእኛ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ነው።”+  ሙሴም አሮንን “ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ‘ማጉረምረማችሁን ስለሰማ ኑ በይሖዋ ፊት ቅረቡ’ በላቸው” አለው።+ 10  አሮን ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ምድረ በዳው ዞሮ ቆመ፤ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ክብር በደመናው ውስጥ ተገለጠ።+ 11  በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12  “የእስራኤላውያንን ማጉረምረም ሰምቻለሁ።+ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘አመሻሹ ላይ* ሥጋ ትበላላችሁ፤ ጠዋት ላይ ደግሞ ዳቦ ትጠግባላችሁ፤+ እኔም አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ።’”+ 13  በዚህም መሠረት ምሽት ላይ ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤+ ጠዋት ላይም በሰፈሩ ውስጥ ሁሉ ጤዛ ወርዶ ነበር። 14  በኋላም ጤዛው ሲተን በምድረ በዳው ላይ እንደ አመዳይ ደቃቅ የሆነ ቅርፊት የሚመስል ስስ ነገር+ መሬቱ ላይ ታየ። 15  እስራኤላውያንም ባዩት ጊዜ ምን እንደሆነ ስላላወቁ እርስ በርሳቸው “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ይባባሉ ጀመር። ስለሆነም ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንድትበሉት የሰጣችሁ ምግብ ነው።+ 16  ይሖዋ እንዲህ ሲል አዟል፦ ‘እያንዳንዱ ሰው የሚበላውን ያህል ይሰብስብ። እያንዳንዳችሁ በድንኳናችሁ ውስጥ ባሉት ሰዎች ቁጥር* ልክ ለእያንዳንዱ ሰው አንድ ኦሜር*+ ሰፍራችሁ ውሰዱ።’” 17  እስራኤላውያንም እንደተባሉት አደረጉ፤ ይሰበስቡም ጀመር፤ አንዳንዶቹ ብዙ ሌሎቹ ደግሞ ትንሽ ሰበሰቡ። 18  የሰበሰቡትን በኦሜር ሲሰፍሩት ብዙ የሰበሰበው ምንም ትርፍ አላገኘም፤ ጥቂት የሰበሰበውም ምንም አልጎደለበትም።+ እያንዳንዳቸው የሰበሰቡት የሚበሉትን ያህል ነበር። 19  ከዚያም ሙሴ “ማንም ሰው እስከ ጠዋት ድረስ ምንም ማስተረፍ የለበትም”+ አላቸው። 20  እነሱ ግን ሙሴን አልሰሙትም። አንዳንዶቹ ከሰበሰቡት ውስጥ የተወሰነውን አሳደሩት፤ ሆኖም ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ በመሆኑም ሙሴ በእነሱ ላይ እጅግ ተቆጣ። 21  በየማለዳው እያንዳንዱ ሰው የሚበላውን ያህል ይሰበስብ ነበር። ፀሐዩ እየበረታ በሚሄድበት ጊዜም ይቀልጥ ነበር። 22  በስድስተኛውም ቀን ሁለት እጥፍ ምግብ+ ይኸውም ለአንድ ሰው ሁለት ኦሜር ሰበሰቡ። በመሆኑም የማኅበረሰቡ አለቆች በሙሉ መጥተው ሁኔታውን ለሙሴ ነገሩት። 23  በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ይሄማ ይሖዋ የተናገረው ነገር ነው። ነገ ሙሉ በሙሉ የእረፍት ቀን* ይኸውም ለይሖዋ ቅዱስ ሰንበት ይሆናል።+ የምትጋግሩትን ጋግሩ፤ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፤+ የተረፈውን ሁሉ አስቀምጡ፤ እስከ ጠዋትም ድረስ አቆዩት።” 24  እነሱም ልክ ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት እስከ ጠዋት ድረስ አቆዩት፤ ምግቡም አልሸተተም ወይም አልተላም። 25  ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “ዛሬ ይህን ብሉ፤ ምክንያቱም ዛሬ የይሖዋ ሰንበት ነው። ዛሬ ሜዳው ላይ አታገኙትም። 26  ስድስት ቀን ትሰበስባላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን ይኸውም በሰንበት ቀን+ ግን ምንም አይገኝም።” 27  ይሁንና ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ሊሰበስቡ ወጡ፤ ሆኖም ምንም አላገኙም። 28  በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እናንተ ሰዎች ትእዛዛቴንና ሕጎቼን ለማክበር እንቢተኛ የምትሆኑት እስከ መቼ ነው?+ 29  ይሖዋ ሰንበትን እንደሰጣችሁ ልብ በሉ።+ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን ምግብ የሰጣችሁም ለዚህ ነው። እያንዳንዱ ሰው ባለበት ስፍራ መቆየት አለበት፤ በሰባተኛውም ቀን ማንም ሰው ካለበት ቦታ መውጣት የለበትም።” 30  ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ሰንበትን አከበረ።*+ 31  የእስራኤልም ቤት ምግቡን “መና”* አሉት። እሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ሲሆን ጣዕሙም ማር እንደተቀባ ቂጣ ነበር።+ 32  ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንዲህ ሲል አዟል፦ ‘ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉት የሰጠኋችሁን ምግብ እንዲያዩ ከእሱ አንድ ኦሜር ሰፍራችሁ ለሚመጡት ትውልዶቻችሁ ሁሉ አስቀምጡ።’”+ 33  በመሆኑም ሙሴ አሮንን “ማሰሮ ወስደህ አንድ ኦሜር መና ጨምርበት፤ ለሚመጡት ትውልዶቻችሁ ሁሉ ተጠብቆ እንዲቆይ በይሖዋ ፊት አስቀምጠው” አለው።+ 34  አሮንም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ተጠብቆ እንዲቆይ መናውን በምሥክሩ*+ ፊት አስቀመጠው። 35  እስራኤላውያንም ወደሚኖሩበት ምድር እስከሚመጡ ድረስ+ ለ40 ዓመት+ መናውን በሉ። ወደ ከነአን ምድር ድንበር+ እስከሚደርሱ ድረስ መናውን በሉ። 36  አንድ ኦሜር፣ የኢፍ መስፈሪያ* አንድ አሥረኛ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
አንድ ኦሜር 2.2 ሊትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ነፍሳት ቁጥር።”
ወይም “የሰንበት በዓል።”
ወይም “አረፈ።”
“ምንድን ነው?” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ አባባል የመጣ ሳይሆን አይቀርም።
“ምሥክሩ” የሚለው ቃል አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የሚቀመጡበትን ሣጥን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።