የማቴዎስ ወንጌል 9:1-38

  • ኢየሱስ አንድ ሽባ ፈወሰ (1-8)

  • ኢየሱስ ማቴዎስን ጠራው (9-13)

  • ጾምን በተመለከተ የቀረበ ጥያቄ (14-17)

  • የኢያኢሮስ ሴት ልጅ፤ አንዲት ሴት የኢየሱስን ልብስ ነካች (18-26)

  • ኢየሱስ ዓይነ ስውሮችንና ዱዳ የሆነውን ሰው ፈወሰ (27-34)

  • አዝመራው ብዙ፣ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት (35-38)

9  ከዚህ በኋላ ጀልባ በመሳፈር ባሕሩን ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ* መጣ።+  በዚያም ሰዎች ቃሬዛ ላይ የተኛ አንድ ሽባ ሰው ወደ እሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ ሽባውን “ልጄ ሆይ አይዞህ! ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።+  በዚህ ጊዜ አንዳንድ ጸሐፍት በልባቸው “ይህ ሰው እኮ አምላክን እየተዳፈረ ነው” አሉ።  ኢየሱስ ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ፦ “በልባችሁ ክፉ ነገር የምታስቡት ለምንድን ነው?+  ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነስተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?+  ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .” አላቸውና ሽባውን “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።+  እሱም ተነስቶ ወደ ቤቱ ሄደ።  ሕዝቡም ይህን ሲያዩ በፍርሃት ተዋጡ፤ እንዲህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውንም አምላክ አከበሩ።  ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ እየሄደ ሳለ ማቴዎስ የሚባል ሰው በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየና “ተከታዬ ሁን” አለው። በዚህ ጊዜ ተነስቶ ተከተለው።+ 10  በኋላም በማቴዎስ ቤት እየበላ ሳለ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይበሉ ጀመር።+ 11  ፈሪሳውያን ግን ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላው ለምንድን ነው?” አሏቸው።+ 12  ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።+ 13  እንግዲያው ሄዳችሁ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’+ የሚለውን ቃል ትርጉም አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነውና።” 14  ከዚያም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እሱ መጥተው “እኛና ፈሪሳውያን ዘወትር ስንጾም የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።+ 15  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሙሽራው ጓደኞች ሙሽራው ከእነሱ ጋር እስካለ ድረስ የሚያዝኑበት ምን ምክንያት አለ?+ ሆኖም ሙሽራው ከእነሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤+ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። 16  በአሮጌ ልብስ ላይ ውኃ ያልነካው አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም፤ አዲሱ ጨርቅ ሲሸበሸብ ልብሱን ስለሚስበው ቀዳዳው የባሰ ይሰፋልና።+ 17  ደግሞም ሰዎች ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ አያስቀምጡም። እንዲህ ቢያደርጉ አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን ሰዎች አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጡት በአዲስ አቁማዳ ነው፤ በመሆኑም ሁለቱም ሳይበላሹ ይቆያሉ።” 18  ይህን እየነገራቸው ሳለ አንድ የምኩራብ አለቃ ወደ እሱ መጥቶ በመስገድ* “እስካሁን ልጄ ሳትሞት አትቀርም፤ ቢሆንም መጥተህ እጅህን ጫንባት፤ ዳግመኛም ሕያው ትሆናለች”+ አለው። 19  ኢየሱስም ተነስቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። 20  እነሆም፣ ለ12 ዓመት ደም ይፈሳት የነበረች አንዲት ሴት+ ከኋላ መጥታ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤+ 21  “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ታስብ ነበርና። 22  ኢየሱስ ወደ ኋላ ዞር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ አይዞሽ! እምነትሽ አድኖሻል” አላት።+ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ሴትየዋ ዳነች።+ 23  ኢየሱስ ወደ ምኩራብ አለቃው ቤት ሲደርስ ዋሽንት ነፊዎቹን እንዲሁም የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ+ 24  “እስቲ አንዴ ውጡ፤ ልጅቷ ተኝታለች+ እንጂ አልሞተችም” አለ። በዚህ ጊዜ በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። 25  ሕዝቡ ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዛት፤+ ልጅቷም ተነሳች።+ 26  ይህም ነገር በዚያ አገር ሁሉ በሰፊው ተወራ። 27  ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ ሲሄድ ሁለት ዓይነ ስውሮች+ “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልን” ብለው እየጮኹ ተከተሉት። 28  ወደ ቤት ከገባ በኋላ ዓይነ ስውሮቹ ወደ እሱ መጡ፤ ኢየሱስም “ዓይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።+ እነሱም “አዎ ጌታ ሆይ” ብለው መለሱለት። 29  ከዚያም ዓይናቸውን ዳስሶ+ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። 30  ዓይናቸውም በራ። ኢየሱስም “ማንም ሰው ስለዚህ ጉዳይ እንዳያውቅ ተጠንቀቁ” ሲል አጥብቆ አሳሰባቸው።+ 31  እነሱ ግን ከወጡ በኋላ በዚያ አካባቢ ሁሉ ስለ እሱ በይፋ አወሩ። 32  እነሱም ሲወጡ፣ ሰዎች ጋኔን ያደረበት ዱዳ ሰው ወደ እሱ አመጡ፤+ 33  ጋኔኑን ካስወጣለት በኋላ ዱዳው ተናገረ።+ ሕዝቡም እጅግ ተደንቀው “በእስራኤል ምድር እንዲህ ያለ ነገር ታይቶ አያውቅም” አሉ።+ 34  ፈሪሳውያን ግን “አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” ይሉ ነበር።+ 35  ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ በየከተማውና በየመንደሩ ይዞር ጀመር።+ 36  ሕዝቡንም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች+ ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።+ 37  ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “አዎ፣ አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው።+ 38  ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ኢየሱስ በገሊላ ሲያገለግል አብዛኛውን ጊዜ ይቀመጥባት የነበረችውን ቅፍርናሆም የተባለች ከተማ ያመለክታል።
ወይም “እጅ በመንሳት።”