ሕዝቅኤል 27:1-36

  • ስለሰመጠው የጢሮስ መርከብ የተነገረ ሙሾ (1-36)

27  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ በጢሮስ ላይ ሙሾ አውርድ፤*+  ጢሮስንም እንዲህ በላት፦‘አንቺ በባሕሩ መግቢያዎች ላይ የምትኖሪናበብዙ ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር የንግድ ልውውጥ የምታደርጊ፣ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጢሮስ ሆይ፣ አንቺ ራስሽ ‘ፍጹም ውብ ነኝ’ ብለሻል።+   ግዛትሽ በባሕሩ መካከል ነው፤የገነቡሽ ሰዎችም ውበትሽን ፍጹም አድርገውታል።   ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሰኒር*+ በመጣ የጥድ እንጨት ሠሩ፤ለአንቺም የመርከብ ምሰሶ ለመሥራት ከሊባኖስ፣ አርዘ ሊባኖስ አመጡ።   በባሳን የባሉጥ ዛፎች መቅዘፊያዎችሽን ሠሩ፤የፊተኛውን ክፍልሽንም ከኪቲም+ ደሴቶች በመጣ በዝሆን ጥርስ በተለበጠ የጥድ እንጨት ሠሩ።   ከግብፅ የመጣው የተለያየ ቀለም ያለው በፍታ የመርከብ ሸራሽን ለመሥራት አገልግሏል፤የላይኛው መድረክ መሸፈኛዎችሽም ከኤሊሻ+ ደሴቶች በመጣ ሰማያዊ ክርና ሐምራዊ ሱፍ የተሠሩ ናቸው።   ቀዛፊዎችሽ የሲዶና እና የአርዋድ+ ነዋሪዎች ነበሩ። ጢሮስ ሆይ፣ የገዛ ራስሽ ባለሙያዎች መርከበኞችሽ ነበሩ።+   ልምድ ያካበቱት* የጌባል+ ባለሙያዎች ስንጥቆችሽን ይደፍናሉ።+ በባሕር ላይ የሚጓዙ መርከቦችና ባሕረኞቻቸው ሁሉ ሸቀጣ ሸቀጦችን ለመገበያየት ወደ አንቺ ይመጡ ነበር። 10  የፋርስ፣ የሉድና የፑጥ+ ሰዎች ተዋጊዎች ሆነው በጦር ሠራዊትሽ ውስጥ ያገለግሉ ነበር። ጋሻቸውንና የራስ ቁራቸውን በአንቺ ውስጥ ሰቀሉ፤ ደግሞም ግርማ ሞገስ አጎናጸፉሽ። 11  በሠራዊትሽ ውስጥ ያሉት የአርዋድ ሰዎች በቅጥሮችሽ ላይ ዙሪያውን ቆመው ነበር፤ጀግኖችም በማማዎችሽ ላይ ነበሩ። ክብ የሆኑ ጋሻዎቻቸውን በቅጥሮችሽ ዙሪያ ሰቀሉ፤ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ። 12  “‘“ከተትረፈረፈው ውድ ሀብትሽ የተነሳ ተርሴስ+ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር።+ ሸቀጣ ሸቀጦችሽን በብር፣ በብረት፣ በቆርቆሮና በእርሳስ ይለውጡ ነበር።+ 13  ያዋን፣ ቱባልና+ መሼቅ+ ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር፤ ሸቀጦችሽን በባሪያዎችና በመዳብ ዕቃዎች ይለውጡ ነበር።+ 14  የቶጋርማ+ ሰዎች ደግሞ ሸቀጦችሽን በጭነት ፈረሶች፣ በጦር ፈረሶችና በበቅሎዎች ይለውጡ ነበር። 15  የዴዳን+ ሰዎች ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር፤ በብዙ ደሴቶች ላይ ነጋዴዎች ቀጠርሽ፤ የዝሆን ጥርስና+ ዞጲ* በግብር መልክ ያመጡልሽ ነበር። 16  ከምታመርቻቸው ዕቃዎች ብዛት የተነሳ ኤዶም ከአንቺ ጋር ትነግድ ነበር። ሸቀጦችሽን በበሉር፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ የተለያዩ ቀለማት ባላቸው ጥልፎች፣ ጥራት ባለው ልብስ፣ በዛጎልና በሩቢ ይለውጡ ነበር። 17  “‘“ይሁዳና የእስራኤል ምድር ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር፤ ሸቀጦችሽን በሚኒት+ ስንዴ፣ ምርጥ በሆኑ ምግቦች፣ በማር፣+ በዘይትና በበለሳን+ ይለውጡ ነበር።+ 18  “‘“ደማስቆ+ ከተትረፈረፈው ምርትሽና ከሀብትሽ የተነሳ ከአንቺ ጋር ትነግድ ነበር፤ የሄልቦን የወይን ጠጅና የዛሃር ሱፍ* ጨርቅ ትሸጥልሽ ነበር። 19  በዑዛል አቅራቢያ የሚገኙት ዌዳንና ያዋን ሸቀጦችሽን በሚተጣጠፍ ብረት፣ በብርጉድና* በጠጅ ሣር ይለውጡ ነበር። 20  ዴዳን፣+ በከብት ላይ ለመቀመጥ የሚያገለግል ግላስ* በማቅረብ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር። 21  የጠቦቶች፣ የአውራ በጎችና የፍየሎች+ ነጋዴ የሆኑ ዓረቦችንና የቄዳር+ አለቆችን ሁሉ ቀጠርሽ። 22  የሳባና የራአማ+ ነጋዴዎች ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር፤ ሸቀጦችሽን በሁሉም ዓይነት ምርጥ የሆኑ ሽቶዎች፣ የከበሩ ድንጋዮችና በወርቅ ይለውጡ ነበር።+ 23  ካራን፣+ ካኔህና ኤደን+ እንዲሁም የሳባ፣+ የአሹርና+ የኪልማድ ነጋዴዎች ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር። 24  በገበያ ቦታሽ ያማሩ ልብሶችን፣ በሰማያዊ ጨርቅና የተለያዩ ቀለማት ባለው ጥልፍ የተሠራን ካባ እንዲሁም ብዙ ዓይነት ቀለም ያላቸውን ምንጣፎች ይነግዱ የነበረ ሲሆን ሁሉም በገመድ በጥብቅ የታሰሩ ነበሩ። 25  የተርሴስ መርከቦች+ ሸቀጦችሽን ያጓጉዙልሽ ነበር፤በመሆኑም በባሕሩ መካከል በሀብት ተሞልተሽና ጭነት በዝቶልሽ* ነበር። 26  ቀዛፊዎችሽ ወደ ታላቅ ባሕር አምጥተውሻል፤የምሥራቁ ነፋስ በተንጣለለው ባሕር መካከል ሰባብሮሻል። 27  ውድቀት በሚደርስብሽ ቀን ሀብትሽ፣ ሸቀጦችሽ፣ የምትነግጃቸው ዕቃዎች፣ ባሕረኞችሽ፣ መርከበኞችሽ፣ስንጥቆችሽን የሚደፍኑልሽ ሰዎች፣ ነጋዴዎችሽና+ ተዋጊዎችሽ ሁሉ+ይኸውም በአንቺ ውስጥ ያለው ሕዝብ* ሁሉበተንጣለለው ባሕር መካከል ይሰምጣል።+ 28  መርከበኞችሽ ሲጮኹ የባሕሩ ጠረፍ ይናወጣል። 29  ቀዛፊዎቹ፣ ባሕረኞቹና መርከበኞቹ ሁሉከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ፤ መሬት ላይም ይቆማሉ። 30  በአንቺ የተነሳ በራሳቸው ላይ አቧራ እየነሰነሱና በአመድ ላይ እየተንከባለሉድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮኻሉ፤ ምርር ብለውም ያለቅሳሉ።+ 31  በአንቺ የተነሳ ራሳቸውን ይላጫሉ፣ ማቅ ይለብሳሉእንዲሁም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው * ያለቅሳሉ። 32  ለአንቺም በሚያለቅሱበት ጊዜ ሙሾ ያወርዳሉ፤ የሐዘን እንጉርጉሮም ያንጎራጉራሉ፦ ‘በባሕር መካከል ጸጥ እንዳለችው እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው?+ 33  ሸቀጥሽ ከተንጣለለው ባሕር በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝቦችን አጥግበሻል።+ የተትረፈረፈው ሀብትሽና ሸቀጣ ሸቀጥሽ የምድርን ነገሥታት አበልጽጓል።+ 34  አሁን ግን በተንጣለለው ባሕር ላይ ተሰባብረሽ ጥልቁ ውኃ ውስጥ ሰምጠሻል፤+ሸቀጥሽና ሕዝብሽ ሁሉ አብረውሽ ሰምጠዋል።+ 35  የደሴቶቹም ነዋሪዎች ሁሉ በመገረም አተኩረው ይመለከቱሻል፤+ነገሥታታቸውም በታላቅ ፍርሃት ይርዳሉ፤+ ፊታቸውም ይለዋወጣል። 36  በብሔራት መካከል ያሉ ነጋዴዎች በአንቺ ላይ ከደረሰው ነገር የተነሳ ያፏጫሉ። ፍጻሜሽ ድንገተኛና አስከፊ ይሆናል፤ደግሞም ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ትሆኛለሽ።’”’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ አሰማ።”
ዘዳ 3:8, 9 ላይ የተጠቀሰውን “የሄርሞን ተራራ” ያመለክታል።
ቃል በቃል “ሽማግሌዎቹ።”
በጣም ተፈላጊ የሆነ ጥቁር እንጨት። እንግሊዝኛ፣ ኢቦኒ።
ወይም “ቀላ ያለ ግራጫ ሱፍ።”
ከቀረፋ ዛፍ ጋር የሚዛመድ ዛፍ ነው።
ወይም “የተሸመነ የኮርቻ ልብስ።”
“ክብር ተላብሰሽ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ጉባኤ።”
ወይም “ከነፍሳቸው ምሬት የተነሳ።”