ሕዝቅኤል 18:1-32

  • እያንዳንዱ በገዛ ኃጢአቱ ይጠየቃል (1-32)

    • ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ ትሞታለች (4)

    • ልጅ በአባቱ ኃጢአት አይጠየቅም (19, 20)

    • በክፉዎች ሞት ደስ አይሰኝም (23)

    • ንስሐ መግባት ሕይወት ያስገኛል (27, 28)

18  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “በእስራኤል ምድር ‘ጎምዛዛ ወይን የበሉት አባቶች ሆነው ሳለ የልጆቹ ጥርስ ጠረሰ’ የሚለውን ምሳሌያዊ አባባል የምትጠቅሱት ምን ለማለት ነው?+  “‘በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ከእንግዲህ በእስራኤል ይህን ምሳሌ አትጠቅሱም።  እነሆ፣ ነፍስ* ሁሉ የእኔ ነው። የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች ሁሉ የልጅም ነፍስ የእኔ ናት። ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እሷ ትሞታለች።*  “‘አንድ ሰው ጻድቅ ነው እንበል፤ ይህ ሰው ፍትሐዊና ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋል።  በተራሮች ላይ ለጣዖት የተሠዋውን+ አይበላም፤ አስጸያፊ ወደሆኑት የእስራኤል ቤት ጣዖቶች* አይመለከትም፤ የባልንጀራውን ሚስት አያባልግም+ ወይም ከሴት ጋር በወር አበባዋ ጊዜ ግንኙነት አይፈጽምም፤+  ማንንም ሰው አይበድልም፤+ ይልቁንም ተበዳሪ መያዣ አድርጎ የሰጠውን ይመልሳል፤+ ማንንም ሰው አይዘርፍም፤+ ይልቁንም ለተራበ ሰው የራሱን ምግብ ይሰጣል፤+ እንዲሁም የተራቆተውን ያለብሰዋል፤+  ወለድ አይጠይቅም ወይም በአራጣ አያበድርም፤+ ይልቁንም ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም ይቆጠባል፤+ በሰዎች መካከል እውነተኛ ፍትሕ ያሰፍናል፤+  ያወጣኋቸውን ደንቦች ይከተላል፤ እንዲሁም በታማኝነት ይመላለስ ዘንድ ድንጋጌዎቼን ይጠብቃል። እንዲህ ያለው ሰው ጻድቅ ነው፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 10  “‘ይሁንና ይህ ሰው ዘራፊ+ ወይም ነፍሰ ገዳይ*+ የሆነ ወይም ከእነዚህ ነገሮች አንዱን የሚያደርግ ልጅ አለው እንበል፤ 11  (አባቱ ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱንም ባያደርግ እንኳ) ልጁ በተራሮች ላይ ለጣዖት የተሠዋውን ይበላል፤ የባልንጀራውን ሚስት ያባልጋል፤ 12  የተቸገረውንና ድሃውን ይበድላል፤+ ሰዎችን ይዘርፋል፤ መያዣ አድርጎ የወሰደውን አይመልስም፤ አስጸያፊ ወደሆኑት ጣዖቶች ይመለከታል፤+ ጸያፍ የሆኑ ልማዶችን ይፈጽማል፤+ 13  በአራጣ ያበድራል፤ እንዲሁም ወለድ ይቀበላል፤+ በመሆኑም ይህ ልጅ ፈጽሞ በሕይወት አይኖርም። እነዚህን ሁሉ አስጸያፊ ነገሮች በመሥራቱ በእርግጥ ይሞታል። ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል። 14  “‘ይሁንና አንድ አባት የተለያዩ ኃጢአቶች ሲሠራ ልጁ ይመለከተዋል እንበል፤ ልጁ ይህን ቢመለከትም እንዲህ ያሉ ነገሮች አይሠራም። 15  በተራሮች ላይ ለጣዖት የተሠዋውን አይበላም፤ አስጸያፊ ወደሆኑት የእስራኤል ቤት ጣዖቶች አይመለከትም፤ የባልንጀራውን ሚስት አያባልግም፤ 16  ማንንም ሰው አይበድልም፤ መያዣ እንዲሆን የተሰጠውን አይወስድም፤ ከሰው ላይ ምንም ነገር አይዘርፍም፤ ለተራበ ሰው የራሱን ምግብ ይሰጣል፤ እንዲሁም የተራቆተውን ያለብሰዋል፤ 17  ድሃውን ሰው ከመጨቆን ይቆጠባል፤ በአራጣ አያበድርም ወይም ወለድ አይጠይቅም፤ ድንጋጌዎቼንም ያከብራል፤ እንዲሁም ያወጣኋቸውን ደንቦች ይከተላል። እንዲህ ያለ ሰው አባቱ በፈጸመው በደል የተነሳ አይሞትም። በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። 18  አባቱ ግን የማጭበርበር ድርጊት በመፈጸሙ፣ ወንድሙን በመዝረፉና በሕዝቡ መካከል መጥፎ የሆነ ነገር በመሥራቱ በፈጸመው በደል የተነሳ ይሞታል። 19  “‘እናንተ ግን “ልጅ፣ አባቱ በሠራው በደል ተጠያቂ የማይሆነው ለምንድን ነው?” ትላላችሁ። ልጁ ፍትሐዊና ጽድቅ የሆነ ነገር ስላደረገ፣ ያወጣኋቸውን ደንቦች ሁሉ ስለጠበቀና በሥራ ላይ ስላዋለ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።+ 20  ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እሷ ትሞታለች።*+ ልጅ፣ አባቱ በሠራው በደል ተጠያቂ አይሆንም፤ አባትም ልጁ በሠራው በደል ተጠያቂ አይሆንም። የጻድቁ ሰው ጽድቅ የሚታሰብለት ለራሱ ብቻ ነው፤ የክፉውም ሰው ክፋት የሚታሰበው በራሱ ላይ ብቻ ነው።+ 21  “‘ክፉ ሰው ከሠራው ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ፣ ያወጣኋቸውን ደንቦች ቢጠብቅ እንዲሁም ፍትሐዊና ጽድቅ የሆነ ነገር ቢያደርግ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። ፈጽሞ አይሞትም።+ 22  ከሠራው በደል ውስጥ አንዱም አይታሰብበትም።*+ በሠራው ጽድቅ የተነሳ በሕይወት ይኖራል።’+ 23  “‘እኔ በክፉ ሰው ሞት ደስ እሰኛለሁ?’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘እኔ ደስ የምሰኘው ከመንገዱ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለም?’+ 24  “‘ይሁንና ጻድቅ ሰው ጽድቅ ማድረጉን ቢተውና መጥፎ* ነገር ቢፈጽም፣ ደግሞም ክፉው ሰው እንደሚያደርገው አስጸያፊ ነገሮችን ሁሉ ቢሠራ በሕይወት ይኖራል? ካከናወነው የጽድቅ ሥራ መካከል አንዱም አይታወስም።+ ታማኝነቱን በማጉደሉና ኃጢአት በመሥራቱ የተነሳ ይሞታል።+ 25  “‘ይሁንና እናንተ “የይሖዋ መንገድ ፍትሐዊ አይደለም” ትላላችሁ።+ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ እባካችሁ ስሙ! በእርግጥ መንገዴ ፍትሐዊ አይደለም?+ ይልቁንስ ፍትሐዊ ያልሆነው የእናንተ መንገድ አይደለም?+ 26  “‘ጻድቅ ሰው ጽድቅ ማድረጉን ቢተውና መጥፎ ነገር ቢፈጽም፣ በዚህም የተነሳ ቢሞት፣ የሚሞተው በገዛ ራሱ በደል ነው። 27  “‘ክፉ ሰው ከሠራው ክፉ ድርጊት ቢመለስና ፍትሐዊና ጽድቅ የሆነ ነገር ማድረግ ቢጀምር የራሱን ሕይወት* ያድናል።+ 28  የሠራውን በደል ሁሉ ተገንዝቦ ከዚያ ቢመለስ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። ፈጽሞ አይሞትም። 29  “‘ይሁንና የእስራኤል ቤት ሰዎች “የይሖዋ መንገድ ፍትሐዊ አይደለም” ይላሉ። የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በእርግጥ መንገዴ ፍትሐዊ አይደለም?+ ይልቁንስ ፍትሐዊ ያልሆነው የእናንተ መንገድ አይደለም?’ 30  “‘ስለዚህ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደየመንገዳችሁ እፈርዳለሁ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘ተመለሱ፤ አዎ፣ ተጠያቂ እንድትሆኑ የሚያደርግ የማሰናከያ ድንጋይ እንዳይሆንባችሁ ከሠራችሁት በደል ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተመለሱ። 31  የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ከራሳችሁ ላይ አስወግዱ፤+ ደግሞም አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ፤*+ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ለምን ትሞታላችሁ?’+ 32  “‘እኔ በማንም ሰው ሞት ደስ አልሰኝም’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሕይወት።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ኃጢአት የሚሠራ ሰው ይሞታል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ቃል በቃል “ደም አፍሳሽ።”
ወይም “ኃጢአት የሚሠራ ሰው ይሞታል።”
ቃል በቃል “አይታወስበትም።”
ወይም “ፍትሕ የጎደለው።”
ወይም “ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ለራሳችሁ ፍጠሩ።”