አንደኛ ሳሙኤል 5:1-12

  • ታቦቱ በፍልስጤማውያን ምድር (1-12)

    • ዳጎን ተዋረደ (1-5)

    • ፍልስጤማውያን በመቅሰፍት ተመቱ (6-12)

5  ፍልስጤማውያኑ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከማረኩ+ በኋላ ከኤቤንዔዘር ወደ አሽዶድ አመጡት።  እነሱም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት* አስገቡት፤ ከዳጎን+ አጠገብም አስቀመጡት።  በማግስቱም አሽዶዳውያን በማለዳ ሲነሱ ዳጎን በይሖዋ ታቦት ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት።+ በመሆኑም ዳጎንን አንስተው ወደ ቦታው መለሱት።+  በሚቀጥለውም ቀን ማለዳ ሲነሱ ዳጎን በይሖዋ ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። የዳጎን ራስና መዳፎቹም ተቆርጠው ደፉ ላይ ወድቀው ነበር። ባለበት የቀረው የዓሣው ክፍል ብቻ* ነበር።  እስከ ዛሬም ድረስ የዳጎን ካህናትና ወደ ዳጎን ቤት የሚገቡ ሁሉ በአሽዶድ የሚገኘውን የዳጎንን ደፍ የማይረግጡት ለዚህ ነው።  የይሖዋም እጅ በአሽዶዳውያን ላይ ከበደባቸው፤ እሱም አሽዶድንና ግዛቶቿን በኪንታሮት*+ በመምታት አጠፋቸው።  የአሽዶድ ሰዎች የተከሰተውን ነገር ሲያዩ “የእስራኤል አምላክ ታቦት በመካከላችን እንዲቆይ አታድርጉ፤ ምክንያቱም እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጨክኖብናል” አሉ።  በመሆኑም ሰዎችን ልከው የፍልስጤምን ገዢዎች በሙሉ በመሰብሰብ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን ብናደርገው ይሻላል?” ብለው ጠየቋቸው። እነሱም “የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት+ ይወሰድ” ሲሉ መለሱላቸው። ስለሆነም የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደዚያ ወሰዱት።  ታቦቱንም ወደዚያ ከወሰዱት በኋላ የይሖዋ እጅ በከተማዋ ላይ ሆነ፤ ታላቅ ሽብርም ለቀቀባቸው። እሱም የከተማዋን ሰዎች ከትንሽ እስከ ትልቅ መታቸው፤ ኪንታሮትም ወጣባቸው።+ 10  በመሆኑም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደ ኤቅሮን+ ላኩት፤ ሆኖም የእውነተኛው አምላክ ታቦት ኤቅሮን ሲደርስ ኤቅሮናውያን “እኛንም ሆነ ሕዝባችንን ለማስፈጀት የእስራኤልን አምላክ ታቦት ይኸው ወደ እኛ ደግሞ አመጡብን!” በማለት ይጮኹ ጀመር።+ 11  ከዚያም ሰዎችን ልከው የፍልስጤምን ገዢዎች በሙሉ በመሰብሰብ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ከዚህ አርቁልን፤ እኛም ሆንን ሕዝባችን እንዳናልቅ ወደ ቦታው እንዲመለስ አድርጉ” አሏቸው። ምክንያቱም መላ ከተማዋ በሞት ፍርሃት ተውጣ ነበር፤ የእውነተኛውም አምላክ እጅ በዚያ በጣም ከብዶ ነበር፤+ 12  ያልሞቱት ሰዎችም በኪንታሮት ተመቱ። ከተማዋ እርዳታ ለማግኘት የምታሰማው ጩኸትም ወደ ሰማይ ወጣ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ቃል በቃል “ዳጎን ብቻ።”
ወይም “በፊንጢጣ ኪንታሮት።”