ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 12:1-29

  • የእምነታችን ፍጹም አድራጊ የሆነው ኢየሱስ (1-3)

    • “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” (1)

  • “ይሖዋ የሚሰጥህን ተግሣጽ አቅልለህ አትመልከት” (4-11)

  • ‘እግራችሁ ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ አድርጉ’ (12-17)

  • ወደ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ቀርባችኋል’ (18-29)

12  እንግዲያው እንዲህ ያለ ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን ስላለልን እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት+ ከላያችን አንስተን እንጣል፤ ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫም በጽናት እንሩጥ፤+  የምንሮጠውም የእምነታችን “ዋና ወኪል”* እና “ፍጹም አድራጊ” የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት በመመልከት ነው።+ እሱ ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል፣ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት* ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል፤ እንዲሁም በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።+  እንግዲህ እንዳትደክሙና ተስፋ እንዳትቆርጡ*+ ኃጢአተኞች የራሳቸውን ጥቅም በመጻረር የሚያሰሙትን እንዲህ ዓይነቱን የተቃውሞ ንግግር በጽናት የተቋቋመውን+ እሱን በጥሞና አስቡ።  እናንተ ከዚህ ኃጢአት ጋር እያደረጋችሁ ባላችሁት ትግል ደማችሁ እስኪፈስ ድረስ ገና አልታገላችሁም።  ደግሞም ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን የተሰጣችሁን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሙሉ በሙሉ ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ* የሚሰጥህን ተግሣጽ አቅልለህ አትመልከት፤ በሚያርምህም ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ፤  ይሖዋ* የሚወዳቸውን ይገሥጻልና፤ እንዲያውም እንደ ልጁ አድርጎ የሚቀበለውን ሁሉ ይቀጣል።”*+  ተግሣጽ የምትቀበሉበት* አንዱ መንገድ ይህ ስለሆነ መከራ ሲደርስባችሁ መጽናት ያስፈልጋችኋል። አምላክ የያዛችሁ እንደ ልጆቹ አድርጎ ነው።+ ለመሆኑ አባቱ የማይገሥጸው ልጅ ማን ነው?+  ሆኖም ሁላችሁም ይህን ተግሣጽ ካልተቀበላችሁ ዲቃላዎች ናችሁ እንጂ ልጆች አይደላችሁም።  ከዚህም በላይ ሰብዓዊ አባቶቻችን ይገሥጹን ነበር፤ እኛም እናከብራቸው ነበር። ታዲያ የመንፈሳዊ ሕይወታችን አባት ለሆነው ይበልጥ በፈቃደኝነት በመገዛት በሕይወት ልንኖር አይገባም?+ 10  እነሱ መልካም መስሎ በታያቸው መንገድ ለጥቂት ጊዜ ገሥጸውናል፤ እሱ ግን ከቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን+ ለጥቅማችን ሲል ይገሥጸናል። 11  እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያስደስት አይመስልም፤ ይልቁንም ያስከፋል፤* በኋላ ግን በተግሣጽ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች የጽድቅን ሰላማዊ ፍሬ ያፈራላቸዋል። 12  ስለዚህ የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ፤+ 13  የተጎዳው የአካል ክፍል እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ እግራችሁ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ አድርጉ።+ 14  ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ፤+ ቅድስናንም ፈልጉ፤+ ያለቅድስና ማንም ሰው ጌታን ማየት አይችልም። 15  ማንም የአምላክን ጸጋ እንዳያጣ ብሎም መርዛማ ሥር በቅሎ ችግር እንዳይፈጥርና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ፤+ 16  በተጨማሪም በመካከላችሁ ሴሰኛ* ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ኤሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።+ 17  ኤሳው የኋላ ኋላ በረከቱን ለመውረስ በፈለገ ጊዜ እንደተከለከለ ታውቃላችሁና፤ ሐሳብ ለማስቀየር* እያለቀሰ ብርቱ ጥረት ቢያደርግም+ እንኳ አልተሳካለትም። 18  እናንተ እኮ የቀረባችሁት ሊዳሰስ ወደሚችለውና+ በእሳት ወደተያያዘው ተራራ፣+ ወደ ጥቁሩ ደመና፣ ወደ ድቅድቁ ጨለማ፣ ወደ አውሎ ነፋሱ፣+ 19  ወደ መለከት ድምፁና+ ቃል ያሰማ ወደነበረው ድምፅ+ አይደለም፤ ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ ሌላ ተጨማሪ ነገር እንዳይነገራቸው ለምነው ነበር።+ 20  “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለው ትእዛዝ በጣም አስፈርቷቸው ነበርና።+ 21  በተጨማሪም በዚያ ይታይ የነበረው ነገር በጣም አስፈሪ ስለነበረ ሙሴ “ፈራሁ፤ ተንቀጠቀጥኩም” ሲል ተናግሯል።+ 22  እናንተ ግን የቀረባችሁት ወደ ጽዮን ተራራና+ የሕያው አምላክ ከተማ ወደሆነችው ወደ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም፣+ አንድ ላይ ወደተሰበሰቡ አእላፋት* መላእክት፣ 23  በሰማያት ወደተመዘገበው የበኩራት ጉባኤ፣+ የሁሉ ፈራጅ ወደሆነው አምላክ፣+ ፍጽምና እንዲያገኙ ወደተደረጉት+ ጻድቃን መንፈሳዊ ሕይወት፣+ 24  የአዲስ ቃል ኪዳን+ መካከለኛ ወደሆነው ወደ ኢየሱስና+ ከአቤል ደም በተሻለ ሁኔታ ወደሚናገረው ወደተረጨው ደም ነው።+ 25  እየተናገረ ያለውን እሱን ከመስማት ወደኋላ እንዳትሉ* ተጠንቀቁ። በምድር ላይ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው የነበረውን ከመስማት ወደኋላ ያሉት ሰዎች ከቅጣት ካላመለጡ ታዲያ እኛ ከሰማይ የሚናገረውን እሱን ከመስማት ዞር ብንል እንዴት እናመልጣለን?+ 26  በዚያን ጊዜ ድምፁ ምድርን አናውጦ ነበር፤+ አሁን ግን “ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማይን ጭምር እንደገና አናውጣለሁ” ሲል ቃል ገብቷል።+ 27  እንግዲህ “እንደገና” የሚለው አባባል የማይናወጡት ነገሮች ጸንተው ይኖሩ ዘንድ የሚናወጡት ይኸውም የተሠሩት ነገሮች የሚወገዱ መሆናቸውን ያመለክታል። 28  ስለዚህ እኛ ሊናወጥ የማይችል መንግሥት ልንቀበል እንደሆነ ስለምናውቅ ጸጋውን መቀበላችንን እንቀጥል፤ ይህም በጸጋው አማካኝነት በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት፣ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንችል ዘንድ ነው። 29  አምላካችን የሚባላ እሳት ነውና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ዋና መሪ።”
ወይም “በነፍሳችሁ እንዳትዝሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ይገርፋል።”
ወይም “ሥልጠና የምታገኙበት።”
ወይም “ያሳዝናል።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
የአባቱን ሐሳብ ለማስቀየር ማለት ነው።
ወይም “በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ።”
ወይም “ላለመስማት ሰበብ እንዳትፈጥሩ፤ ከመስማት ቸል እንዳትሉ።”