የማርቆስ ወንጌል 14:1-72

  • ካህናት ኢየሱስን ለመግደል አሴሩ (1, 2)

  • አንዲት ሴት ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ኢየሱስ ላይ አፈሰሰች (3-9)

  • ይሁዳ ኢየሱስን ከዳው (10, 11)

  • የመጨረሻው ፋሲካ (12-21)

  • የጌታ ራት ተቋቋመ (22-26)

  • ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንደሚክደው ተናገረ (27-31)

  • ኢየሱስ በጌትሴማኒ ጸለየ (32-42)

  • ኢየሱስ ተያዘ (43-52)

  • በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ለፍርድ ቀረበ (53-65)

  • ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው (66-72)

14  ፋሲካና*+ የቂጣ* በዓል+ ሁለት ቀን ቀርቶት ነበር።+ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት የተንኮል ዘዴ ተጠቅመው እሱን የሚይዙበትንና* የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፤+  ደግሞም “ሕዝቡ ሁከት ሊያስነሳ ስለሚችል በበዓሉ ወቅት መሆን የለበትም” ይሉ ነበር።  በቢታንያ፣ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በነበረው በስምዖን ቤት እየበላ ሳለ አንዲት ሴት እጅግ ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ይኸውም ንጹሕ ናርዶስ የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች። ብልቃጡንም ሰብራ በመክፈት ዘይቱን ራሱ ላይ ታፈስ ጀመር።+  በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ተቆጥተው እንዲህ ተባባሉ፦ “ይህ ዘይት እንዲህ የሚባክነው ለምንድን ነው?  ከ300 ዲናር* በላይ ተሸጦ ገንዘቡ ለድሆች ሊሰጥ ይችል ነበር!” በሴትየዋም እጅግ ተበሳጩ።*  ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “ተዉአት። ለምን ታስቸግሯታላችሁ? እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች።+  ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤+ በፈለጋችሁ ጊዜ ሁሉ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፤ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።+  እሷ የምትችለውን አድርጋለች፤ ሰውነቴን ለቀብሬ ለማዘጋጀት ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት አስቀድማ ቀብታዋለች።+  እውነት እላችኋለሁ፣ በመላው ዓለም ምሥራቹ በሚሰበክበት+ ቦታ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውም መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”+ 10  ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።+ 11  እነሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸውና የብር ገንዘብ* ሊሰጡት ቃል ገቡለት።+ ስለዚህ እሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን አጋጣሚ ይፈልግ ጀመር። 12  የቂጣ በዓል+ በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፣ እንደተለመደው የፋሲካን መሥዋዕት+ በሚያቀርቡበት ዕለት ደቀ መዛሙርቱ “ፋሲካን እንድትበላ የት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።+ 13  እሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፦ “ወደ ከተማው ሂዱ፤ በዚያም የውኃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ። እሱንም ተከተሉት፤+ 14  ወደሚገባበት ቤት ሄዳችሁ የቤቱን ጌታ ‘መምህሩ “ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የት ነው?” ብሏል’ በሉት። 15  እሱም የተነጠፈና የተሰናዳ ሰፊ ሰገነት ያሳያችኋል። እዚያ አዘጋጁልን።” 16  ደቀ መዛሙርቱም ሄዱ፤ ወደ ከተማውም ገቡ፤ እንዳላቸውም ሆኖ አገኙት፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ። 17  እሱም ከመሸ በኋላ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ።+ 18  በማዕድ ተቀምጠው እየበሉ ሳለም ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ፣ ከእኔ ጋር እየበላ ያለ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ።+ 19  እነሱም አዝነው በየተራ “እኔ እሆን?” ይሉት ጀመር። 20  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይኸውም ከእኔ ጋር በሳህኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው።+ 21  የሰው ልጅ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት!+ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።”+ 22  እየበሉም ሳሉ ቂጣ አንስቶ ባረከ፤ ከቆረሰውም በኋላ ሰጣቸውና “እንኩ፣ ይህ ሥጋዬን ያመለክታል” አለ።+ 23  ጽዋ አንስቶም አምላክን ካመሰገነ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከእሱ ጠጡ።+ 24  እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ለብዙዎች የሚፈሰውን+ ‘የቃል ኪዳን+ ደሜን’+ ያመለክታል። 25  እውነት እላችኋለሁ፣ በአምላክ መንግሥት አዲሱን ወይን እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ በኋላ ከዚህ ወይን አልጠጣም።” 26  በመጨረሻ የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ።+ 27  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “‘እረኛውን እመታለሁ፤+ በጎቹም ይበተናሉ’+ ተብሎ ስለተጻፈ ሁላችሁም ትሰናከላላችሁ። 28  ከተነሳሁ በኋላ ግን ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”+ 29  ይሁንና ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለው።+ 30  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ፦ ዛሬ፣ አዎ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።+ 31  እሱ ግን “አብሬህ መሞት ቢኖርብኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” በማለት አጥብቆ ይናገር ጀመር። የቀሩትም ሁሉ እንደዚሁ አሉ።+ 32  ከዚያም ጌትሴማኒ ወደተባለ ቦታ መጡ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “እኔ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።+ 33  ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ከእሱ ጋር ይዟቸው ሄደ፤+ ከዚያም እጅግ ይጨነቅና* ይረበሽ ጀመር። 34  ኢየሱስም “እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ።*+ እዚህ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ”+ አላቸው። 35  ትንሽ ወደ ፊት ራቅ በማለት መሬት ላይ ተደፍቶ ቢቻል ሰዓቱ ከእሱ እንዲያልፍ ይጸልይ ጀመር። 36  እንዲህም አለ፦ “አባ፣* አባት ሆይ፣+ አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ ትችላለህ፤ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ሆኖም እኔ የምፈልገው ሳይሆን አንተ የምትፈልገው ይሁን።”+ 37  ተመልሶ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸውና ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ስምዖን፣ ተኝተሃል? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አልቻልክም?+ 38  ወደ ፈተና እንዳትገቡ+ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ። እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ* ነው፤ ሥጋ* ግን ደካማ ነው።”+ 39  እንደገናም ሄዶ ስለዚያው ነገር ጸለየ።+ 40  ዳግመኛም ተመልሶ ሲመጣ እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ስለነበር ተኝተው አገኛቸው፤ በመሆኑም የሚሉት ነገር ጠፋቸው። 41  ለሦስተኛ ጊዜም ተመልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው? በቃ! ሰዓቱ ደርሷል!+ እነሆ፣ የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች አልፎ ሊሰጥ ነው። 42  ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”+ 43  ወዲያውም ገና እየተናገረ ሳለ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆች፣ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።+ 44  አሳልፎ የሚሰጠውም “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙትና እንዳያመልጥ ተጠንቅቃችሁ ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። 45  ይሁዳም በቀጥታ መጥቶ ወደ እሱ በመቅረብ “ረቢ!” ብሎ ሳመው። 46  ሰዎቹም ያዙት፤ ደግሞም አሰሩት። 47  ይሁን እንጂ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው።+ 48  ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው?+ 49  በየዕለቱ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ+ ከእናንተ ጋር ነበርኩ፤ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም። ይሁንና ይህ የሆነው ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።”+ 50  በዚህ ጊዜ ሁሉም ጥለውት ሸሹ።+ 51  ሆኖም እርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት በቅርብ ርቀት ይከተለው ጀመር፤ ሊይዙትም ሞከሩ፤ 52  እሱ ግን በፍታውን ትቶ ራቁቱን* አመለጠ። 53   ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤+ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍትም በሙሉ ተሰበሰቡ።+ 54  ይሁንና ጴጥሮስ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በርቀት ተከተለው፤ ከዚያም ከቤቱ አገልጋዮች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ጀመር።+ 55  በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የምሥክሮች ቃል እየፈለጉ ነበር፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።+ 56  እርግጥ ብዙዎች በእሱ ላይ የሐሰት ምሥክርነት ይሰጡ ነበር፤+ ሆኖም ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም። 57   አንዳንዶችም ተነስተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት ይመሠክሩበት ነበር፦ 58  “‘ይህን በእጅ የተሠራ ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ በእጅ ያልተሠራ ሌላ እገነባለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።”+ 59  በዚህ ጉዳይም ቢሆን የምሥክርነት ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም። 60  ከዚያም ሊቀ ካህናቱ በመካከላቸው ቆሞ ኢየሱስን “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” ሲል ጠየቀው።+ 61  እሱ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም።+ ሊቀ ካህናቱም እንደገና “አንተ ብሩክ የሆነው አምላክ ልጅ ክርስቶስ ነህ?” እያለ ይጠይቀው ጀመር። 62  ኢየሱስም “አዎ ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ+ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ+ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ”+ አለ። 63  በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ እንዲህ አለ፦ “ከዚህ በላይ ምን ምሥክሮች ያስፈልጉናል?+ 64  አምላክን ሲሳደብ ሰምታችኋል። ታዲያ ውሳኔያችሁ ምንድን ነው?”* ሁሉም ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።+ 65  አንዳንዶች ይተፉበት ጀመር፤+ ፊቱንም ሸፍነው በቡጢ እየመቱት “ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደመታህ ንገረን!” ይሉት ነበር። የሸንጎው አገልጋዮችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።+ 66  ጴጥሮስ ግቢው ውስጥ በታች በኩል ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ሴት አገልጋዮች አንዷ መጣች።+ 67  እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከዚህ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። 68  እሱ ግን “ሰውየውን አላውቀውም፤ ምን እንደምታወሪም አላውቅም” ሲል ካደ፤ ከዚያም ወደ መግቢያው* ሄደ። 69  አገልጋይዋም እዚያ አየችውና በአጠገቡ ለቆሙት “ይህ ከእነሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ትናገር ጀመር። 70  አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በዚያ ቆመው የነበሩት ጴጥሮስን እንደገና “የገሊላ ሰው ስለሆንክ፣ በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” ይሉት ጀመር። 71  እሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” ሲል ይምልና ራሱን ይረግም ጀመር። 72  ወዲያውኑ ዶሮ ለሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤+ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው።+ ከዚያም እጅግ አዝኖ ያለቅስ ጀመር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሚያስሩበትንና።”
ወይም “የማለፍ በዓልና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሴትየዋን ተቆጧት፤ ነቀፏት።”
ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።
ወይም “ይደነግጥና።”
ወይም “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች።”
“አባት ሆይ!” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ወይም የአረማይክ ቃል ነው።
ወይም “ፈቃደኛ።”
የሰው ልጅ ኃጢአተኛና ፍጽምና የጎደለው መሆኑን ያመለክታል።
ወይም “ከውስጥ በለበሳት ልብስ ብቻ።”
ወይም “ምን ይመስላችኋል?”
ወይም “መተላለፊያው።”