አንደኛ ነገሥት 8:1-66

  • ታቦቱን ቤተ መቅደሱ ውስጥ አስቀመጡት (1-13)

  • ሰለሞን ለሕዝቡ ንግግር አቀረበ (14-21)

  • ሰለሞን ቤተ መቅደሱ ሲወሰን ያቀረበው ጸሎት (22-53)

  • ሰለሞን ሕዝቡን ባረከ (54-61)

  • የቀረቡት መሥዋዕቶችና የውሰናው በዓል (62-66)

8  በዚህ ጊዜ ሰለሞን የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የነገዶቹን መሪዎች ሁሉና የእስራኤልን የአባቶች ቤት አለቆች+ ሰበሰበ።+ እነሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ+ ማለትም ከጽዮን+ ለማምጣት በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ ንጉሥ ሰለሞን መጡ።  የእስራኤል ሰዎች በሙሉ በሰባተኛው ወር ማለትም በኤታኒም* ወር በሚከበረው በዓል* ላይ ንጉሥ ሰለሞን ፊት ተሰበሰቡ።+  የእስራኤል ሽማግሌዎችም በሙሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሱ።+  የይሖዋን ታቦት፣ የመገናኛ ድንኳኑንና+ በድንኳኑ ውስጥ የነበሩትን ቅዱስ ዕቃዎች በሙሉ አመጡ። እነዚህንም ያመጡት ካህናቱና ሌዋውያኑ ናቸው።  ንጉሥ ሰለሞንና ወደ እሱ እንዲመጣ የተጠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ታቦቱ ፊት ነበሩ። ከብዛታቸው የተነሳ ሊቆጠሩ የማይችሉ ብዙ በጎችና ከብቶች መሥዋዕት ሆነው ቀረቡ።+  ከዚያም ካህናቱ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት አምጥተው ቦታው+ ላይ ማለትም በቤቱ ውስጠኛ ክፍል ይኸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቦቹ ክንፎች በታች አስቀመጡት።+  የኪሩቦቹ ክንፎች ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ተዘርግተው ስለነበር ኪሩቦቹ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ከላይ ከልለዋቸው ነበር።+  መሎጊያዎቹ+ ረጅም ስለነበሩ የመሎጊያዎቹን ጫፎች ከውስጠኛው ክፍል ፊት ለፊት ባለው በቅድስቱ ውስጥ ሆኖ ማየት ይቻል ነበር፤ ከውጭ ግን አይታዩም ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ።  የእስራኤል ሰዎች ከግብፅ ምድር ሲወጡ+ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባበት ጊዜ+ ሙሴ በኮሬብ ታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው+ ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች+ በስተቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም። 10  ካህናቱ ከቅዱሱ ስፍራ በወጡ ጊዜ ደመናው+ የይሖዋን ቤት ሞላው።+ 11  የይሖዋ ክብር የይሖዋን ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ከደመናው የተነሳ በዚያ ቆመው ማገልገል አልቻሉም።+ 12  በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ በድቅድቅ ጨለማ+ ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል። 13  እኔም እጅግ ከፍ ያለ ቤት፣ ለዘላለም የምትኖርበት ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ+ ገንብቼልሃለሁ።” 14  ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ቆሞ ሳለ ንጉሡ ዞሮ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መባረክ ጀመረ።+ 15  እንዲህም አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ እንዲህ ብሎ ቃል የገባውና ይህን በራሱ እጅ የፈጸመው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ፦ 16  ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ዕለት አንስቶ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስሜ የሚጠራበት ቤት እንዲሠራበት አንድም ከተማ አልመረጥኩም፤+ ዳዊትን ግን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዢ እንዲሆን መረጥኩ።’ 17  አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት ከልቡ ተመኝቶ ነበር።+ 18  ሆኖም ይሖዋ አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት ከልብህ ተመኝተህ ነበር፤ ይህን በልብህ መመኘትህም መልካም ነው። 19  ይሁንና ቤቱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ሆኖም ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ የሚወለድልህ የገዛ ልጅህ* ይሆናል።’+ 20  ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል፤ ልክ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት አባቴን ዳዊትን ተክቼ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁና። በተጨማሪም ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ሠርቻለሁ፤+ 21  እንዲሁም አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ይሖዋ ከእነሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የያዘው ታቦት+ የሚያርፍበትን ቦታ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።” 22  ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ መሠዊያ ፊት፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ለፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤+ 23  እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በፊቱ በሙሉ ልባቸው ለሚመላለሱ+ አገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር+ የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ አምላክ በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር የለም።+ 24  ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቀሃል። በገዛ አፍህ ቃል ገባህ፤ ዛሬ ደግሞ በራስህ እጅ ፈጸምከው።+ 25  አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ ‘አንተ በፊቴ እንደተመላለስከው ሁሉ ልጆችህም በጥንቃቄ በፊቴ ከተመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከፊቴ ፈጽሞ አይታጣም’ በማለት ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቅ።+ 26  አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ እባክህ ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም። 27  “በእርግጥ አምላክ በምድር ላይ ይኖራል?+ እነሆ ሰማያት፣ አዎ ሰማየ ሰማያት እንኳ ሊይዙህ አይችሉም፤+ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤትማ ምንኛ ያንስ!+ 28  እንግዲህ አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመና በትኩረት ስማ፤ አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰማውን ጩኸትና በዛሬው ዕለት በፊትህ የሚያቀርበውን ጸሎት አዳምጥ። 29  አገልጋይህ ወደዚህ ስፍራ የሚያቀርበውን ጸሎት ለመስማት ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’+ ወዳልከው ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ቀንና ሌሊት ይመልከቱ።+ 30  አገልጋይህ ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመናና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በመጸለይ የሚያቀርበውን ልመና አዳምጥ፤ በሰማያት ባለው ማደሪያህ ሆነህ ስማ፤+ ሰምተህም ይቅር በል።+ 31  “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ እንዲምል ቢደረግ፣* በመሐላውም* ተጠያቂ ቢሆን፣ በዳዩም በዚህ መሐላ* ሥር ሆኖ እዚህ ቤት ውስጥ ባለው መሠዊያህ ፊት ቢቀርብ፣+ 32  አንተ በሰማያት ሆነህ ስማ፤ ክፉውን ጥፋተኛ* በማለትና እንደ ሥራው በመመለስ፣ ጻድቁንም ንጹሕ* መሆኑን በማሳወቅና እንደ ጽድቁ ወሮታውን በመክፈል እርምጃ ውሰድ፤ አገልጋዮችህንም ዳኝ።+ 33  “ሕዝብህ እስራኤላውያን አንተን ከመበደላቸው የተነሳ በጠላት ድል ቢነሱና+ ወደ አንተ ተመልሰው ስምህን ቢያወድሱ+ እንዲሁም በዚህ ቤት ወደ አንተ ቢጸልዩና ሞገስ ለማግኘት ልመና ቢያቀርቡ+ 34  ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደሰጠኸው ምድርም መልሳቸው።+ 35  “ሕዝቡ አንተን በመበደሉ የተነሳ+ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ቢጠፋ፣+ እነሱም አንተ ስላዋረድካቸው* ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢያወድሱ እንዲሁም ከኃጢአታቸው ቢመለሱ+ 36  ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የአገልጋዮችህን፣ የሕዝብህን የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር በል፤ ስለሚሄዱበት ቀና መንገድ ታስተምራቸዋለህና፤+ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ ባወረስከው ምድርህም ላይ ዝናብ አዝንብ።+ 37  “በምድሪቱ ላይ ረሃብ+ ወይም ቸነፈር፣ የሚለበልብና የሚያደርቅ ነፋስ ወይም ዋግ+ ቢከሰት፣ የአንበጣ መንጋ ወይም የማይጠግብ አንበጣ* ቢመጣ አሊያም ጠላቶቻቸው በምድሪቱ ላይ ባለ በየትኛውም ከተማ* ውስጥ ሳሉ ቢከቧቸው ወይም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት አሊያም ማንኛውም ዓይነት በሽታ ቢከሰትና+ 38  ማንኛውም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል በሙሉ (እያንዳንዱ የልቡን ጭንቀት ያውቃልና)+ ወደ አንተ ለመጸለይ ወይም ሞገስ እንድታሳየው ልመና+ ለማቅረብ እጁን ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ 39  አንተ ከመኖሪያ ቦታህ+ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ ደግሞም ይቅር በል፤+ እርምጃም ውሰድ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ብድራቱን ክፈለው፤+ ምክንያቱም አንተ ልቡን ታውቃለህ (የሰውን ልብ በሚገባ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ)፤+ 40  ይህም ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ አንተን እንዲፈሩ ነው። 41  “በተጨማሪም ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ የባዕድ አገር ሰው በስምህ* የተነሳ ከሩቅ አገር ቢመጣ፣+ 42  (መቼም ስለ ታላቁ ስምህ፣+ ስለ ኃያሉ እጅህና ስለተዘረጋው ክንድህ መስማታቸው አይቀርም) ወደዚህም ቤት መጥቶ ቢጸልይ 43  ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት+ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ስምህን እንዲያውቁና እንዲፈሩህ+ እንዲሁም ስምህ እኔ በሠራሁት በዚህ ቤት እንደሚጠራ እንዲያውቁ ያ የባዕድ አገር ሰው የጠየቀህን ሁሉ ፈጽምለት። 44  “ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ለጦርነት ቢወጡና+ አንተ ወደመረጥከው ከተማ+ እንዲሁም ለስምህ ወደሠራሁት ቤት አቅጣጫ+ ወደ ይሖዋ ቢጸልዩ+ 45  ከሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና ስማ፤ ፍረድላቸውም። 46  “በአንተ ላይ ኃጢአት ቢሠሩ (መቼም ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለም)፣+ አንተም በእነሱ እጅግ ተቆጥተህ ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ ጠላቶቻቸውም ራቅ ወዳለ ወይም ቅርብ ወደሆነ የጠላት ምድር ምርኮኛ አድርገው ቢወስዷቸው+ 47  እነሱም በምርኮ በተወሰዱበት ምድር ወደ ልቦናቸው ቢመለሱና+ ወደ አንተ ዞር በማለት+ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ አጥፍተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’+ በማለት በተማረኩበት ምድር+ ሆነው ሞገስ ለማግኘት ወደ አንተ ልመና ቢያቀርቡ፣ 48  ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቻቸውም ምድር ሆነው በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው* ወደ አንተ ቢመለሱ+ እንዲሁም ለአባቶቻቸው በሰጠሃቸው ምድር፣ አንተ በመረጥካት ከተማና ለስምህ በሠራሁት ቤት አቅጣጫ ወደ አንተ ቢጸልዩ+ 49  ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት ያቀረቡትን ልመና ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ+ ስማ፤ ፍረድላቸውም፤ 50  በአንተ ላይ የፈጸሙትን በደል ሁሉ ይቅር በማለት በአንተ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሕዝብህን ይቅር በል። የማረኳቸውም ሰዎች እንዲያዝኑላቸው ታደርጋለህ፤ እነሱም ያዝኑላቸዋል+ 51  (ምክንያቱም እነሱ እንደ ብረት ማቅለጫ+ ከሆነችው ከግብፅ ያወጣሃቸው+ ሕዝቦችህና ርስትህ+ ናቸው)። 52  አገልጋይህም ሆነ ሕዝብህ እስራኤል ወደ አንተ በሚጮኹበት ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤ ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትንም ልመና+ ዓይኖችህ ይመልከቱ።+ 53   ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አባቶቻችንን ከግብፅ ባወጣሃቸው ጊዜ በአገልጋይህ በሙሴ በኩል በተናገርከው መሠረት ከምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ርስትህ አድርገህ ለይተሃቸዋልና።”+ 54  ሰለሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ወደ ይሖዋ አቅርቦ እንደጨረሰ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ ከተንበረከከበት ከይሖዋ መሠዊያ ፊት ተነሳ።+ 55  ከዚያም ቆሞ የእስራኤልን ጉባኤ በሙሉ ጮክ ብሎ እንዲህ ሲል ባረከ፦ 56  “በገባው ቃል መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል የእረፍት ቦታ የሰጠው ይሖዋ ይወደስ።+ በአገልጋዩ በሙሴ አማካኝነት ከሰጠው መልካም ተስፋ ሁሉ መካከል ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም።+ 57   አምላካችን ይሖዋ ከአባቶቻችን ጋር እንደነበረ ሁሉ ከእኛም ጋር ይሁን።+ አይተወን፤ ደግሞም አይጣለን።+ 58  በመንገዱ ሁሉ እንድንሄድ እንዲሁም አባቶቻችን እንዲጠብቁ ያዘዛቸውን ትእዛዛቱን፣ ሥርዓቱንና ድንጋጌዎቹን እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እሱ ያዘንብል።+ 59  ሞገስ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ያቀረብኩት ይህ ልመና በአምላካችን በይሖዋ ፊት ቀንና ሌሊት ይታወስ፤ ለአገልጋዩና ለሕዝቡ ለእስራኤልም በየዕለቱ የሚያስፈልገውን ፍርድ ይፍረድላቸው፤ 60  ይህም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ መሆኑን እንዲያውቁ ነው።+ ከእሱ ሌላ ማንም የለም!+ 61  በመሆኑም እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ በአምላካችን በይሖዋ ሥርዓቶች በመሄድና ትእዛዛቱን በመጠበቅ ልባችሁ በእሱ ዘንድ ሙሉ ይሁን።”*+ 62  ከዚያም ንጉሡና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ በይሖዋ ፊት ታላቅ መሥዋዕት አቀረቡ።+ 63  ሰለሞን 22,000 ከብቶችና 120,000 በጎች ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕት+ አድርጎ አቀረበ። በዚህ መንገድ ንጉሡና እስራኤላውያን በሙሉ የይሖዋን ቤት መረቁ።+ 64  ንጉሡም በዚያ ቀን በይሖዋ ቤት ፊት የሚገኘውን የግቢውን መሃል መቀደስ አስፈልጎት ነበር፤ ምክንያቱም የሚቃጠሉትን መሥዋዕቶች፣ የእህል መባዎቹንና የኅብረት መሥዋዕቶቹን በዚያ ማቅረብ ነበረበት፤ ይህም የሆነው በይሖዋ ፊት ያለው የመዳብ መሠዊያ+ የሚቃጠሉትን መሥዋዕቶች፣ የእህል መባዎቹንና የኅብረት መሥዋዕቶቹን ስብ+ መያዝ ስላልቻለ ነው። 65  በዚያ ጊዜ ሰለሞን ከመላው እስራኤል ጋር ይኸውም ከሌቦሃማት* አንስቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ*+ ድረስ ካለው ምድር ከመጣው ታላቅ ጉባኤ ጋር በመሆን በአምላካችን በይሖዋ ፊት ለ7 ቀን፣ ከዚያም ለተጨማሪ 7 ቀን በአጠቃላይ ለ14 ቀን በዓሉን አከበረ።+ 66  በቀጣዩም* ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ እነሱም ንጉሡን ባረኩ፤ ይሖዋ ለአገልጋዩ ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባሳየው ጥሩነት ሁሉ እየተደሰቱና ከልባቸው እየፈነደቁ+ ወደየቤታቸው ሄዱ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
የዳስ በዓልን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ።”
ወይም “ባልንጀራው በእርግማን ሥር ቢያደርገው።” ግለሰቡ የማለው በውሸት ከሆነ ወይም መሐላውን ከጣሰ እርግማኑ እንደ ቅጣት እንደሚደርስበት ያመለክታል።
ቃል በቃል “በእርግማኑም።”
ቃል በቃል “እርግማን።”
ቃል በቃል “ክፉ።”
ቃል በቃል “ጻድቅ።”
ወይም “ስላጎሳቆልካቸው።”
ወይም “ፌንጣ።”
ቃል በቃል “በበሮቹ ምድር።”
ወይም “በዝናህ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለእሱ ያደረ ይሁን።”
ወይም “ከሃማት መግቢያ።”
ቃል በቃል “በስምንተኛውም።” ከተጨማሪው ሰባት ቀን በኋላ ያለውን ቀን ያመለክታል።