ዘሌዋውያን 10:1-20

  • ናዳብንና አቢሁን እሳት ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በላቸው (1-7)

  • ምግብና መጠጥን አስመልክቶ ለካህናቱ የተሰጡ ሕጎች (8-20)

10  በኋላም የአሮን ወንዶች ልጆች ናዳብና አቢሁ+ እያንዳንዳቸው የዕጣን ማጨሻቸውን አምጥተው በላዩ ላይ እሳት አደረጉበት፤ በእሳቱም ላይ ዕጣን ጨመሩበት።+ ከዚያም ይሖዋ እንዲያደርጉ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደ እሳት+ በፊቱ አቀረቡ። 2  በዚህ ጊዜ እሳት ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በላቸው፤+ እነሱም በይሖዋ ፊት ሞቱ።+ 3  ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡ ሰዎች መካከል እቀደሳለሁ፤+ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከበራለሁ’ ብሏል።” አሮንም ዝም አለ። 4  ሙሴም የአሮን አጎት የዑዚኤል+ ልጆች የሆኑትን ሚሳኤልንና ኤሊጻፋንን ጠርቶ “ኑ፣ ወንድሞቻችሁን ከቅዱሱ ስፍራ ፊት ለፊት አንስታችሁ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ቦታ አውጧቸው” አላቸው። 5  ስለዚህ መጥተው ልክ ሙሴ በነገራቸው መሠረት ሟቾቹን ከነቀሚሳቸው ተሸክመው ከሰፈሩ ውጭ አወጧቸው። 6  ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲሁም ሌሎቹን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እንዳትሞቱ እንዲሁም አምላክ በመላው ማኅበረሰብ ላይ እንዳይቆጣ ፀጉራችሁን አታንጨብርሩ ወይም ልብሶቻችሁን አትቅደዱ።+ ሆኖም ወንድሞቻችሁ ይኸውም መላው የእስራኤል ቤት ይሖዋ በእሳት ለገደላቸው ያለቅሱላቸዋል። 7  የይሖዋ የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ላይ ስላለ ከመገናኛ ድንኳኑ ደጃፍ መራቅ የለባችሁም፤+ አለዚያ ትሞታላችሁ።” እነሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ። 8  ከዚያም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ 9  “እንዳትሞቱ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ስትገቡ አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶች ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ።+ ይህ ትእዛዝ ለትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላለማዊ ደንብ ነው። 10  ይህም ቅዱስ የሆነውን ከረከሰው ነገር እንዲሁም ንጹሕ ያልሆነውን ንጹሕ ከሆነው ነገር ለመለየት+ 11  እንዲሁም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸውን ሥርዓቶች በሙሉ ለእስራኤላውያን ለማስተማር ነው።”+ 12  ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲሁም የተረፉትን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች የተረፈውን የእህል መባ ወስዳችሁ ያለእርሾ በማዘጋጀት በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤+ ምክንያቱም ይህ እጅግ ቅዱስ ነገር ነው።+ 13  ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች ላይ ይህ የአንተ ድርሻና የወንዶች ልጆችህ ድርሻ ስለሆነ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ብሉት፤+ ምክንያቱም እንዲህ እንዳደርግ ታዝዣለሁ። 14  እንዲሁም የሚወዘወዘውን መባ ፍርምባና የቅዱሱን ድርሻ+ እግር አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ንጹሕ በሆነ ስፍራ ትበሉታላችሁ፤+ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች እስራኤላውያን ከሚያቀርቧቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ላይ የአንተ ድርሻና የወንዶች ልጆችህ ድርሻ ሆነው የተሰጡ ናቸው። 15  እነሱም የቅዱሱን ድርሻ እግርና የሚወዘወዘውን መባ ፍርምባ በእሳት ከሚቀርቡት የስብ መባዎች ጋር ያመጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉት የሚወዘወዘውን መባ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ለመወዝወዝ ነው፤ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረትም ይህ ለአንተና ከአንተ ጋር ላሉት ወንዶች ልጆችህ ዘላለማዊ ድርሻ ሆኖ ያገለግላል።”+ 16  ሙሴም ለኃጢአት መባ የሚሆነውን ፍየል በደንብ አፈላለገ፤+ በኋላም ፍየሉ መቃጠሉን ተረዳ። በመሆኑም የተረፉትን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቆጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ 17  “ይህ መባ እጅግ ቅዱስ ነገር ሆኖ ሳለና መባውንም የሰጣችሁ የማኅበረሰቡን ኃጢአት እንድትሸከሙ እንዲሁም በይሖዋ ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ሆኖ ሳለ የኃጢአት መባውን በቅዱሱ ስፍራ ያልበላችሁት+ ለምንድን ነው? 18  ይኸው ደሙ ወደ ቅዱሱ ስፍራ አልገባም።+ ልክ እንደታዘዝኩት በቅዱሱ ስፍራ ልትበሉት ይገባችሁ ነበር።” 19  በዚህ ጊዜ አሮን ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እነሱ በዛሬው ዕለት የኃጢአት መባቸውንና የሚቃጠል መባቸውን በይሖዋ ፊት ያቀረቡት+ እኔ እንዲህ ያለ ነገር ደርሶብኝ እያለ ነው። ታዲያ ዛሬ የኃጢአት መባውን በልቼ ቢሆን ኖሮ ይሖዋ ይደሰት ነበር?” 20  ሙሴም ይህን ሲሰማ ነገሩን አጥጋቢ ሆኖ አገኘው።

የግርጌ ማስታወሻዎች