ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 3:1-17

  • የመጨረሻዎቹ ቀኖች (1-7)

  • የጳውሎስን ምሳሌ በጥብቅ መከተል (8-13)

  • ‘በተማርካቸው ነገሮች ጽና’ (14-17)

    • “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው” (16)

3  ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ቀናት+ ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ።  ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣  ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣* ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣  ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤  ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፤ በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ፤+ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።  በየቤቱ ሾልከው የሚገቡ ሰዎች የሚነሱት ከእነዚህ መካከል ነው፤ እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ምኞቶች የሚነዱትን፣ በኃጢአት የተተበተቡትን ደካማ ሴቶች ይማርካሉ፤  እንደነዚህ ያሉት ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ሆኖም ትክክለኛውን የእውነት እውቀት መረዳት አይችሉም።  እንግዲህ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደተቃወሙት ሁሉ እነዚህም እውነትን ይቃወማሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ የተበላሸ ከመሆኑም ሌላ በእምነት ጎዳና ስለማይመላለሱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥተዋል።  ይሁንና የእነዚያ ሁለት ሰዎች ሞኝነት ለሰው ሁሉ በጣም ግልጽ እንደነበረ ሁሉ የእነዚህ ሰዎች ሞኝነትም ግልጽ ስለሚሆን በአካሄዳቸው ብዙም ሊገፉበት አይችሉም።+ 10  አንተ ግን ትምህርቴን፣ አኗኗሬን፣+ ዓላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና ጽናቴን በጥብቅ ተከትለሃል፤ 11  እንደ አንጾኪያ፣+ ኢቆንዮንና+ ልስጥራ+ ባሉ ቦታዎች የደረሰብኝን ስደትና መከራ ታውቃለህ። ይህን ሁሉ ስደት በጽናት አሳልፌአለሁ፤ ጌታም ከዚህ ሁሉ ታደገኝ።+ 12  በእርግጥም የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።+ 13  ሆኖም ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች እያሳሳቱና እየተሳሳቱ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።+ 14  አንተ ግን በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር፤+ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች እነማን እንዳስተማሩህ ታውቃለህ፤ 15  እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት+ ከጨቅላነትህ+ ጀምሮ አውቀሃል።+ 16  ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤+ እንዲሁም ለማስተማር፣+ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና* በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ፤+ 17  ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለሰው ፍቅር የሌላቸው።”
ወይም “ለማረምና።”