ዕንባቆም 3:1-19
3 ነቢዩ ዕንባቆም በሙሾ* ያቀረበው ጸሎት፦
2 ይሖዋ ሆይ፣ ስለ አንተ የተወራውን ሰምቻለሁ።
ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ፍርሃት* አሳደረብኝ።
በዓመታት መካከል* ሥራህን ሕያው አድርግ!
በዓመታትም መካከል* ሥራህን አሳውቅ።
መዓት በሚወርድበት ጊዜ ምሕረትን አስታውስ።+
3 አምላክ ከቴማን፣ቅዱሱም ከፋራን ተራራ መጣ።+ (ሴላ)*
ግርማው ሰማያትን ሸፈነ፤+ምድርም በውዳሴው ተሞላች።
4 ጸዳሉ እንደ ፀሐይ ብርሃን ነው።+
ከእጁ ሁለት ጨረሮች ፈነጠቁ፤ብርታቱም በዚያ ተሰውሯል።
5 ቸነፈር ከፊቱ ሄደ፤+የሚያቃጥል ትኩሳትም እግር በእግር ተከተለው።
6 ቆመ፤ ምድርንም አንቀጠቀጠ።+
ባየም ጊዜ ብሔራትን አብረከረካቸው።+
ዘላለማዊ የሆኑት ተራሮች ተፈረካከሱ፤የጥንቶቹ ኮረብቶች ተደፉ።+
የጥንቶቹ መንገዶች የእሱ ናቸው።
7 በኩሻን ድንኳኖች ውስጥ ችግር አየሁ።
የምድያም የድንኳን ሸራዎች ተንቀጠቀጡ።+
8 ይሖዋ ሆይ፣ ቁጣህ የነደደው በወንዞች ላይ ነው?በእርግጥ በወንዞች ላይ ነው?
ወይስ ታላቅ ቁጣህን የገለጽከው በባሕሩ ላይ ነው?+
በፈረሶችህ ላይ ተቀምጠህ ጋልበሃልና፤+ሠረገሎችህ ድል ተቀዳጅተዋል።*+
9 የቀስትህ ሽፋን ተነስቷል፤ ቀስትህም ተዘጋጅቷል።
ዘንጎቹ* በመሐላ ተመድበዋል።* (ሴላ)
ምድሪቱን በወንዞች ከፈልክ።
10 ተራሮች አንተን ሲያዩ በሥቃይ ተንፈራገጡ።+
ዶፍ ዝናብ ጠራርጎ ሄደ።
ጥልቁ በኃይል ጮኸ።+
እጁን ወደ ላይ አነሳ።
11 ፀሐይና ጨረቃ ከፍ ባለው መኖሪያ ስፍራቸው ቆሙ።+
ፍላጾችህ እንደ ብርሃን ተወረወሩ።+
ጦርህ እንደ መብረቅ አብረቀረቀ።
12 በምድር ላይ በቁጣ ዘመትክ።
ብሔራትን በቁጣ ረገጥካቸው።*
13 ሕዝብህን ለመታደግ፣ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ።
የክፉውን ቤት መሪ* አደቀቅክ።
ቤቱ ከመሠረቱ አንስቶ እስከ አናቱ* ድረስ ተጋለጠ። (ሴላ)
14 እኔን ለመበታተን በቁጣ በተነሱ ጊዜበገዛ ራሱ መሣሪያዎች* የተዋጊዎቹን ራስ ወጋህ።
እነሱ ጎስቋላውን ሰው በስውር በመዋጥ ሐሴት አድርገዋል።
15 በባሕር ውስጥ፣ በሚናወጠው ብዙ ውኃ መካከልበፈረሶችህ እየጋለብክ አለፍክ።
16 እኔ ሰማሁ፤ ሆዴም ታወከ፤ከድምፁ የተነሳ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ።
አጥንቶቼም ነቀዙ፤+ከታች ያሉት እግሮቼ ተብረከረኩ።
ሆኖም የጭንቀትን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ፤+ይህ ቀን ጥቃት በሚሰነዝርብን ሕዝብ ላይ ይመጣልና።
17 የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣የወይን ተክልም ፍሬ ባይሰጥ፣የወይራ ዛፍም ባያፈራ፣እርሻዎቹም* እህል ባይሰጡ፣መንጋው ከጉረኖው ቢጠፋ፣ከብቶቹም ሁሉ በረት ውስጥ ባይገኙ፣
18 እኔ ግን በይሖዋ ሐሴት አደርጋለሁ፤አዳኜ በሆነውም አምላክ እደሰታለሁ።+
19 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ብርታቴ ነው፤+እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታ ስፍራዎችም ላይ ያስኬደኛል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በሐዘን እንጉርጉሮ።”
^ ወይም “አክብሮታዊ ፍርሃት።”
^ “በእኛ ዘመን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “በእኛም ዘመን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “መዳን አስገኝተዋል።”
^ “ቀስቶቹ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “ነገዶቹ የገቧቸው ቃለ መሐላዎች ተገልጸዋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “ወቃሃቸው።”
^ ቃል በቃል “ራስ።”
^ ቃል በቃል “አንገቱ።”
^ ቃል በቃል “በዘንጎቹ።”
^ ወይም “እርከኖቹም።”