የማቴዎስ ወንጌል 12:1-50

  • ኢየሱስ “የሰንበት ጌታ ነው” (1-8)

  • እጁ የሰለለ አንድ ሰው ተፈወሰ (9-14)

  • አምላክ የሚወደው አገልጋይ (15-21)

  • ኢየሱስ በአምላክ ኃይል አጋንንትን አስወጣ (22-30)

  • ይቅር የማይባል ኃጢአት (31, 32)

  • ዛፍ በፍሬው ይታወቃል (33-37)

  • የዮናስ ምልክት (38-42)

  • ሰባት ርኩስ መናፍስት ይዞ ይመጣል (43-45)

  • የኢየሱስ እናትና ወንድሞች (46-50)

12  በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል አለፈ። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ስለነበር እሸት እየቀጠፉ መብላት ጀመሩ።+  ፈሪሳውያን ይህን ባዩ ጊዜ “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር እያደረጉ ነው” አሉት።+  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁም?+  ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር+ እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች እንዲበሉ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት+ አልበሉም?  ደግሞስ ካህናት የሰንበትን ሕግ እንደሚተላለፉና ይህም እንደ በደል እንደማይቆጠርባቸው በሕጉ ላይ አላነበባችሁም?+  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ከቤተ መቅደሱ የሚበልጥ እዚህ አለ።+  ይሁንና ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን+ እንጂ መሥዋዕትን+ አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም ተረድታችሁ ቢሆን ኖሮ ምንም በደል ባልሠሩት ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር።  የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”+  ከዚያ ስፍራ ከሄደ በኋላ ወደ ምኩራባቸው ገባ፤ 10  በዚያም እጁ የሰለለ* አንድ ሰው ነበር።+ እነሱም ኢየሱስን መክሰስ ፈልገው “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል?” ሲሉ ጠየቁት።+ 11  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው ሰው ቢኖርና በሰንበት ቀን ጉድጓድ ውስጥ ቢገባበት በጉን ጎትቶ የማያወጣው ይኖራል?+ 12  ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል።” 13  ከዚያም ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም እንደ ሌላኛው እጁ ደህና ሆነለት። 14  ፈሪሳውያኑ ግን ወጥተው እሱን ለመግደል አሴሩ። 15  ኢየሱስም ይህን ሲያውቅ አካባቢውን ለቆ ሄደ። ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤+ እሱም የታመሙትን ሁሉ ፈወሳቸው፤ 16  ሆኖም የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ በጥብቅ አዘዛቸው፤+ 17  ይህን ያደረገው በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦ 18  “እነሆ፣ የምወደውና ደስ የምሰኝበት*+ የመረጥኩት አገልጋዬ!+ መንፈሴን በእሱ ላይ አደርጋለሁ፤+ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነም ለብሔራት ያሳውቃል። 19  አይጨቃጨቅም+ ወይም አይጮኽም፤ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ድምፁን የሚሰማ አይኖርም። 20  ፍትሕን በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪያሰፍን ድረስ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም።+ 21  በእርግጥም ብሔራት በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”+ 22  ከጊዜ በኋላም፣ ጋኔን የያዘው ዓይነ ስውርና ዱዳ ሰው ወደ እሱ አመጡ፤ እሱም ፈወሰው፤ ዱዳውም መናገርና ማየት ቻለ። 23  ሕዝቡም ሁሉ በጣም ተደንቀው “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆን እንዴ?” ይሉ ጀመር። 24  ፈሪሳውያን ይህን ሲሰሙ “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል* ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን ሊያስወጣ አይችልም” አሉ።+ 25  ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁሉ ጸንቶ አይቆምም። 26  በተመሳሳይም ሰይጣን ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተከፋፍሏል ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ታዲያ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል? 27  በተጨማሪም እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ* የሚያስወጧቸው ታዲያ በማን ነው? ልጆቻችሁ ፈራጆች የሚሆኑባችሁ* ለዚህ ነው። 28  ሆኖም አጋንንትን የማስወጣው በአምላክ መንፈስ ከሆነ የአምላክ መንግሥት ሳታስቡት ደርሶባችኋል ማለት ነው።+ 29  ደግሞስ አንድ ሰው በቅድሚያ ሰውየውን ሳያስር ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት ገብቶ እንዴት ንብረቱን ሊወስድ ይችላል? ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። 30  ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ሁሉ ይበትናል።+ 31  “ስለሆነም እላችኋለሁ፣ ሰዎች የሚሠሩት ኃጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ግን ይቅር አይባልለትም።+ 32  ለምሳሌ በሰው ልጅ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ሁሉ ይቅርታ ይደረግለታል፤+ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ክፉ ቃል የሚናገር ሁሉ ግን በዚህም ሆነ በሚመጣው ሥርዓት* ይቅርታ አይደረግለትም።+ 33  “መልካም ዛፍ ካላችሁ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ካላችሁ ደግሞ የበሰበሰ ፍሬ ያፈራል፤ ዛፍ የሚታወቀው በፍሬው ነውና።+ 34  እናንተ የእፉኝት ልጆች፣+ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ እንዴት መልካም ነገር ልትናገሩ ትችላላችሁ? አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነውና።+ 35  ጥሩ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር ጥሩ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰው ደግሞ በልቡ ካከማቸው መጥፎ ነገር ክፉ ነገር ያወጣል።+ 36  ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰዎች ለሚናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል፤+ 37  ከቃልህ የተነሳ ጻድቅ ትባላለህና፤ ከቃልህም የተነሳ ትኮነናለህ።” 38  ከዚያም ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ “መምህር፣ ምልክት እንድታሳየን እንፈልጋለን” አሉት።+ 39  እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ክፉና አመንዝራ* ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም።+ 40  ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ+ ሁሉ የሰው ልጅም በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል።+ 41  የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሐ ስለገቡ+ በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይኮንኑታል። ነገር ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።+ 42  የደቡብ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለመጣች+ በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትኮንነዋለች። ነገር ግን ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።+ 43  “ርኩስ መንፈስ ከሰው ሲወጣ የሚያርፍበት ቦታ ፍለጋ ውኃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሆኖም የሚያርፍበት ቦታ አያገኝም።+ 44  ከዚያም ‘ወደለቀቅኩት ቤቴ ተመልሼ እሄዳለሁ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና አጊጦ ያገኘዋል። 45  ከዚያም ሄዶ ከእሱ የከፉ ሌሎች ሰባት መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም ይኖሩበታል፤ የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከቀድሞው የከፋ ይሆንበታል።+ ይህ ክፉ ትውልድም ተመሳሳይ ነገር ይደርስበታል።” 46  ኢየሱስ ለሕዝቡ እየተናገረ ሳለ እናቱና ወንድሞቹ+ ሊያነጋግሩት ፈልገው ውጭ ቆመው ነበር።+ 47  ስለሆነም አንድ ሰው “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” አለው። 48  ኢየሱስም መልሶ ሰውየውን “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። 49  እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!+ 50  በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነውና።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሽባ የሆነ።”
ወይም “የምወደውና ነፍሴ ደስ የምትሰኝበት።”
ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው።
ወይም “መሳሳታችሁን የሚነግሯችሁ።”
ወይም “ተከታዮቻችሁ።”
ወይም “በሚመጣው ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ለአምላክ ታማኝ ያልሆነ።”