ዘፀአት 11:1-10

  • አሥረኛው መቅሰፍት እንደሚመጣ ተነገረ (1-10)

    • እስራኤላውያን ከግብፃውያን ላይ ስጦታ እንዲጠይቁ ተነገራቸው (2)

11  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ አንድ ተጨማሪ መቅሰፍት አመጣለሁ። ከዚያ በኋላ ከዚህ እንድትሄዱ ይለቃችኋል።+ ደግሞም በሚለቃችሁ ጊዜ አንዳችሁንም ሳያስቀር ከዚህ ያባርራችኋል።+ 2  እንግዲህ አሁን ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ሁሉ ከየጎረቤቶቻቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎችን እንዲጠይቁ ለሕዝቡ ንገር።”+ 3  ይሖዋም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስ ሰጣቸው። ሙሴ ራሱም ቢሆን በፈርዖን አገልጋዮችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ ምድር እጅግ የተከበረ ሰው ሆኖ ነበር። 4  ሙሴም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኩለ ሌሊት ገደማ በግብፅ መሃል እወጣለሁ፤+ 5  በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኩር ልጅ አንስቶ የወፍጮ መጅ እስከምትገፋው ባሪያ የበኩር ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር ያለ በኩር ሁሉ ይሞታል፤+ የእንስሳም በኩር ሁሉ ይሞታል።+ 6  በመላው የግብፅ ምድርም ከዚያ በፊት በጭራሽ ሆኖ የማያውቅ ከዚያ በኋላም ፈጽሞ ዳግመኛ የማይከሰት ታላቅ ዋይታ ይሆናል።+ 7  ሆኖም ይሖዋ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት ማድረግ እንደሚችል እንድታውቁ በእስራኤላውያን ላይ፣ በሰዎቹም ሆነ በእንስሶቻቸው ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽም።’*+ 8  አገልጋዮችህም ሁሉ ወደ እኔ ወርደው ‘አንተም ሆንክ አንተን የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ሂዱልን’ በማለት ይሰግዱልኛል።+ ከዚያ በኋላም እወጣለሁ።” ሙሴም ይህን ተናግሮ በታላቅ ቁጣ ከፈርዖን ፊት ወጣ። 9  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ተአምራቶቼ በግብፅ ምድር ላይ እንዲበዙ+ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው።+ 10  ሙሴና አሮንም እነዚህን ሁሉ ተአምራት በፈርዖን ፊት ፈጸሙ፤+ ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ስለፈቀደ ፈርዖን እስራኤላውያን ከምድሩ እንዲሄዱ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ምላሱን አያሾልም።”