ለጢሞቴዎስ የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 3:1-16

  • የበላይ ተመልካቾች ብቃት (1-7)

  • የጉባኤ አገልጋዮች ብቃት (8-13)

  • “ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር” (14-16)

3  ይህ ቃል እምነት የሚጣልበት ነው፦ የበላይ ተመልካች+ ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።  ስለዚህ የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ በልማዶቹ ልከኛ የሆነ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣*+ ሥርዓታማ፣ እንግዳ ተቀባይ፣+ የማስተማር ብቃት ያለው፣+  የማይሰክር፣*+ ኃይለኛ ያልሆነ፣* ይልቁንም ምክንያታዊ የሆነ፣+ የማይጣላ፣+ ገንዘብ ወዳድ ያልሆነ፣+  ታዛዥና ቁም ነገረኛ የሆኑ ልጆች ያሉትና የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባዋል፤+  (ደግሞስ አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?)  በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ የተፈረደበት ዓይነት ፍርድ እንዳይፈረድበት አዲስ ክርስቲያን አይሁን።+  ከዚህም በተጨማሪ እንዳይነቀፍና* በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ በውጭ ባሉት* ሰዎች ዘንድ በመልካም የተመሠከረለት* ሊሆን ይገባል።+  የጉባኤ አገልጋዮችም በተመሳሳይ ቁም ነገረኞች፣ በሁለት ምላስ የማይናገሩ፣* ብዙ የወይን ጠጅ የማይጠጡ፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይስገበገቡ፣+  የእምነትን ቅዱስ ሚስጥር በንጹሕ ሕሊና አጥብቀው የሚይዙ መሆን ይገባቸዋል።+ 10  በተጨማሪም ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅድሚያ ይፈተኑ፤ ከዚያም ከክስ ነፃ ሆነው+ ከተገኙ አገልጋይ ሆነው ያገልግሉ። 11  ሴቶችም እንደዚሁ ቁም ነገረኞች፣ የሰው ስም የማያጠፉ፣+ በልማዶቻቸው ልከኞችና በሁሉም ነገር ታማኞች ሊሆኑ ይገባል።+ 12  የጉባኤ አገልጋዮች የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድሩ ሊሆኑ ይገባል። 13  በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግሉ ወንዶች ለራሳቸው መልካም ስም የሚያተርፉ ከመሆናቸውም በላይ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚያስችል ነፃነት ያገኛሉና። 14  በቅርቡ ወደ አንተ እንደምመጣ ተስፋ ባደርግም እነዚህን ነገሮች ጽፌልሃለሁ፤ 15  ይህን ያደረግኩት ምናልባት ብዘገይ በአምላክ ቤተሰብ+ ይኸውም የእውነት ዓምድና ድጋፍ በሆነው የሕያው አምላክ ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንዳለብህ ታውቅ ዘንድ ነው። 16  በእርግጥም ይህ ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፦ ‘በሥጋ እንዲገለጥ ተደረገ፤+ በመንፈስ ጻድቅ ተባለ፤+ ለመላእክት ታየ፤+ በአሕዛብ መካከል ተሰበከ፤+ በዓለም ያሉ አመኑበት፤+ በክብር አረገ።’

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያለው።”
ቃል በቃል “ለወይን ጠጅ ያላደረ።”
ወይም “የማይማታ።” የግሪክኛው ቃል ሌሎችን መስደብንም ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “እንዳይዋረድና።”
ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ባልሆኑት።”
ወይም “ጥሩ ስም ያተረፈ።”
ወይም “በአንደበታቸው የማያታልሉ።”