የማርቆስ ወንጌል 8:1-38

  • ኢየሱስ 4,000 ሰዎችን መገበ (1-9)

  • ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁ (10-13)

  • “ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” (14-21)

  • በቤተሳይዳ አንድ ዓይነ ስውር ተፈወሰ (22-26)

  • ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው (27-30)

  • ኢየሱስ እንደሚሞት ተናገረ (31-33)

  • እውነተኛ ደቀ መዝሙር (34-38)

8  በዚያን ወቅት፣ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ የሚበሉትም አልነበራቸውም። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦  “እነዚህ ሰዎች ሦስት ቀን ሙሉ ከእኔ ጋር ስለቆዩና የሚበሉት ስለሌላቸው+ አዝንላቸዋለሁ።+  እንዲሁ ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው መንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ፤ ደግሞም አንዳንዶቹ የመጡት ከሩቅ ነው።”  ደቀ መዛሙርቱ ግን “በዚህ ገለልተኛ ስፍራ እነዚህን ሰዎች የሚያጠግብ በቂ ዳቦ ከየት ማግኘት ይቻላል?” ሲሉ መለሱለት።  በዚህ ጊዜ “ስንት ዳቦ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “ሰባት” አሉት።+  እሱም ሕዝቡ መሬት ላይ እንዲቀመጥ አዘዘ። ከዚያም ሰባቱን ዳቦ ይዞ አምላክን አመሰገነ፤ ቆርሶም እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነሱም ለሕዝቡ አደሉ።+  ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎችም ነበሯቸው፤ እነዚህንም ከባረከ በኋላ እንዲያድሉ ነገራቸው።  ሕዝቡም በልቶ ጠገበ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም ሰባት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+  በዚያም 4,000 ገደማ ወንዶች ነበሩ። በመጨረሻም አሰናበታቸው። 10  ወዲያውኑ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ተሳፍሮ ዳልማኑታ ወደተባለ ክልል መጣ።+ 11  እዚያም ፈሪሳውያን መጥተው እሱን ለመፈተን ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው በመጠየቅ ይከራከሩት ጀመር።+ 12  እሱም እጅግ አዝኖ በረጅሙ ከተነፈሰ በኋላ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው?+ እውነት እላችኋለሁ፣ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም” አለ።+ 13  ከዚያም ትቷቸው ሄደ፤ እንደገና ጀልባ ተሳፍሮም ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻገረ። 14  ይሁንና ዳቦ መያዝ ረስተው ስለነበር በጀልባው ውስጥ ከአንድ ዳቦ በስተቀር ምንም አልነበራቸውም።+ 15  ኢየሱስም “ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ሲል በግልጽ አስጠነቀቃቸው።+ 16  እነሱም ዳቦ ባለመያዛቸው እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። 17  ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ዳቦ ባለመያዛችሁ ለምን ትከራከራላችሁ? አሁንም አልገባችሁም? ደግሞስ አላስተዋላችሁም? ልባችሁ መረዳት እንደተሳነው ነው? 18  ‘ዓይን እያላችሁ አታዩም? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙም?’ ደግሞስ አታስታውሱም? 19  አምስቱን ዳቦ ለ5,000ዎቹ ወንዶች በቆረስኩ+ ጊዜ ስንት ቅርጫት ሙሉ ትርፍራፊ ሰበሰባችሁ?” እነሱም “አሥራ ሁለት”+ አሉት። 20  “ሰባቱን ዳቦ ለ4,000ዎቹ ወንዶች በቆረስኩ ጊዜ ስንት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ትርፍራፊ አነሳችሁ?” እነሱም “ሰባት” አሉት።+ 21  እሱም “ታዲያ አሁንም አልገባችሁም?” አላቸው። 22  ከዚያም ወደ ቤተሳይዳ መጡ። በዚያም ሰዎች አንድ ዓይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ተማጸኑት።+ 23  እሱም ዓይነ ስውሩን፣ እጁን ይዞ ከመንደሩ ውጭ ወሰደው። በዓይኖቹ ላይ እንትፍ ካለ በኋላ+ እጆቹን ጫነበትና “የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። 24  ሰውየውም ቀና ብሎ በማየት “ሰዎች ይታዩኛል፤ ሆኖም የሚራመዱ ዛፎች ይመስላሉ” አለ። 25  ኢየሱስ እንደገና እጆቹን ሰውየው ዓይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው አጥርቶ አየ። ዓይኖቹም በሩ፤ ሁሉንም ነገር በደንብ ለይቶ ማየት ቻለ። 26  በመጨረሻም “ወደ መንደሩ አትግባ” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው። 27  ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ መንደሮች አመሩ፤ በመንገድም ላይ ሳሉ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ጠየቃቸው።+ 28  እነሱም “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣+ ሌሎች ኤልያስ፣+ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል” አሉት። 29  ከዚያም እነሱን “እናንተስ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ ነህ”+ ብሎ መለሰለት። 30  በዚህ ጊዜ ስለ እሱ ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አዘዛቸው።+ 31  በተጨማሪም የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበሉ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት ተቀባይነት ማጣቱ ብሎም መገደሉና+ ከሦስት ቀን በኋላ መነሳቱ+ እንደማይቀር ያስተምራቸው ጀመር። 32  ደግሞም ይህን በግልጽ ነገራቸው። ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ ይገሥጸው ጀመር።+ 33  በዚህ ጊዜ ዞር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ተመለከተና ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን!* የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ አታስብም” ሲል ገሠጸው።+ 34  ከዚህ በኋላ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት* ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።+ 35  ሕይወቱን* ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታልና፤ ለእኔና ለምሥራቹ ሲል ሕይወቱን* የሚያጣ ሁሉ ግን ያድናታል።+ 36  ደግሞስ አንድ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ ቢያደርግና ሕይወቱን* ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?+ 37  ሰው ለሕይወቱ* ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?+ 38  በዚህ አመንዝራና* ኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ሲመጣ+ ያፍርበታል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ሰይጣን” የሚለው ቃል ተቃዋሚ የሚል ትርጉም ስላለው ኢየሱስ ጴጥሮስን “ተቃዋሚ” ብሎ መጥራቱ ነበር።
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ለነፍሱ።”
ወይም “ለአምላክ ታማኝ ባልሆነና።”