ኢዮብ 6:1-30
6 ከዚያም ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2 “ምነው ሥቃዬ ሁሉ+ በተመዘነ ኖሮ!ከመከራዬም ጋር ሚዛን ላይ በተቀመጠ ኖሮ!
3 ከባሕር አሸዋ ይልቅ ከባድ ሆኖብኛልና።
ከዚህም የተነሳ እንዳመጣልኝ* እናገራለሁ።+
4 ሁሉን የሚችለው አምላክ ፍላጻዎች ወግተውኛልና፤መንፈሴም መርዛቸውን እየጠጣ ነው፤+ከአምላክ የመጣ ሽብር በእኔ ላይ ተሰልፏል።
5 የዱር አህያ+ ሣር እያለው ያናፋል?በሬስ ገፈራ እያለው ይጮኻል?
6 ጣዕም የሌለው ምግብ ያለጨው ይበላል?ወይስ የልት* ፈሳሽ ጣዕም ይኖረዋል?
7 እንዲህ ያሉ ነገሮችን መንካት ተጸይፌአለሁ።*
በምግቤ ውስጥ እንዳሉ የሚበክሉ ነገሮች ናቸው።*
8 ምነው ጥያቄዬ መልስ ባገኘ!አምላክም ፍላጎቴን በፈጸመልኝ!
9 ምነው አምላክ እኔን ለማድቀቅ በፈቀደ!እጁንም ዘርግቶ ባጠፋኝ!+
10 ይህም እንኳ ባጽናናኝ ነበርና፤ፋታ የማይሰጥ ሥቃይ ቢኖርብኝም በደስታ እዘላለሁ፤የቅዱሱን አምላክ ቃል አልካድኩምና።+
11 ከዚህ በላይ መታገሥ የምችልበት ምን አቅም አለኝ?+
በሕይወት መኖሬን ብቀጥልስ* ምን አገኛለሁ?
12 እኔ የዓለት ዓይነት ጥንካሬ አለኝ?
ወይስ ሥጋዬ ከመዳብ የተሠራ ነው?
13 ራሴን የምደግፍበት ነገር ሁሉ ከእኔ ርቆ ሳለ፣ራሴን መርዳት የምችልበት መንገድ ይኖራል?
14 ለገዛ ወዳጁ ታማኝ ፍቅር የማያሳይ ሰው፣+ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ መፍራት ይተዋል።+
15 የገዛ ወንድሞቼ እንደ ክረምት ጅረት፣እንደሚደርቅ የክረምት የጅረት ውኃ ከዳተኞች ሆኑብኝ።+
16 ከበረዶ የተነሳ ደፈረሱ፤የሚቀልጥ አመዳይም በእነሱ ውስጥ ተሰውሯል።
17 ሆኖም ወቅቱ ሲደርስ ውኃ አልባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ደብዛቸው ይጠፋል፤በሙቀትም ጊዜ ይደርቃሉ።
18 የሚሄዱበት መንገድ ይቀየራል፤ወደ በረሃ ፈስሰው ይጠፋሉ።
19 የቴማ+ ነጋዴዎች ይፈልጓቸዋል፤የሳባም+ መንገደኞች* እነሱን ይጠባበቃሉ።
20 የተሳሳተ እምነት አድሮባቸው ስለነበር ለኀፍረት ተዳረጉ፤ወደዚያ ቢሄዱም የጠበቁትን ባለማግኘታቸው አዘኑ።
21 እናንተም እንደዚሁ ሆናችሁብኛል፤+መከራዬ ያስከተለውን ሽብር አይታችሁ በፍርሃት ተዋጣችሁ።+
22 ለመሆኑ እኔ ‘አንድ ነገር ስጡኝ’ ብያለሁ?
ወይስ ካፈራችሁት ሀብት ላይ ስጦታ እንድትሰጡኝ ጠይቄአለሁ?
23 ከጠላት እጅ እንድትታደጉኝ፣ወይም ከጨቋኞች እንድታድኑኝ* ጠይቄአለሁ?
24 አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ፤+የሠራሁትን ስህተት እንዳስተውል እርዱኝ።
25 በሐቀኝነት የተነገረ ቃል አያቆስልም!+
የእናንተ ወቀሳ ግን ጥቅሙ ምንድን ነው?+
26 እኔ የምናገረውን ቃል፣ነፋስ ጠራርጎ የሚወስደውን፣ ተስፋ የቆረጠ ሰው ንግግር+ ለማረም ታስባላችሁ?
27 ወላጅ አልባ በሆነውም ልጅ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤+ወዳጃችሁንም ትሸጣላችሁ!*+
28 እስቲ አሁን ዞር ብላችሁ ተመልከቱኝ፤በፊታችሁ አልዋሽም።
29 እባካችሁ፣ ቆም ብላችሁ አስቡበት፤ በተሳሳተ መንገድ አትረዱኝ፤አዎ፣ ቆም ብላችሁ አስቡበት፤ ጽድቄ እንዳለ ነውና።
30 ምላሴ አግባብ ያልሆነ ነገር ይናገራል?
ላንቃዬስ የሆነ ችግር እንዳለ መለየት አይችልም?
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በችኮላ፤ በግዴለሽነት።”
^ ጣዕም የሌለውና ዝልግልግ ፈሳሽ የሚወጣው ተክል።
^ ወይም “ነፍሴ ተጸይፋለች።”
^ ይህ አባባል ኢዮብ የደረሰበትን መከራ ወይም አጽናኞቹ የሰጡትን ምክር ሊያመለክት ይችላል።
^ ወይም “ሕይወቴን (ነፍሴን) ባራዝምስ።”
^ ወይም “በቡድን የሚጓዙ ሳባውያንም።”
^ ቃል በቃል “ከጨቋኞች እንድትዋጁኝ።”
^ ወይም “ትለውጣላችሁ።”