የማርቆስ ወንጌል 3:1-35

  • እጁ የሰለለ አንድ ሰው ተፈወሰ (1-6)

  • በባሕሩ ዳርቻ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ (7-12)

  • የኢየሱስ 12 ሐዋርያት (13-19)

  • መንፈስ ቅዱስን መሳደብ (20-30)

  • የኢየሱስ እናትና ወንድሞች (31-35)

3  ዳግመኛ ወደ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ* አንድ ሰው ነበር።+ 2  ኢየሱስን ሊከሱት ይፈልጉ ስለነበር ሰውየውን በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር። 3  እሱም እጁ የሰለለበትን* ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” አለው። 4  ከዚያም “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት* ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።+ እነሱ ግን ዝም አሉ። 5  በልባቸው ደንዳናነት+ በጣም አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት። 6  ፈሪሳውያኑ ወጥተው ከሄዱ በኋላ ወዲያው ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች+ ጋር በመሰብሰብ እንዴት እንደሚገድሉት መመካከር ጀመሩ። 7  ኢየሱስ ግን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላና ከይሁዳ የመጣ ብዙ ሕዝብም ተከተለው።+ 8  ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች የሰሙ ብዙ ሰዎች ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስና ከዮርዳኖስ ማዶ እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ እንኳ ሳይቀር ወደ እሱ መጡ። 9  ኢየሱስም ሕዝቡ እንዳያጨናንቀው አንዲት ትንሽ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። 10  ብዙ ሰዎችን ፈውሶ ስለነበር ከባድ በሽታ የያዛቸው ሁሉ እሱን ለመንካት በዙሪያው ይጋፉ ነበር።+ 11  ርኩሳን መናፍስት+ እንኳ ሳይቀሩ ባዩት ቁጥር በፊቱ ወድቀው “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር።+ 12  ሆኖም የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ በተደጋጋሚ አጥብቆ አዘዛቸው።+ 13  ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ሰዎች ጠራ፤+ እነሱም ወደ እሱ መጡ።+ 14  ከዚያም 12 ሰዎች መርጦ ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤* እነዚህ አብረውት የሚሆኑ ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ለስብከት ሥራ የሚልካቸውና 15  አጋንንትን የማስወጣት ሥልጣን የሚሰጣቸው ናቸው።+ 16  የመረጣቸውም* 12 ሐዋርያት+ እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፣+ 17  የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስ (እነዚህን ቦአኔርጌስ ብሎ የሰየማቸው ሲሆን ትርጉሙም “የነጎድጓድ ልጆች” ማለት ነው)፣+ 18  እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀነናዊው* ስምዖን 19  እንዲሁም በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። ከዚያ በኋላ ወደ አንድ ቤት ሄደ፤ 20  ዳግመኛም ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ ከዚህም የተነሳ እህል እንኳ መቅመስ አልቻሉም። 21  ዘመዶቹ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ “አእምሮውን ስቷል” በማለት ሊይዙት መጡ።+ 22  ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም “ብዔልዜቡል* አለበት፤ አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” ይሉ ነበር።+ 23  በመሆኑም ወደ እሱ ከጠራቸው በኋላ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንዴት ሰይጣንን ሊያስወጣ ይችላል? 24  አንድ መንግሥት እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ያ መንግሥት ጸንቶ ሊቆም አይችልም፤+ 25  አንድ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ጸንቶ ሊቆም አይችልም። 26  በተመሳሳይም ሰይጣን በራሱ ላይ የሚነሳና የሚከፋፈል ከሆነ ያከትምለታል እንጂ ሊጸና አይችልም። 27  ደግሞም ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት የገባ ሰው በቅድሚያ ብርቱውን ሰው ሳያስር ንብረቱን ሊሰርቅ አይችልም። ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። 28  እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጆች ምንም ዓይነት ኃጢአት ቢሠሩ ወይም ምንም ዓይነት የስድብ ቃል ቢናገሩ ሁሉም ይቅር ይባልላቸዋል። 29  ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ሁሉ ለዘላለም ይቅር አይባልም፤+ ከዚህ ይልቅ ለዘላለም የሚጠየቅበት ኃጢአት ይሆንበታል።”+ 30  ይህን ያለው “ርኩስ መንፈስ አለበት” ይሉ ስለነበር ነው።+ 31  በዚህ ጊዜ እናቱና ወንድሞቹ+ መጡ፤ ውጭ ቆመውም ሰው ልከው አስጠሩት።+ 32  በዙሪያውም ብዙ ሰዎች ተቀምጠው ስለነበር “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ሆነው እየጠሩህ ነው” አሉት።+ 33  እሱ ግን መልሶ “እናቴና ወንድሞቼ እነማን ናቸው?” አላቸው። 34  ከዚያም ዙሪያውን ከበው ወደተቀመጡት ሰዎች ተመልክቶ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!+ 35  የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሽባ የሆነ።”
ወይም “ሽባ የሆነበትን።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ሾማቸው።”
ወይም “የሾማቸውም።”
ወይም “ቀናተኛው።”
ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው።