ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 3:1-29

  • የሕግ ሥራዎችና እምነት (1-14)

    • “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” (11)

  • ለአብርሃም የተገባው የተስፋ ቃል በሕጉ ላይ የተመሠረተ አይደለም (15-18)

    • የአብርሃም ዘር የሆነው ክርስቶስ (16)

  • ሕጉ የተሰጠበት ዓላማ (19-25)

  • ‘በእምነት የተነሳ የአምላክ ልጆች ናችሁ’ (26-29)

    • ‘የክርስቶስ ከሆናችሁ የአብርሃም ዘር ናችሁ’ (29)

3  እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁ የገላትያ ሰዎች! ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእንጨት ላይ ተቸንክሮ ፊት ለፊት ያያችሁት ያህል በዓይነ ሕሊናችሁ ተስሎ ነበር፤+ ታዲያ አሁን አፍዝ አደንግዝ ያደረገባችሁ ማን ነው?+ 2  እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፦ መንፈስን የተቀበላችሁት ሕግን በመጠበቅ ነው ወይስ የሰማችሁትን በማመን?+ 3  ይህን ያህል ማስተዋል የጎደላችሁ ናችሁ? በመንፈሳዊ መንገድ መጓዝ ከጀመራችሁ በኋላ በሥጋዊ መንገድ ልታጠናቅቁ ታስባላችሁ?+ 4  ብዙ መከራ የተቀበላችሁት እንዲያው በከንቱ ነው? መቼም በከንቱ ነው ብዬ አላስብም። 5  መንፈስን የሚሰጣችሁና በመካከላችሁ ተአምራት የሚፈጽመው+ እሱ ይህን የሚያደርገው ሕግን በመጠበቃችሁ ነው ወይስ የሰማችሁትን በማመናችሁ? 6  ይህም አብርሃም “በይሖዋ* አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” እንደተባለው ነው።+ 7  የአብርሃም ልጆች የሆኑት እምነትን አጥብቀው የሚከተሉት መሆናቸውን እንደምታውቁ የተረጋገጠ ነው።+ 8  ቅዱስ መጽሐፉ፣ አምላክ ከብሔራት ወገን የሆኑ ሰዎችን በእምነት አማካኝነት ጸድቃችኋል እንደሚላቸው አስቀድሞ ተረድቶ “ብሔራት ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ” በማለት ምሥራቹን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታውቆታል።+ 9  በመሆኑም እምነትን አጥብቀው የሚይዙ በእምነት ከተመላለሰው ከአብርሃም ጋር የበረከቱ ተካፋዮች ሆነዋል።+ 10  ሕግን በመጠበቅ የሚታመኑ ሁሉ የተረገሙ ናቸው፤ “በሕጉ የመጽሐፍ ጥቅልል የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ በመፈጸም እነሱን ተግባራዊ ማድረጉን የማይቀጥል ሰው ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፏልና።+ 11  በተጨማሪም “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ ስለተጻፈ+ በአምላክ ፊት ማንም በሕግ አማካኝነት ጻድቅ ሊባል እንደማይችል ግልጽ ነው።+ 12  ሕጉ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ትእዛዛቱን የሚጠብቅ ማንኛውም ሰው በእነሱ አማካኝነት በሕይወት ይኖራል” ይላል።+ 13  ክርስቶስ በእኛ ፋንታ የተረገመ ሆኖ እኛን ከሕጉ እርግማን ነፃ በማውጣት+ ዋጅቶናል፤+ ምክንያቱም “በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሰው ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፏል።+ 14  ይህም የሆነው ለአብርሃም ቃል የተገባው በረከት በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ለብሔራት እንዲደርስና+ እኛም በእምነታችን አማካኝነት ቃል የተገባውን መንፈስ ማግኘት እንድንችል ነው።+ 15  ወንድሞች፣ በሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደ አንድ ምሳሌ ልጠቀም፦ አንድ ቃል ኪዳን፣ በሰውም እንኳ ቢሆን አንዴ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም ምንም ነገር ሊጨምርበት አይችልም። 16  የተስፋው ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነው።+ ቅዱስ መጽሐፉ ስለ ብዙዎች እንደሚናገር “ለዘሮችህ” አይልም። ከዚህ ይልቅ ስለ አንድ እንደሚናገር “ለዘርህ” ይላል፤ እሱም ክርስቶስ ነው።+ 17  በተጨማሪም ይህን እላለሁ፦ ከ430 ዓመታት በኋላ+ የተሰጠው ሕግ ቀደም ሲል አምላክ የገባውን ቃል ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም። 18  ውርሻው የሚገኘው በሕግ አማካኝነት ቢሆን ኖሮ በተስፋ ቃል አማካኝነት መሆኑ በቀረ ነበርና፤ ሆኖም አምላክ ውርሻውን ለአብርሃም በደግነት የሰጠው በተስፋ ቃል አማካኝነት ነው።+ 19  ታዲያ ሕግ የተሰጠው ለምንድን ነው? ሕጉ የተጨመረው፣ ቃል የተገባለት ዘር እስኪመጣ ድረስ+ ሕግ ተላላፊነትን ይፋ ለማድረግ ነው፤+ ሕጉ የተሰጠውም በመላእክት አማካኝነት+ በአንድ መካከለኛ እጅ ነው።+ 20  ይሁንና አንድ ወገን ብቻ ባለበት መካከለኛ አይኖርም፤ አምላክ ደግሞ አንድ ወገን ብቻ ነው። 21  ታዲያ ሕጉ የአምላክን የተስፋ ቃል ይጻረራል ማለት ነው? በጭራሽ! ሕይወት ሊያስገኝ የሚችል ሕግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ጽድቅ የሚገኘው በሕግ አማካኝነት በሆነ ነበር። 22  ሆኖም ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉም ነገሮች የኃጢአት እስረኛ እንዲሆኑ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፤ ይህም የሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ሁሉ ይሰጥ ዘንድ ነው። 23  ይሁን እንጂ እምነት ከመምጣቱ በፊት፣ ሊገለጥ ያለውን እምነት እየተጠባበቅን በሕግ ጥበቃ ሥር እስረኞች እንድንሆን አልፈን ተሰጥተናል።+ 24  በመሆኑም በእምነት አማካኝነት መጽደቅ እንችል ዘንድ+ ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚታችን* ሆኗል።+ 25  አሁን ግን ያ እምነት ስለመጣ+ ከእንግዲህ ወዲህ በሞግዚት* ሥር አይደለንም።+ 26  እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ባላችሁ እምነት የተነሳ+ የአምላክ ልጆች ናችሁ።+ 27  ወደ ክርስቶስ የተጠመቃችሁ ሁላችሁም ክርስቶስን ለብሳችኋልና።*+ 28  ሁላችሁም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት በመፍጠር አንድ በመሆናችሁ+ በአይሁዳዊና በግሪካዊ፣+ በባሪያና በነፃ ሰው+ እንዲሁም በወንድና በሴት+ መካከል ልዩነት የለም። 29  በተጨማሪም የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥም የአብርሃም ዘር ናችሁ፤+ በተስፋውም ቃል መሠረት+ ወራሾች ናችሁ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አስተማሪያችን።”
ወይም “በአስተማሪ።”
ወይም “እንደ ክርስቶስ ሆናችኋልና።”