ዘኁልቁ 6:1-27
6 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ለይሖዋ ናዝራዊ*+ ሆነው ለመኖር ልዩ ስእለት ቢሳሉ
3 ስእለት የተሳለው ሰው ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር ሌላ መጠጥ መራቅ ይኖርበታል። የወይን ጠጅ ኮምጣጤ ወይም የማንኛውም ዓይነት የሚያሰክር መጠጥ ኮምጣጤ አይጠጣ።+ ከወይን ፍሬ የተዘጋጀን ማንኛውንም መጠጥ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ።
4 ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ከወይን ተክል የተዘጋጀን ማንኛውንም ነገር፣ ያልበሰለውን የወይን ፍሬም ሆነ ግልፋፊውን ፈጽሞ መብላት የለበትም።
5 “‘ናዝራዊ ሆኖ ለመቆየት በተሳለበት ጊዜ ሁሉ ራሱን ምላጭ አይንካው።+ ለይሖዋ የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የራስ ፀጉሩን በማሳደግ ቅዱስ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል።
6 ራሱን ለይሖዋ በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሞተ ሰው* አይቅረብ።*
7 ለአምላኩ ናዝራዊ መሆኑን የሚያሳየው ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እህቱ ቢሞቱ እንኳ በእነሱ ራሱን አያርክስ።+
8 “‘ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ለይሖዋ ቅዱስ ይሆናል።
9 ይሁንና አንድ ሰው ድንገት አጠገቡ ቢሞትና+ ለአምላክ የተለየ መሆኑን የሚያሳየውን ፀጉሩን ቢያረክስ* መንጻቱን በሚያረጋግጥበት ቀን ራሱን ይላጭ።+ በሰባተኛውም ቀን ፀጉሩን ይላጨው።
10 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወደሚገኘው ካህን ያምጣ።
11 ካህኑም አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርጎ በማዘጋጀት ከሞተ ሰው* ጋር በተያያዘ ስለሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል።+ ከዚያም በዚያ ቀን ራሱን ይቀድስ።
12 ናዝራዊ ሆኖ ለሚቆይበት ጊዜ እንደገና ራሱን ለይሖዋ ይለይ፤ አንድ ዓመት ገደማ የሆነው የበግ ጠቦት የበደል መባ አድርጎ ያምጣ። ሆኖም ናዝራዊነቱን ስላረከሰ የቀድሞዎቹ ጊዜያት አይታሰቡለትም።
13 “‘እንግዲህ ናዝራዊን በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፦ ናዝራዊ ሆኖ የሚቆይበትን ጊዜ ሲያጠናቅቅ+ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ እንዲመጣ ይደረግ።
14 በዚያም የሚከተሉትን ለይሖዋ መባ አድርጎ ያቅርብ፦ ለሚቃጠል መባ አንድ ዓመት ገደማ የሆነውን እንከን የሌለበት አንድ የበግ ጠቦት፣+ ለኃጢአት መባ አንድ ዓመት ገደማ የሆናትን እንከን የሌለባት አንዲት ጠቦት፣+ ለኅብረት መሥዋዕት እንከን የሌለበትን አንድ አውራ በግ፣+
15 በዘይት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጁ እርሾ ያልገባባቸው አንድ ቅርጫት የቀለበት ቅርጽ ያላቸው ዳቦዎችና ዘይት የተቀቡ ስስ ቂጣዎች* እንዲሁም የእህል መባዎቻቸውንና+ የመጠጥ መባዎቻቸውን።+
16 ካህኑም እነዚህን በይሖዋ ፊት ያቀርባቸዋል፤ የሰውየውን የኃጢአት መባና የሚቃጠል መባም ያቀርባል።
17 አውራውንም በግ በቅርጫቱ ውስጥ ካሉት ቂጣዎች ጋር የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለይሖዋ ያቀርበዋል፤ ካህኑም የእህል መባውንና+ የመጠጥ መባውን ያቀርበዋል።
18 “‘ከዚያም ናዝራዊው ያልተቆረጠውን ፀጉሩን*+ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ይላጭ፤ ናዝራዊ ሆኖ በቆየበት ጊዜ ያደገውን የራሱን ፀጉር ወስዶ ከኅብረት መሥዋዕቱ ሥር ባለው እሳት ውስጥ ይጨምረው።
19 ናዝራዊው የናዝራዊነት ምልክቱን ከተላጨ በኋላ ካህኑ የአውራውን በግ አንድ የተቀቀለ+ የፊት እግር፣ ከቅርጫቱም ውስጥ እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው አንድ ዳቦ እንዲሁም አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ በናዝራዊው መዳፍ ላይ ያድርጋቸው።
20 ካህኑም እነዚህን የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዝውዛቸው።+ ይህም ከሚወዘወዘው መባ ፍርምባና መዋጮ ሆኖ ከተሰጠው እግር ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ይሆናል።+ ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል።
21 “‘ስእለት የሚሳልን ናዝራዊ+ በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፦ ናዝራዊው ስእለት ከተሳለና በናዝራዊነት ከሚጠበቅበት በተጨማሪ ለይሖዋ መባ ለማቅረብ አቅሙ የሚፈቅድለት ከሆነ ለናዝራዊነቱ ሕግ ካለው አክብሮት የተነሳ ስእለቱን መፈጸም ይገባዋል።’”
22 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
23 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤልን ሕዝብ የምትባርኩት+ በዚህ መንገድ ነው። እንዲህ በሏቸው፦
24 “ይሖዋ ይባርክህ፤+ ደግሞም ይጠብቅህ።
25 ይሖዋ ፊቱን ያብራልህ፤+ ሞገሱንም ያሳይህ።
26 ይሖዋ ፊቱን ወደ አንተ ይመልስ፤ ሰላምም ይስጥህ።”’+
27 እኔም እንድባርካቸው+ ስሜን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያድርጉ።”+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ በዕብራስይጥ ናዚር ሲሆን “ተነጥሎ የወጣ፤ ለአንድ ነገር የተወሰነ፤ ለአንድ ዓላማ የተለየ” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “የሞተ ሰው ወዳለበት ቦታ አይቅረብ።”
^ ወይም “የናዝራዊነት ራሱን ቢያረክስ።”
^ ወይም “ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “የናዝራዊነት ራሱን።”