ኢዮብ 41:1-34

  • አምላክ የሌዋታንን አስደናቂ አፈጣጠር ገለጸ (1-34)

41  “ሌዋታንን*+ በመንጠቆ ልትይዘው፣ወይስ ምላሱን በገመድ ልታስረው ትችላለህ?   በአፍንጫው ገመድ* ልታስገባ፣ወይስ መንጋጋዎቹን በሜንጦ* ልትበሳ ትችላለህ?   እሱ እንድትምረው ይለማመጥሃል?ወይስ በለሰለሰ አንደበት ያናግርሃል?   ዕድሜ ልኩን ባሪያህ ታደርገው ዘንድ፣ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባል?   ከወፍ ጋር እንደምትጫወተው ከእሱ ጋር ትጫወታለህ?ወይስ ለትናንሽ ሴት ልጆችህ መጫወቻ እንዲሆን በውሻ ማሰሪያ ታስረዋለህ?   ነጋዴዎች ይገበያዩበታል? ለቸርቻሪዎችስ ያከፋፍሉታል?   ቆዳውን ለአደን በሚያገለግል ጦር፣+ራሱንስ በዓሣ መውጊያ ጭሬ ልትጠቀጥቅ ትችላለህ?   እስቲ እጅህን አሳርፍበት፤ግብግቡን መቼም አትረሳውም፤ ዳግመኛም እንዲህ ለማድረግ አይቃጣህም!   እሱን በቁጥጥር ሥር አውላለሁ ማለት ከንቱ ልፋት ነው። እሱን በማየትህ ብቻ እንኳ ብርክ ይይዝሃል።* 10  እሱን ለመተንኮስ የሚደፍር የለም። ታዲያ እኔን ሊቋቋም የሚችል ማን ነው?+ 11  ብድራት እመልስለት ዘንድ በመጀመሪያ አንዳች ነገር የሰጠኝ ማን ነው?+ ከሰማያት በታች ያለው ሁሉ የእኔ ነው።+ 12  ስለ እግሮቹ፣ ደግሞም ስለ ኃይሉናግሩም በሆነ መንገድ ስለተሠራው አካሉ ከመናገር አልቆጠብም። 13  የላይኛውን ሽፋኑን የገፈፈ ማን ነው? ወደተከፈቱ መንጋጋዎቹስ ማን ይገባል? 14  የአፉን* በሮች በኃይል ሊከፍት የሚችል ማን ነው? በዙሪያው ያሉት ጥርሶቹ አስፈሪ ናቸው። 15  ጀርባው ላይ እርስ በርስ የተጣበቁ፣በረድፍ የተቀመጡ ቅርፊቶች አሉ።* 16  ቅርፊቶቹ ግጥግጥ ያሉ ከመሆናቸው የተነሳ፣በመካከላቸው አየር እንኳ ሊገባ አይችልም። 17  አንዳቸው ከሌላው ጋር የተጣበቁ ናቸው፤እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው፤ ሊለያዩም አይችሉም። 18  ፉርፉርታው የብርሃን ብልጭታ ያወጣል፤ዓይኖቹም እንደ ማለዳ ጨረር ናቸው። 19  ከአፉ የመብረቅ ብልጭታዎች ይወጣሉ፤የእሳት ፍንጣሪዎችም ይረጫሉ። 20  በእንግጫ እንደተቀጣጠለ ምድጃ፣ከአፍንጫው ጭስ ይወጣል። 21  እስትንፋሱ ከሰል ያቀጣጥላል፤ከአፉም ነበልባል ይወረወራል። 22  በአንገቱ ውስጥ ታላቅ ብርታት አለ፤ሽብርም በፊቱ ይሮጣል። 23  የሥጋው ንብርብር እርስ በርስ የተጣበቀ ነው፤ከቦታው እንደማይነቃነቅ ብረት ጠንካራ ነው። 24  ልቡ እንደ ድንጋይ የጠጠረ፣አዎ፣ እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጠነከረ ነው። 25  በሚነሳበት ጊዜ ኃያላን እንኳ ይርዳሉ፤ውኃውን እየመታ ሲሄድ ያስደነብራል። 26  ሰይፍ፣ ጦር፣ መውጊያም ሆነ ፍላጻ ቢያገኙትሊያሸንፉት አይችሉም።+ 27  ብረትን እንደ ገለባ፣መዳብንም እንደበሰበሰ እንጨት ይቆጥራል። 28  ፍላጻ አያባርረውም፤የወንጭፍ ድንጋይም ለእሱ እንደ ገለባ ነው። 29  ቆመጥን እንደ ገለባ ይቆጥረዋል፤ጦር ሲሰበቅም ይስቃል። 30  ሆዱ እንደሾሉ የሸክላ ስብርባሪዎች ነው፤እንደ ማሄጃ*+ በጭቃ ላይ ምልክት ትቶ ያልፋል። 31  ጥልቁን ውኃ እንደ ድስት ያፈላዋል፤ባሕሩንም እንደ ቅባት መያዣ ይበጠብጠዋል። 32  በመንገዱ ላይ የሚያብረቀርቅ ፈለግ እየተወ ያልፋል። ተመልካችም ጥልቁ ውኃ ሽበት ያለው ይመስለዋል። 33  በምድር ላይ ያለፍርሃት የተፈጠረ፣እንደ እሱ ያለ ፍጡር የለም። 34  ትዕቢተኛ በሆነው ሁሉ ላይ በቁጣ ያፈጣል። ግርማ በተላበሱ የዱር እንስሳት ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

አዞ ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እንግጫ።”
ቃል በቃል “በእሾህ።”
ወይም “ተርበትብተህ ትወድቃለህ።”
ቃል በቃል “የፊቱን።”
“ጀርባው ላይ ያሉት እርስ በርስ የተጣበቁና በረድፍ የተቀመጡ ቅርፊቶች እንዲታበይ ያደርጉታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ጥርስ መሳይ ጉጦች ያሉት የእህል መውቂያ።