ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 10:1-33

  • ከእስራኤል ታሪክ የምናገኘው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ (1-13)

  • “ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” (14-22)

    • የይሖዋ ማዕድና የአጋንንት ማዕድ (21)

  • ነፃነትና ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት (23-33)

    • “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” (31)

10  እንግዲህ ወንድሞች፣ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች+ እንደነበሩና ሁሉም በባሕር መካከል እንዳለፉ+ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤  ሁሉም ከሙሴ ጋር በመተባበር በደመናውና በባሕሩ ተጠመቁ፤  ደግሞም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ፤+  በተጨማሪም ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ።+ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዓለት ይጠጡ ነበርና፤ ይህም ዓለት ክርስቶስን ያመለክታል።*+  ይሁንና አምላክ በአብዛኞቹ ስላልተደሰተ በምድረ በዳ ወድቀው ቀርተዋል።+  እነሱ ጎጂ የሆኑ ነገሮችን እንደተመኙ እኛም እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ለእኛ ምሳሌ ሆነውልናል።+  “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ። ከዚያም ሊጨፍሩ ተነሱ” ተብሎ እንደተጻፈው ከእነሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ።+  ከእነሱ አንዳንዶቹ የፆታ ብልግና* ፈጽመው ከመካከላቸው 23,000 የሚሆኑት በአንድ ቀን እንደረገፉ እኛም የፆታ ብልግና* አንፈጽም።+  ከእነሱ አንዳንዶቹ ይሖዋን* ተፈታትነው በእባቦች እንደጠፉ እኛም አንፈታተነው።+ 10  በተጨማሪም ከእነሱ አንዳንዶቹ በማጉረምረማቸው+ በአጥፊው እንደጠፉ+ አጉረምራሚዎች አትሁኑ። 11  እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ በእነሱ ላይ ደረሱ፤ የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።+ 12  በመሆኑም የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።+ 13  በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም።+ ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤+ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።+ 14  ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ።+ 15  ይህን የምናገረው ማስተዋል ላላቸው ሰዎች ነው፤ የምናገረው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 16  የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም መቋደስ አይደለም?+ የምንቆርሰውስ ቂጣ ከክርስቶስ አካል መቋደስ አይደለም?+ 17  ምክንያቱም እኛ ብዙ ብንሆንም ቂጣው አንድ ስለሆነ አንድ አካል ነን፤+ ሁላችንም የምንካፈለው ከዚሁ አንድ ቂጣ ነውና። 18  እስቲ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ተመልከቱ፦ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ተቋዳሾች አይደሉም?+ 19  እንግዲህ ምን እያልኩ ነው? ለጣዖት የተሠዋ ነገር የተለየ ፋይዳ አለው ማለቴ ነው? ወይስ ጣዖት ዋጋ አለው ማለቴ ነው? 20  እንዲህ ማለቴ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አሕዛብ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቧቸውን ነገሮች የሚሠዉት ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት ነው ማለቴ ነው፤+ ከአጋንንት ጋር እንድትተባበሩ ደግሞ አልፈልግም።+ 21  የይሖዋን* ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ “ከይሖዋ* ማዕድ”+ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም። 22  ወይስ ‘ይሖዋን* እያስቀናነው ነው’?+ እኛ ከእሱ ይበልጥ ብርቱዎች ነን እንዴ? 23  ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ያንጻል ማለት አይደለም።+ 24  እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።+ 25  ከሕሊናችሁ የተነሳ ምንም ጥያቄ ሳታነሱ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ማንኛውንም ነገር ብሉ፤ 26  “ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ የይሖዋ* ነውና።”+ 27  አማኝ ያልሆነ ሰው ቢጋብዛችሁና መሄድ ብትፈልጉ ከሕሊናችሁ የተነሳ ምንም ጥያቄ ሳታነሱ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ። 28  ይሁንና አንድ ሰው “ይህ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበ ነው” ቢላችሁ ይህን ለነገራችሁ ሰውና ለሕሊና ስትሉ አትብሉ።+ 29  እንዲህ ስል ስለ ራሳችሁ ሕሊና ሳይሆን ስለ ሌላው ሰው ሕሊና መናገሬ ነው። ነፃነቴ በሌላው ሰው ሕሊና ለምን ይፈረድበት?+ 30  አመስግኜ የምበላ ከሆነ ባመሰገንኩበት ነገር ለምን እነቀፋለሁ?+ 31  ስለዚህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።+ 32  ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪካውያን እንዲሁም ለአምላክ ጉባኤ እንቅፋት አትሁኑ፤+ 33  እኔ ብዙዎች እንዲድኑ የእነሱን እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በማደርገው ነገር ሁሉ፣+ ሁሉንም ሰው ለማስደሰት እንደምጥር እናንተም እንዲሁ አድርጉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ክርስቶስ ነበር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።