ነህምያ 6:1-19

  • በግንባታ ሥራው ላይ የተነሳው ተቃውሞ ቀጠለ (1-14)

  • ቅጥሩ በ52 ቀናት ውስጥ ተሠርቶ ተጠናቀቀ (15-19)

6  ሳንባላጥ፣ ጦብያ፣+ የዓረብ+ ተወላጅ የሆነው ጌሼምና የቀሩት ጠላቶቻችን ቅጥሩን መልሼ እንደገነባሁና+ ክፍተቶቹ ሁሉ እንደተደፈኑ ሲነገራቸው (ምንም እንኳ ገና መዝጊያዎቹን በበሮቹ ላይ ባልገጥማቸውም)፣+  ሳንባላጥና ጌሼም “እስቲ መጥተህ በኦኖ+ ሸለቋማ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዱ ለመገናኘት ቀጠሮ እንያዝ” የሚል መልእክት ወዲያውኑ ላኩብኝ። ሆኖም እኔን ለመጉዳት አሲረው ነበር።  በመሆኑም “ትልቅ ሥራ እየሠራሁ ስለሆነ ወደዚያ መውረድ አልችልም። ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ምክንያት ለምን ሥራው ይስተጓጎል?” ብለው እንዲነግሯቸው መልእክተኞችን ላክሁባቸው።  እነሱም ያንኑ መልእክት አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም በላኩብኝ ቁጥር ይህንኑ መልስ መለስኩላቸው።  ከዚያም ሳንባላጥ አገልጋዩን ያልታሸገ ደብዳቤ በእጁ አስይዞ ለአምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት ላከብኝ።  ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንተም ሆንክ አይሁዳውያኑ ለማመፅ እያሴራችሁ+ መሆኑን ብሔራት ሁሉ ሰምተዋል፤ ጌሼምም+ ይህንኑ እየተናገረ ነው። ቅጥሩንም እየገነባህ ያለኸው ለዚሁ ነው፤ እንደተባለው ከሆነ ደግሞ ንጉሣቸው ልትሆን ነው።  በተጨማሪም በመላው ኢየሩሳሌም ‘በይሁዳ ንጉሥ አለ!’ ብለው ስለ አንተ እንዲያውጁ ነቢያትን ሾመሃል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ንጉሡ ጆሮ መድረሳቸው አይቀርም። ስለሆነም መጥተህ በጉዳዩ ላይ ብንነጋገር ይሻላል።”  እኔ ግን እንዲህ ስል መለስኩለት፦ “ከተናገርከው ነገር መካከል አንዱም አልተፈጸመም፤ ሁሉም ነገር አንተ ራስህ በአእምሮህ* የፈጠርከው ነው።”  ምክንያቱም ሁሉም “እጃቸው ስለሚዝል ሥራው እንደሆነ አይጠናቀቅም” በማለት ሊያስፈራሩን ይሞክሩ ነበር።+ በዚህ ጊዜ እጆቼን አበርታልኝ ብዬ ጸለይኩ።+ 10  ከዚያም የመሄጣቤል ልጅ ወደሆነው ወደ ደላያህ ልጅ ወደ ሸማያህ ቤት ሄድኩ፤ እሱም ቤቱ ውስጥ ነበር። እንዲህም አለኝ፦ “ሊገድሉህ ስለሚመጡ በእውነተኛው አምላክ ቤት ይኸውም ቤተ መቅደሱ ውስጥ መቼ እንደምንገናኝ እንቀጣጠር፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋ። አንተን ለመግደል በሌሊት ይመጣሉ።” 11  እኔ ግን “እንደ እኔ ያለ ሰው መሸሽ ይገባዋል? ደግሞስ እንደ እኔ ያለ ሰው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብቶ በሕይወት ሊኖር ይችላል?+ በፍጹም አልገባም!” አልኩት። 12  ከዚያም ይህን ሰው አምላክ እንዳላከው ከዚህ ይልቅ ጦብያና ሳንባላጥ+ በእኔ ላይ ይህን ትንቢት እንዲናገር እንደቀጠሩት ተገነዘብኩ። 13  ይህን ሰው የቀጠሩት አስፈራርቶ ኃጢአት እንድሠራ እንዲያደርገኝና በዚህም የተነሳ ስሜን የሚያጠፉበት ምክንያት በማግኘት ሊሳለቁብኝ ፈልገው ነው። 14  አምላኬ ሆይ፣ ጦብያና+ ሳንባላጥ የሚያደርጉትን ይህን ነገር እንዲሁም እኔን ለማስፈራራት ተደጋጋሚ ሙከራ የሚያደርጉትን ነቢዪቱ ኖአድያህንና ሌሎቹን ነቢያት አስብ። 15  ቅጥሩም በኤሉል* ወር በ25ኛው ቀን በ52 ቀናት ውስጥ ተሠርቶ ተጠናቀቀ። 16  ጠላቶቻችን በሙሉ ይህን ሲሰሙና በዙሪያችን ያሉት ብሔራትም ይህን ሲያዩ በኀፍረት ተዋጡ፤*+ ይህ ሥራ የተከናወነው በአምላካችን እርዳታ እንደሆነም ተገነዘቡ። 17  በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ የተከበሩ ሰዎች+ ለጦብያ ብዙ ደብዳቤዎችን ይልኩለት የነበረ ሲሆን እሱም መልስ ይጽፍላቸው ነበር። 18  ጦብያ የኤራ+ ልጅ የሸካንያህ አማች ስለነበርና ልጁ የሆሃናን ደግሞ የቤራክያህን ልጅ የመሹላምን+ ሴት ልጅ ስላገባ በይሁዳ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በታማኝነት ከጎኑ እንደሚቆሙ ምለውለት ነበር። 19  በተጨማሪም ዘወትር ስለ እሱ መልካም ነገሮችን ይነግሩኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እኔ የምለውንም ለእሱ ያወሩለት ነበር። ጦብያም እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በልብህ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በገዛ ዓይናቸው ፊት ክፉኛ ወደቁ።”