መዝሙር 51:1-19
ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። ከቤርሳቤህ ጋር ግንኙነት ከፈጸመ በኋላ ነቢዩ ናታን መጥቶ ባነጋገረው ጊዜ ዳዊት ያቀረበው ማህሌት።+
51 አምላክ ሆይ፣ እንደ ታማኝ ፍቅርህ መጠን ሞገስ አሳየኝ።+
እንደ ታላቅ ምሕረትህ መተላለፌን ደምስስ።+
2 ከበደሌ ሙሉ በሙሉ እጠበኝ፤+ከኃጢአቴም አንጻኝ።+
3 መተላለፌን በሚገባ አውቃለሁና፤ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነው።*+
4 አንተን፣ አዎ ከማንም በላይ አንተን* በደልኩ፤+በአንተ ዓይን ክፉ የሆነውን ነገር ፈጸምኩ።+
ስለዚህ አንተ በምትናገርበት ጊዜ ጻድቅ ነህ፤በምትፈርድበት ጊዜም ትክክል ነህ።+
5 እነሆ፣ በደለኛ ሆኜ ተወለድኩ፤እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ።*+
6 ከልብ የመነጨ እውነት ደስ ያሰኝሃል፤+ልቤን* እውነተኛ ጥበብ አስተምረው።
7 ንጹሕ እሆን ዘንድ በሂሶጵ ከኃጢአቴ አንጻኝ፤+ከበረዶም የበለጠ እነጣ ዘንድ እጠበኝ።+
8 ያደቀቅካቸው አጥንቶች ደስ እንዲላቸው፣+የደስታንና የሐሴትን ድምፅ አሰማኝ።
9 ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ፤*+የፈጸምኳቸውንም ስህተቶች ሁሉ አስወግድ።*+
10 አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤+በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር።+
11 ከፊትህ አትጣለኝ፤ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድ።
12 የአንተ ማዳን የሚያስገኘውን ደስታ መልስልኝ፤+አንተን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጤ እንዲቀሰቀስ አድርግ።*
13 ኃጢአተኞች ወደ አንተ እንዲመለሱ፣ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ።+
14 አምላክ ሆይ፣ የመዳኔ አምላክ፣+ አንደበቴ ጽድቅህን በደስታ ያስታውቅ ዘንድ+የደም ባለዕዳ ከመሆን አድነኝ።+
15 ይሖዋ ሆይ፣ አፌ ምስጋናህን እንዲያውጅከንፈሮቼን ክፈት።+
16 መሥዋዕት እንዲቀርብልህ አትፈልግምና፤ ቢሆንማ ኖሮ ባቀረብኩልህ ነበር፤+ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አያስደስትህም።+
17 አምላክን የሚያስደስተው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም።*+
18 በበጎ ፈቃድህ ለጽዮን መልካም ነገር አድርግላት፤የኢየሩሳሌምን ግንቦች ገንባ።
19 በዚያን ጊዜ የጽድቅ መሥዋዕቶች፣የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችና ሙሉ በሙሉ የሚቀርቡ መባዎች ደስ ያሰኙሃል፤በዚያን ጊዜ ኮርማዎች በመሠዊያህ ላይ ይቀርባሉ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ከአእምሮዬ አይጠፋም።”
^ ቃል በቃል “አንተን ብቻ።”
^ ወይም “እናቴ ከፀነሰችኝ ጊዜ አንስቶ ኃጢአተኛ ነኝ።”
^ ወይም “የውስጥ ሰውነቴን።”
^ ወይም “ሰውር።”
^ ወይም “ደምስስ።”
^ ቃል በቃል “በፈቃደኝነት መንፈስ ደግፈኝ።”
^ ወይም “አትንቅም።”