የማቴዎስ ወንጌል 27:1-66

  • ኢየሱስ ለጲላጦስ አልፎ ተሰጠ (1, 2)

  • ይሁዳ ታንቆ ሞተ (3-10)

  • ኢየሱስ ጲላጦስ ፊት ቀረበ (11-26)

  • ሰዎች አፌዙበት (27-31)

  • በጎልጎታ በእንጨት ላይ ተቸነከረ (32-44)

  • ኢየሱስ ሞተ (45-56)

  • ኢየሱስ ተቀበረ (57-61)

  • መቃብሩ እንዲጠበቅ አደረጉ (62-66)

27  በነጋ ጊዜም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል አንድ ላይ ተማከሩ።+  ካሰሩት በኋላ ወስደው ለአገረ ገዢው ለጲላጦስ አስረከቡት።+  አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ ጸጸት ተሰምቶት 30ዎቹን የብር ሳንቲሞች* ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ሽማግሌዎቹ ይዞ በመምጣት+  “ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ። እነሱም “ታዲያ እኛ ምን አገባን? የራስህ ጉዳይ ነው!”* አሉት።  ስለዚህ የብር ሳንቲሞቹን ቤተ መቅደሱ ውስጥ በትኖ ወጣ። ከዚያም ሄደና ታንቆ ሞተ።+  የካህናት አለቆቹ ግን የብር ሳንቲሞቹን ወስደው “ይህ ገንዘብ የደም ዋጋ ስለሆነ ግምጃ ቤት ውስጥ መግባት የለበትም” አሉ።  ከተመካከሩም በኋላ ለእንግዶች የመቃብር ቦታ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት።  በመሆኑም ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት”+ ተብሎ ይጠራል።  በዚህ ጊዜ በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፦ “ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ የገመቱትን፣ ለሰውየው የወጣውን የዋጋ ተመን ይኸውም 30ዎቹን የብር ሳንቲሞች ወሰዱ፤ 10  ይሖዋ* ባዘዘኝም መሠረት ሳንቲሞቹን ለሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉ።”+ 11  ኢየሱስም አገረ ገዢው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዢውም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው።+ 12  የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ በከሰሱት ጊዜ ግን ምንም መልስ አልሰጠም።+ 13  በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “በስንት ነገር እየመሠከሩብህ እንዳሉ አትሰማም?” አለው። 14  እሱ ግን አገረ ገዢው እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም። 15  አገረ ገዢው ሁልጊዜ በዚህ በዓል ወቅት፣ ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚፈልጉትን ማንኛውንም እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።+ 16  በዚያን ጊዜ በዓመፀኝነቱ የታወቀ በርባን የተባለ እስረኛ ነበራቸው። 17  በመሆኑም ሕዝቡ በተሰበሰቡ ጊዜ ጲላጦስ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ወይስ ክርስቶስ የሚባለውን ኢየሱስን?” አላቸው። 18  ጲላጦስ ይህን ያለው አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ነው። 19  በተጨማሪም በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ “በእሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለተሠቃየሁ በዚያ ጻድቅ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት። 20  ይሁንና የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ በርባን እንዲፈታላቸው፣+ ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይጠይቁ ዘንድ ሕዝቡን አግባቡ።+ 21  አገረ ገዢውም መልሶ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነሱም “በርባንን” አሉ። 22  ጲላጦስም “እንግዲያው ክርስቶስ የሚባለውን ኢየሱስን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው። ሁሉም “ይሰቀል!”* አሉ።+ 23  እሱም “ለምን? ምን ያጠፋው ነገር አለ?” አላቸው። እነሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ የባሰ መጮኻቸውን ቀጠሉ።+ 24  ጲላጦስ ያደረገው ጥረት ምንም የፈየደው ነገር እንደሌለ ከዚህ ይልቅ ሁከት እያስነሳ መሆኑን በመገንዘብ “ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ። ከዚህ በኋላ ተጠያቂ የምትሆኑት እናንተ ናችሁ” በማለት ውኃ አምጥቶ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። 25  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ መልሰው “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ።+ 26  ከዚያም በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ+ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።+ 27  በዚህ ጊዜ የአገረ ገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ አገረ ገዢው መኖሪያ ቤት ወሰዱት፤ ሠራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ።+ 28  ልብሱንም ገፈው ቀይ መጎናጸፊያ አለበሱት፤+ 29  የእሾህ አክሊል ጎንጉነውም በራሱ ላይ ደፉበት፤ በቀኝ እጁም የመቃ ዘንግ አስያዙት። በፊቱ ተንበርክከውም “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ አሾፉበት። 30  ደግሞም ተፉበት፤+ መቃውንም ወስደው ራሱን ይመቱት ጀመር። 31  ሲያፌዙበት ከቆዩ በኋላም መጎናጸፊያውን ገፈው የራሱን መደረቢያዎች አለበሱት፤ ከዚያም በእንጨት ላይ እንዲቸነከር ይዘውት ሄዱ።+ 32  እየሄዱም ሳሉ ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው አገኙ። ሰውየውንም ኢየሱስ የሚሰቀልበትን የመከራ እንጨት* እንዲሸከም አስገደዱት።*+ 33  የራስ ቅል ቦታ የሚል ትርጉም ወዳለው ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ+ በደረሱ ጊዜ 34  ሐሞት* የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤+ እሱ ግን ከቀመሰው በኋላ ሊጠጣው አልፈለገም። 35  እንጨት ላይ ከቸነከሩት በኋላ ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ፤+ 36  በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። 37  እንዲሁም “ይህ የአይሁዳውያን ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የተከሰሰበትን ጉዳይ የሚገልጽ ጽሑፍ ከራሱ በላይ አንጠልጥለው ነበር።+ 38  በዚያን ጊዜ ሁለት ዘራፊዎች ከእሱ ጋር፣ አንዱ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው በእንጨት ላይ ተሰቅለው ነበር።+ 39  በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡት ነበር፤+ ራሳቸውንም እየነቀነቁ+ 40  “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ፣+ እስቲ ራስህን አድን! የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት* ላይ ውረድ!” ይሉት ነበር።+ 41  የካህናት አለቆችም እንደዚሁ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች ጋር ሆነው እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ጀመር፦+ 42  “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! የእስራኤል ንጉሥ+ ከሆነ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት* ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። 43  በአምላክ ታምኗል፤ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’+ ብሎ የለ፤ አምላክ ከወደደው እስቲ አሁን ያድነው።”+ 44  ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ የተሰቀሉት ዘራፊዎችም እንኳ ሳይቀሩ ልክ እንደዚሁ ይነቅፉት ነበር።+ 45  ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አገሩ በሙሉ በጨለማ ተሸፈነ።+ 46  በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ይህም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው።+ 47  በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ “ይህ ሰው ኤልያስን እየተጣራ ነው” ይሉ ጀመር።+ 48  ወዲያውኑም ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ በመሄድ ሰፍነግ* ወስዶ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ውስጥ ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠው።+ 49  የቀሩት ግን “ተወው! ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። 50  ኢየሱስ ዳግመኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ።*+ 51  በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ+ ከላይ እስከ ታች+ ለሁለት ተቀደደ፤+ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጣጠቁ። 52  መቃብሮችም ተከፈቱ፤ በሞት ካንቀላፉት ቅዱሳን ሰዎች መካከልም የብዙዎቹ አስከሬኖች ወጡ፤ 53   ብዙ ሰዎችም አዩአቸው። (ኢየሱስ ከተነሳ በኋላ ሰዎች ከመቃብር ስፍራው ወጥተው ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ገቡ።)* 54  ሆኖም መኮንኑና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች የምድር ነውጡንና የተከሰቱትን ነገሮች ሲመለከቱ እጅግ ፈርተው “ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አሉ።+ 55  ኢየሱስን ለማገልገል ከገሊላ ጀምሮ አብረውት የነበሩ ብዙ ሴቶችም+ እዚያ ሆነው ከሩቅ ይመለከቱ ነበር፤ 56  ከእነሱም መካከል መግደላዊቷ ማርያም፣ የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ይገኙ ነበር።+ 57   ቀኑ በመገባደድ ላይ ሳለ የአርማትያስ ሰው የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ሀብታም መጣ፤ እሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር።+ 58  ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጠየቀ።+ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ።+ 59  ከዚያም ዮሴፍ አስከሬኑን ወስዶ በንጹሕ በፍታ ገነዘው፤+ 60  ከዓለት ፈልፍሎ በሠራው በራሱ አዲስ መቃብር ውስጥም አኖረው።+ ከዚያም አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን ደጃፍ ዘጋውና ሄደ። 61  በዚህ ጊዜ መግደላዊቷ ማርያምና ሌላዋ ማርያም ከመቃብሩ ፊት ለፊት እዚያው ተቀምጠው ነበር።+ 62  እነዚህ ነገሮች የተከናወኑት ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ቀን+ ነበር። በማግስቱም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን አንድ ላይ ተሰብስበው ጲላጦስ ፊት ቀረቡና 63  እንዲህ አሉ፦ “ክቡር ሆይ፣ ያ አስመሳይ በሕይወት ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሳለሁ’ ብሎ የተናገረው ትዝ አለን።+ 64  ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው እንዳይሰርቁትና+ ለሕዝቡ ‘ከሞት ተነስቷል!’ እንዳይሉ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ መቃብሩ እንዲጠበቅ ትእዛዝ ስጥልን። አለዚያ ይህ የኋለኛው ማታለያ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል።” 65  ጲላጦስም “ጠባቂዎች መውሰድ ትችላላችሁ። ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ” አላቸው። 66  ስለዚህ ሄደው ድንጋዩ ላይ ማኅተም በማድረግ መቃብሩን አሸጉ፤ ጠባቂም አቆሙ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።
ወይም “እሱ የአንተ ችግር ነው!”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል!”
ወይም “በመሸከም የግዳጅ አገልግሎት እንዲፈጽም አደረጉት።”
“ከዕፀዋት የሚዘጋጅ የማደንዘዝ ባሕርይ ያለው መራራ ንጥረ ነገር ሳይሆን አይቀርም።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የመከራ እንጨት” የሚለውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻው ላይ “የመከራ እንጨት” የሚለውን ተመልከት።
ስፖንጅ ተብሎ ከሚጠራ የባሕር እንስሳ የሚገኝ ውኃን መምጠጥና መያዝ የሚችል ነገር።
ወይም “ሞተ።”
በቅንፍ ውስጥ ያለው ሐሳብ ከጊዜ በኋላ የተከናወነውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው።