የማቴዎስ ወንጌል 8:1-34

  • በሥጋ ደዌ የተያዘ ሰው ተፈወሰ (1-4)

  • አንድ የጦር መኮንን ያሳየው እምነት (5-13)

  • ኢየሱስ በቅፍርናሆም ብዙ ሰዎችን ፈወሰ (14-17)

  • ኢየሱስን መከተል (18-22)

  • ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አሰኘ (23-27)

  • ኢየሱስ አጋንንቱን ወደ አሳማዎች እንዲገቡ ፈቀደላቸው (28-34)

8  ከተራራው ከወረደ በኋላ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው።  በዚህ ጊዜ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ወደ እሱ መጥቶ በመስገድ* “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው።+  ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው።+ ወዲያውኑ ከሥጋ ደዌው ነጻ።+  ከዚያም ኢየሱስ “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤+ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤+ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ።+ ካህናቱም ማስረጃውን ይመለከታሉ” አለው።  ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ አንድ የጦር መኮንን ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ ሲል ተማጸነው፦+  “ጌታዬ፣ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ ቤት ተኝቷል፤ በጣም እየተሠቃየ ነው።”  እሱም “መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።  መኮንኑም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ፣ አንተ ወደ ቤቴ ትገባ ዘንድ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን እዚሁ ሆነህ አንድ ቃል ተናገር፣ አገልጋዬም ይፈወሳል።  እኔ ራሴ የምታዘዛቸው የበላይ አዛዦች አሉ፤ ለእኔም የሚታዘዙ የበታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” 10  ኢየሱስ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት+ ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም። 11  ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማያትም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በማዕድ ይቀመጣሉ።+ 12  የመንግሥተ ሰማያት ልጆች ግን ውጭ ወዳለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ።”+ 13  ከዚያም ኢየሱስ መኮንኑን “ሂድ። እንደ እምነትህ ይሁንልህ”+ አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።+ 14  ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ሲመጣ የጴጥሮስ አማት+ ትኩሳት ይዟት ተኝታ አገኛት።+ 15  እጇንም ሲዳስሳት+ ትኩሳቱ ለቀቃት፤ ተነስታም ታገለግለው ጀመር። 16  ከመሸ በኋላ ሰዎች አጋንንት ያደሩባቸውን ብዙ ሰዎች ወደ እሱ አመጡ፤ መናፍስቱንም በአንድ ቃል አስወጣ፤ እየተሠቃዩ የነበሩትንም ሁሉ ፈወሰ፤ 17  ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ “እሱ ሕመማችንን ተቀበለ፤ ደዌያችንንም ተሸከመ” ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።+ 18  ኢየሱስ በዙሪያው ብዙ ሰዎች እንደተሰበሰቡ ባየ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው።+ 19  ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ “መምህር፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።+ 20  ኢየሱስ ግን “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” አለው።+ 21  ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “ጌታ ሆይ፣ በመጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።+ 22  ኢየሱስም “አንተ እኔን መከተልህን ቀጥል፤ ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው” አለው።+ 23  ከዚያም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጀልባ ላይ ተሳፈሩ።+ 24  እነሆ፣ በጉዞ ላይ ሳሉ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ማዕበል ስለተነሳ ጀልባዋ በውኃ ተሞልታ ልትሰጥም ተቃረበች፤ ኢየሱስ ግን ተኝቶ ነበር።+ 25  እነሱም ወደ እሱ ቀርበው ቀሰቀሱትና “ጌታ ሆይ፣ ማለቃችን እኮ ነው፤ አድነን!” አሉት። 26  እሱ ግን “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?”* አላቸው።+ ከዚያም ተነስቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።+ 27  ሰዎቹም ተደንቀው “ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” አሉ። 28  ባሕሩን ተሻግሮ ገዳሬኖስ* ወደተባለው ክልል በደረሰ ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ቦታ ወጥተው ከእሱ ጋር ተገናኙ።+ ሰዎቹ በጣም ኃይለኛ ከመሆናቸው የተነሳ ማንም ሰው በዚያ ለማለፍ አይደፍርም ነበር። 29  እነሱም “የአምላክ ልጅ ሆይ፣ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን?+ የመጣኸው ጊዜው ሳይደርስ+ ልታሠቃየን ነው?”+ ብለው ጮኹ። 30  ከእነሱ ራቅ ብሎ ብዙ የአሳማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።+ 31  አጋንንቱም “የምታስወጣን ከሆነ ወደ አሳማው መንጋ ስደደን” ብለው ይማጸኑት ጀመር።+ 32  እሱም “ሂዱ!” አላቸው። እነሱም ወጥተው ወደ አሳማዎቹ ሄዱ፤ የአሳማውም መንጋ በሙሉ ከገደሉ አፋፍ* እየተንደረደረ በመውረድ ባሕሩ ውስጥ ሰጥሞ አለቀ። 33  እረኞቹ ግን ሸሽተው ወደ ከተማው በመሄድ አጋንንት ባደሩባቸው ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጨምሮ የሆነውን ነገር ሁሉ አወሩ። 34  ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ለማግኘት ወጣ፤ ሰዎቹም ባዩት ጊዜ አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድ ለመኑት።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እሱን እጅ በመንሳት።”
ወይም “ለምን ትርበተበታላችሁ?”
ማር 5:1 እና ሉቃስ 8:26 ላይ ጌርጌሴኖን ተብሎም ተጠርቷል።
ወይም “ገደላማ ከሆነው የባሕሩ ዳርቻ።”