ኢዮብ 3:1-26
3 ከዚህ በኋላ ኢዮብ መናገርና የተወለደበትን ቀን መርገም ጀመረ።+
2 ኢዮብም እንዲህ አለ፦
3 “የተወለድኩበት ቀን፣‘ወንድ ልጅ ተፀነሰ!’ የተባለበትም ሌሊት ይጥፋ።+
4 ያ ቀን ጨለማ ይሁን።
በላይ ያለው አምላክ አያስበው፤ብርሃንም አይፈንጥቅበት።
5 ድቅድቅ ጨለማ* ይውረሰው።
ጥቁር ደመና ይረፍበት።
ቀንን የሚያጨልም ነገር ያሸብረው።
6 ያን ሌሊት ጨለማ ይውረሰው፤+ከዓመቱ ቀኖች መካከል ያ ሌሊት ደስ አይበለው፤ከወራቱም ቁጥር መካከል አይደመር።
7 አዎ፣ ያ ሌሊት መሃን ይሁን!እልልታም አይሰማበት።
8 ቀንን የሚረግሙ፣ሌዋታንንም*+ መቀስቀስ የሚችሉ ቀኑን ይርገሙት።
9 አጥቢያ ኮከቦቹ ይጨልሙ፤የቀን ብርሃንን ቢጠብቅም አያግኝ፤የንጋትንም ጮራ አይመልከት።
10 የእናቴን ማህፀን በሮች አልዘጋምና፤+ችግርንም ከዓይኔ አልሰወረም።
11 ምነው ስወለድ በሞትኩ!
ምነው ከማህፀን ስወጣ በተቀጨሁ!+
12 የሚቀበሉኝ ጉልበቶች፣የሚያጠቡኝም ጡቶች ለምን ተገኙ?
13 ይህን ጊዜ ሳልረበሽ በተጋደምኩ ነበርና፤+በተኛሁና እረፍት ባገኘሁ ነበር፤+
14 በአሁኑ ጊዜ ፈራርሰው ያሉ ቦታዎችን ለራሳቸው ከገነቡ*የምድር ነገሥታትና አማካሪዎቻቸው ጋር፣
15 ወይም ቤታቸውን በብር ከሞሉወርቅ ካላቸው መኳንንት ጋር ባረፍኩ ነበር።
16 እንደተሰወረ ጭንጋፍ፣ፈጽሞ ብርሃን እንዳላዩ ልጆች ለምን አልሆንኩም?
17 በዚያ ክፉዎች እንኳ ከሚረብሽ ነገር ተገላግለዋል፤የዛሉ ሰዎች በዚያ አርፈዋል።+
18 በዚያ እስረኞች በአንድነት ተረጋግተው ይኖራሉ፤አስገድዶ የሚያሠራቸውን ሰው ድምፅ አይሰሙም።
19 በዚያ ትንሹም ሆነ ትልቁ አንድ ናቸው፤+ባሪያውም ከጌታው ነፃ ወጥቷል።
20 እሱ መከራ ላይ ላለ ሰው ብርሃን፣ለተመረሩ ሰዎችስ* ሕይወት ለምን ይሰጣል?+
21 ሞትን ቢመኙም የማያገኙት ለምንድን ነው?+
ከተሰወረ ሀብት ይበልጥ ይሹታል፤
22 መቃብር ሲያገኙ ሐሴት ያደርጋሉ፤እጅግም ደስ ይላቸዋል።
23 መንገዱ ለጠፋበት፣አምላክም ዙሪያውን ላጠረበት ሰው+ ለምን ብርሃን ይሰጣል?
24 በምግቤ ፋንታ ሲቃ ተናንቆኛልና፤+የሥቃይ ጩኸቴ+ እንደ ውኃ ይፈስሳል።
25 የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፤ያሸበረኝም ነገር ደርሶብኛል።
26 ሰላምም ሆነ እርጋታ አላገኘሁም፤ እረፍትም አልነበረኝም፤ይልቁንም መከራ አልተለየኝም።”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ጨለማና የሞት ጥላ።”
^ አዞን ወይም በውኃ ውስጥ የሚኖርን ትልቅና ኃይለኛ የሆነ ሌላ እንስሳ እንደሚያመለክት ይታመናል።
^ “የፈራረሱ ቦታዎችን ለራሳቸው ከገነቡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ነፍሳቸው ለተመረረችስ።”